
ከ 5 ሰአት በፊት
ምዕራባውያን በዩክሬን ወረራ ምክንያት ሩሲያ ከዓለም የኢኮኖሚ ሰንሰለት እንድትነጠል ለማድረግ ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛል።
ማዕቀቦችን በመጣል የአገሪቱ ምጣኔ ሀብትን ከዓለም አቀፉ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር እንዲቋረጥ ለማድረግ ሞክረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል ክሶች የእስር ማዘዣ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ አውጥቶባቸዋል። የምዕራቡ ዓለም ጫና እና ግፊት እየሠራ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።
ጫናውን መቋቋም እንደሚችሉ የሚናገሩት ፑቲን ከሰሞኑ የብሪክስ ጉባኤን በአገራቸው እያስተናገዱ ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከጥቅምት 12 -14/2017 ዓ.ም. በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ በሩሲያዋ ካዛን ከተማ ተሰብስበዋል።
የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን እና በፈጣን ዕድገት የሚገኙ ከ20 በላይ አገራት መሪዎች በዚህ ጉባኤ ላይ ይታደማሉ።
ክሬምሊን በሩሲያ ከተደረጉ “ታላላቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክስተቶች አንዱ” ሲል ነው ጉባኤውን የጠራው።
በዚህ ጉባኤ “ማስተላላፍ የተፈለገው ግልጹ መልዕክት ሩሲያን ለማግለል የተደረገው ሙከራ አልተሳካም የሚል ነው” ይላሉ በጂኦ ፖለቲካ እና ፖሊሲ ላይ የሚያተኩረው ማክሮ አድቫይዘሪ የተሰኘው ድርጅት መሥራች ክሪስ ዌፈር።
“ሩሲያ ማዕቀቦችን ተቋቁማ አይበገሬነትዋን እያሳየች እንደሆነ ከክሬምሊን የተላከ ትልቅ መልዕክት ነው። ከውጭ እንደሚታየው ሳይሆን በአገሪቷ ውስጥ ከባድ ስንጥቆች እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን በጂኦፖለቲካዊ ዕይታ ሩሲያ ወዳጆች እንዳሏት ማሳያ ነው። እነዚህም የሩሲያ አጋሮች ይሆናሉ” ይላሉ።
- ኢትዮጵያን በአባልነት የተቀበለው ብሪክስ የአሜሪካን ልዕለ ኃያልነት ይገዳደር ይሆን?31 ነሐሴ 2023
- ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?26 ነሐሴ 2023
- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ተወሰነ24 ነሐሴ 2023

ለመሆኑ የሩሲያ ወዳጆች እነማን ናቸው?
ብሪክስ የሚለው የእንግሊዝኛ ምኅጻረ ቃል አባል አገራቱን ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን የሚያመለክት ነው።
የምዕራቡን ዓለም መሪነትን በመጻረር እንዲሁም ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላላፍ እንዲኖር በማለት የተመሠረተ እንደሆነ የሚነገርለት ብሪክስ፤ አድማሱን በማስፋት ግብፅን፣ ኢትዮጵያን፣ ኢራንን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በአዳዲስ አባልነት ተቀብሏል። ሳዑዲ አረቢያም የአገራቱን ጥምረት እንድትቀላቀል ተጋብዛለች።
የብሪክስ አባል አገራት የዓለማችን 45 በመቶ ሕዝብ ይኖርባቸዋል። የአገራቱ ምጣኔ ሀብት ሲደመርም ከ28.5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ ይህም የዓለማችንን 28 በመቶ ምጣኔ ሀብት አካባቢ ነው።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ሌሎች ተጨማሪ 30 አገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ወይም ከድርጅቱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። አንዳንዶቹም እነዚህ አገራት በጉባዔው ላይ ተሳታፊ ናቸው።
በሩሲያ ካዛን በተካሄደው ጉባኤ ከተንጸባረቁ ጉዳዮች አንዱ ብሪክስ ምን ያህል “አብዛኛውን የዓለም ሕዝብ” እንደሚያቅፍ ይጠቀሳል። ጉባኤው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጂኦ ፖለቲካዊ መድረክ ያላቸውን ስፍራ ከማሳየት ውጪ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?
የምዕራባውያንን ጫና ለመቀልበስ የሚፈልጉት ፑቲን ለዓለም አቀፍ መገበያያዎች ከዶላር ሌላ አማራጭ ገንዘብ እንዲኖር የብሪክስ አባል አገራትን ለማሳመን ተስፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።
“የሩሲያ የምጣኔ ሀብት እያጋጠመው ያሉ ችግሮች የወጭ ንግድ እና ክፍያ ጋር የተገናኙ ናቸው። አብዛኛው ደግሞ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ቁርኝት አለው” ይላሉ ዌፈር።
“የአሜሪካው ግምጃ ቤት በዓለም ንግድ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው፤ ምክንያቱም ዋነኛ መገበያያ ገንዘቡ የአሜሪካ ዶላር ስለሆነ ነው። የሩሲያ ዋነኛ ፍላጎት የአሜሪካን የዶላር የበላይነት መስበር ነው።
“ለዚህም የብሪክስ አገራት አማራጭ የንግድ ዘዴ እንዲዘረጉ እና ዶላር፣ ዩሮን ወይም የትኛውን የቡድን 7 አገራት ገንዘቦችን ያላከተተ የወጭ ንግድ እና የመገበያያ ሥርዓት እንዲኖር ትፈልጋለች። በዚያውም ማዕቀቡንም ጥርስ አልባ ማድረግ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ሆኖም ተቺዎች በብሪክስ አባል አገራት ውስጥ ያለውን ልዩነት በመንቀስ “ፍጹም ተመሳሳይ አቋም” የያዙ አይደሉም ይላሉ።
“በአንዳንድ መንገዶች ቻይና እና ሕንድ በማንኛውም ነገር መስማማት አለመቻላቸው ለምዕራቡ ዓለም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሁለቱ አገራት ቢስማሙ ብሪክስ በዓለማችን ላይ ታላቅ ተጽእኖ ማሳደር ይችል ነበር” ሲሉ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎት የሆነው ጎልድማን ሳክስ የቀድሞ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጂም ኦኔል ይገልጻሉ።
“ቻይና እና ሕንድ አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ ለመጠላለፍ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀነስ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህን አገራት በምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ ትብብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የከበደ ፈተና ነው” ሲሉ ጂም ኦኔል ያስረዳሉ ።
ጂም ኦኔል ብሪክ የሚለውን ምኅጻረ ቃለ ለአራት በፈጣን ዕድገት ላይ ላሉ አገራት ሲያልሙት የነበሩ ሲሆን፣ አገራቱ ወደ ዓለም አቀፉ የፖሊሲ ውሳኔ እንደሚመጡም ያምኑ ነበር።
ነገር ግን አምስት ሆነው ብሪክስን የፈጠሩት አገራት የምዕራቡን በተለይም በዓለም ሰባት ታላላቅ ኢኮኖሚዎች (ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ) የሚመራውን ዓለም ለመገደዳደር እየሞከሩ ይገኛሉ።
በአባላት አገራቱ መካከል ሕንድ እና ቻይና ብቻ አይደለም ልዩነት ያላቸው። በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት የሚወዛገቡት አዳዲሶቹ አባላት ኢትዮጵያ እና ግብፅ ያላቸው ውጥረት ከሯል።
በተለይም ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣና ስጋት ላይ ጥሏል። ግብፅ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን መላኳን ተከትሎ ውጥረቶች ነግሷል።
የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት ማስታወቋ ይገለጻል።
ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ያላቸውን ውጥረት ለማርገብ ንግግሮች ቢኖሩም ሁለቱ አገራት በቀጣናው ላይ ያሉ ተቀናቃኞች ናቸው።
“ሁሉም በአንድ ትልቅ ነገር ላይ በመሠረታዊነት ይስማማሉ የሚለው ሃሳብ በእውነቱ የማይረባ ነው” ይላሉ ኦኔል።
ሩሲያ በፀረ- ምዕራባውያን በተሞላ ትርክቶች ስለ “አዲስ የዓለም ሥርዓት” መመሥረት አስፈላጊነትን ስትናገር እንደ ሕንድ ያሉ የብሪክስ አባላት ከምዕራቡ ዓለም ጋር መልካም የፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።
በሩሲያዋ ካዛን ከተማ በተደረገው ጉባኤ የቭላድሚር ፑቲን ተግባር በአባል አገራቱ መካከል ያለውን ልዩነት በማቃለል ለሩሲያ ሕዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድነትን መሳል ነው።