
ከ 5 ሰአት በፊት
እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ሊጋነን ወይም ሊቃለል እንደማይገባ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ተናገሩ።
መንፈሳዊ መሪው አገራቸው ከእስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩበት ባለበት በአሁኑ ወቅት ያሰሙት ንግግር የተመጠነ እና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ነው።
እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ አራት ወታደሮች የተገደሉባት ኢራን “ተገቢውን አጸፋዊ ምላሽ” እንደምትሰጥ የተናገሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው “ኢራን ጦርነት አልፈለገችም” ብለዋል።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት ጥቅምት 16/ 2017 ዓ.ም. በበርካታ የኢራን ግዛቶች ያሉ ወታደራዊ ተቋማትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
እስራኤል፣ ኢራን መስከረም 21/2017 ዓ.ም. ላስወነጨፈቻቸው ወደ 200 የሚጠጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች አጸፋዊ ምላሽ ነው ብላለች።
እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የአየር መከላከያ እና የሚሳኤል ማምረቻ ሥርዓቶችን ማሽመድመድ ችላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናግረዋል። ጥቃቶቹ የኢራንን የመላከል አቅም እና ሚሳኤል የማምረት ብቃትን በእጅጉ የጎዳ ነውም ብለዋል።
በጋዛ ላይ የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት ኔታንያሁ “ጥቃቱ ትክክለኛ፣ ከበድ ያለ እና ዓላማውን ያሳካ” ነው ብለውታል።
“ገዥው አካል አንድ ቀላል መርኅን ሊረዳ ይገባል። ይህም የሚጎዳንን የትኛውንም አካል እኛም እንጎዳዋለን” ብለዋል።
ኢራን የደረሰባትን ጥቃት ማቃለሏን ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሚሳዔሎች መምከናቸውን እንዲሁም መክሸፍ ያልቻሉት በአየር መከላከያ ሥርዓቶች ላይ የተገደበ ጉዳት ብቻ አድርሰዋል ብለዋል።
- ትንታኔ፡ በእስራኤል ላይ አጸፋ በመመለስ እና ደካማ ሆኖ በመታየት አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀችው ኢራን27 ጥቅምት 2024
- እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን የአየር ጥቃት የሚያሳይ ቪዲዮ27 ጥቅምት 2024
- እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቢገቡ ምን ይከሰታል? በወታደራዊ አቅምስ ይመጣጠናሉ?4 ጥቅምት 2024
የኢራን መንፈሳዊ መሪ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት “የኢራን ሕዝብ እና መንግሥትን ሥልጣን ባማከለ መልኩ እንዲሁም የአገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ እርምጃዎችን በእስራኤል ላይ መውሰድ የባለሥልጣናቱ ፈንታ ነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ፔዝሽኪያንም በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የመንፈሳዊ መሪውን ንግግር ያስተጋቡ ሲሆን “ጦርነት አንፈልግም ነገር ግን የአገራችን እና የሕዝባችንን መብት እናስከብራለን” ብለዋል።
እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከተጠበቀው በላይ የተገደቡ እንደነበሩ ተገልጿል። አሜሪካ የኢራን የነዳጅ እና የኑክሌር ተቋማትን እንዳትመታ በአጋሯ እስራኤል ላይ በይፋ ጫና ያደረገች ሲሆን፣ እነዚህም ጥቃቶች ይህንን መመመሪያ ቴል አቪቭ ማክበሯን ያሳያል ተብሏል።
ኢራን እስራኤል ልትፈጽማቸው ስላቀደቻቸው ጥቃቶች ከሰዓታት በፊት “ፍንጭ አግኝታለች” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እሁድ ዕለት ተናግረዋል።
“በዚያች ምሽት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ጥቆማዎች ደርሶን ነበር” ሲሉ አባስ አራግቺ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ምዕራባውያን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ያለው ግጭት ወደ ሁለንተናዊ ጦርነት ሊያመራ ይችላል በሚል ስጋት ኢራን ምላሽ እንዳትሰጥ አሳስበዋል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃንም ከጥቃቱ በኋላ የሕዝቡ እንቅስቃሴ በተለመደ መልኩ መቀጠሉን እና የደረሰውም ጉዳት ውስንነት ነበረው ነው በሚል መልኩ ዘገባዎችን አስተላልፈዋል።