የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ

25 ጥቅምት 2024, 14:20 EAT

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጭ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን በደቡብ ሱዳን ዋና መዲና ጁባ ጥቅምት 21 እና ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም. ሊያካሄዱ ነው።

የ2025 የቻን ማጣሪያ ውድድር መርሐ ግብር በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀምር ሲሆን ሁለቱ አገራት በሦስተኛ አገር ሜዳ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።

የሁለቱ አገራት የመጀመሪያው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ታንዛኒያ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ሁለቱም ጨዋታ ጁባ እንደሚከናወን ዘግይተው የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል ካፍ መስፈርት የሚያሟላ ስታድየም የላቸውም።

በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን አፍሪካ ዋንጫ ከአውሮፓውያኑ የካቲት 1 እስከ 28/2025 ይካሄዳል።

ቻን በሦስት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚካሄድ መሆኑን ካፍ አረጋግጧል።

ውድድሩን ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ እንደሚያዘጋጁት የካፍ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ አሳውቀዋል።

ኤርትራ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ የውድድር ጨዋታ አድርገው የማያውቁት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለፍልሚያው ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በቅርቡ የተሾሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለማጣሪያው ጨዋታ የመለመሏቸውን ተጫዋቾች ጠርተዋል።

ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በጁባ ስታድየም የሚደረገው የካፍን መስፈርት የሚያሟሉ ስታድየሞች ባለመኖራቸው ይሁን በሌላ ምክንያት የሚታወቅ ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ እንደምትጫወት ይፋ የተደረገው በግብፅ መዲና ካይሮ በተካሄደው የዕጣ ድልድል ሥነ-ሥርዓት ነው ።

ኤርትራ በቻን ውድድር ከተሳተፈች በርካታ ዓመታት አስቆጥራለች።

አልፎም የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች መሳተፍ ካቆመ ቆይቷል።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ አሸናፊው ቡድን ከሱዳን እና ታንዛኒያ አሸናፊ ጋር ይጋጠማል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ለጨዋታው እየተዘጋጀ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በኤርትራ በኩል ግን ቡድኗ ጁባ ላይ በሚካሄደው ግጥሚያ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።