
ከ 4 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደም የሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባል ማይክ አሜስበሪ አንድን ግለሰብ በቡጢ መትተው ሲጥሉ የሚያሳይ የደህንነት ካሜራ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ከፓርቲያቸው እንዲታገዱ ተወሰነ።
ዴይሊ ሜይል ይፋ ባደረገው ቪዲዮ ላይ የረንኮርን እና የሄልስቢ አካባቢ የህዝብ እንደራሴው ግለሰቡ መንገድ ላይ ከወደቀ በኋላም መማታታቸውን መቀጠላቸው ታይቷል።
የቼሻየር ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የ55 ዓመት ግለሰብ በፍቃደኝነት ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት እና በጉዳዩ ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እንደተለቀቀ አስታውቋል።
አሜስበሪ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ጥረት ተደርጓል።
የፓርላማ አባሉ በፍሮድሻም፣ ቼሻየር በጎዳና ላይ በወደቀው ግለሰብ ላይ ሲጮሁ እና ሲሳደቡ የሚያሳይ ሌላ ቪዲዮ በኤክስ ላይ ተለጥፏል።
“ማይክ አሜስበሪ በአርብ ምሽቱ ክስተት ዙሪያ የቼሻየር ፖሊስን ሲተባበሩ ቆይተዋል” ሲል የሌበር ፓርቲ ቃል አቀባይ አስታውቋል።
“የሌበር ፓርቲ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ አሜስቤሪን ከሌበር ፓርቲ አባልነት አግዶታል።”
በፓርላማ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነትም መነጠቃቸውም ተነግሯል።
በቪዲዮው ከተቀረጸው ጉዳይ በፊት ስለነበረው ነገር ምን እንደተፈጠረ ግልጽ አይደለም ።
በቪዲዮው መጀመሪያ ላይ አሜስበሪ “የፓርላማ አባልን ከእንግዲህ አታስፈራራም አይደል?” በማለት ጮኽው ሲናገሩ ይሰማል።
የዴይሊ ሜይል ቪዲዮ ከመውጣቱ በፊት የቼሻየር ፖሊስ በሰጠው መግለጫ “ፖሊስ በፍሮድሻም ስለተፈጸመ ጥቃት ሪፖርት ደርሶታል” ብሏል።
“አንድ ቅሬታ አቅራቢ መንገድ ላይ እንደደረሰበት ተናግሯል። ምርመራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው” ሲል አክሏል።
- እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ‘ሊጋነን ወይም ሊቃለል’ እንደማይገባ መሪዋ ተናገሩከ 5 ሰአት በፊት
- ኬንያዊው የማህበረሰብ አንቂ ‘ጭምብል ባጠለቁ’ ሰዎች ታፍኖ ተወሰደከ 5 ሰአት በፊት
- ትራምፕ ለአሜሪካ ከፈጣሪ የተላኩ መሪ ናቸው ብለው የሚያምኑት ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖችከ 6 ሰአት በፊት
የ55 ዓመቱ የፓርላማ አባል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ “ትናንት ምሽት ከጓደኞቼ ጋር ከተዝናናሁ በኋላ ስጋት ስለተሰማኝ በአንድ ክስተት ውስጥ ተሳትፌያለሁ።”
“ዛሬ ጠዋት የሆነውን ነገር ለመግለጽ የቼሻየር ፖሊስን አነጋግሬ ነበር።”
“ከዚህ በላይ አስተያየት ባልሰጥም ግን በቼሻየር ፖሊስ በተፈለግኩበት ጊዜ ሁሉ እተባበራለሁ” ሲሉ አክለዋል።
ስለእሑዱ ቪዲዮ እና የፖሊስ መግለጫ በተመለከተ የተጠየቁት የትምህርት ሚንስትሯ ብሪጅት ፊሊፕሰን “ፖሊስ አሁን ጉዳዩን እየመረመረ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እኔ እንደማስበው እነሱ እየተከታተሉት ስለሆነ እና ስራቸውን እንዲሰሩ መፍቀድ አስፈላጊ በመሆኑ ብዙ የምናገረው ነገር የለም” ሲሉ አክለዋል።
አሜስበሪ ስለ ድርጊቶቹ መልስ የሚሰጣቸው ጥያቄዎች እንዳሉ የተናገሩት የወግ አጥባቂ ፓርቲ ቃል አቀባይ “በጥልቀት መመርመራቸው ትክክል ነው” ብለዋል።
በሐምሌ ወር ምርጫ በአሜስበሪ የተሸነፈውን ዕጩ ያቀረበው የሪፎርም ዩኬ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የህዝብ እንደራሴው ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
አባታቸው በአንድ ቡጢ ምክንያት በሞት ያጡት የቀድሞ የወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል ዴሄና ዴቪሰን ቪዲዮውን “አሰቃቂ” ሲሉ ጠርተውታል።
በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም “ፖሊስ እየመረመረ በመሆኑ እውነታዎቹ በቅርቡ እንደሚወጡ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።
“አንድ ጊዜ ቡጢ ሊያመጣ በሚችለውን አደጋ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከዋን ፓንች ዩኬ ጋር በመሥራት ዓመታትን አሳልፌያለሁ።”
“ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ አይነት ግጭት በጭራሽ እና በፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።”
አሜስበሪ ከ2017 ጀምሮ በቼሻየር የሌበር ፓርቲን ወክለው ፓርላማ አባል ሆነው አገልግለዋል።
በሐምሌ ወር በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ክልላቸውን በ14 ሺህ 696 ድምፍ በማግኘት አሸንፈዋል።