
የጽሁፉ መረጃ
- ፀሐፊ,ጄሬሚ ቦዌን
- የሥራ ድርሻ,የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታዒ
- 27 ጥቅምት 2024
እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ጦርነት የበለጠ ያባብሰዋል። የከፋ አደጋን ማስወገድም ሆነ ቀውሱን የበለጠ የሚያቀጣጥለው ውሳኔ በኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ እና ቁልፍ አማካሪዎቻቸው በሚያሳልፏቸው ውሳኔው ላይ የተመሠረቱ ይሆናሉ።
ከበርካታ አስቸጋሪ ምርጫዎች መካከልም ከሁሉ የቀለለውን ፈታኙን በትንሹን በመጥፎ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው። በአንደኛው የውሳኔያቸው ጫፍ ላይ በሌላ ዙር የባለስቲክ ሚሳዔሎች ውርጅብኝ ለእስራኤል ምላሽ መስጠት ሲሆን፣ ይህ ከሆነ ደግሞ እስራኤል እንደገና የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
በሌላ በኩል ሁለቱ አገራት በየግዛቶቻቸው ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን የአውዳሚ የጥቃት ልውውጥ መስመር አበጅተውለት ለመግታት መወሰን ነው። ነገር ግን ኢራን በእስራኤል ላይ አጸፋ ከመመለስ ከተቆጠበች በእስራኤል ወታደራዊ ኃይል እና በዩናይትድ ስቴትስ የማይወላውል ፖለቲካዊ የሚደገፍ ምክንያት ተገትታ ደካማ እንድትመስል የሚያደርጋት አደጋ ደቅኖባታል።
በመጨረሻም የኢራን የበላይ መሪ እና አማካሪዎቻቸው በእነሱ ዕይታ የኢራን እስላማዊ መንግሥት አገዛዝ ኅልውና ላይ በጣሙን ትንሹን ጉዳት የሚያስከትለው ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።
ባዶ ማስፈራሪያ?
የኢራን መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን ከእስራኤል ጥቃቶች በፊት እና በኋላ በነበሩት ሰዓታት ውስጥ ባቀረቡት ጠንካራ መግለጫ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ አጸፋ ለመመለስ ቀድሞውኑም ውሳኔ ላይ መደረሱን የሚያመለክት መልዕክት አቅርበዋል። የመግለጫው የቋንቋ አጠቃቀም እራስን ከጥቃት የመከላከል መብትን በመጥቀስ ከእስራኤል ጋር ተመሳሳይነት ነበረው። ነገር ግን የሚከተለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ኢራን ዛቻዋን ልትቀለብስ የምትችልበት ዕድል ከፍያለ ይመስላል።
ኢራን በእስራኤል ላይ መስከረም 21/2017 ዓ.ም. ባሊስቲክ ሚሳዔሎቿን ከተኮሰች የምታወጣቸው መግለጫዎች ወጥ አቋምን የሚገልጹ ናቸው። ከሳምንት በፊት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለቱርክ የኤንቲቪ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት “በኢራን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ለእኛ ቀይ መስመር እንደማለፍ ይቆጠራል። እንዲህ ያለው ጥቃት ደግሞ ምላሽ ሳይሰጠው አይታለፍም” ብለዋል።
የእስራኤሉ ጥቃት ከሰዓታት በፊት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባቃይ “የእስራኤል መንግሥት በኢራን ላይ የሚፈጽመው ማንኛውም ጥቃት በሙሉ ኃይል ምላሽ ይሰጠዋል” ብለዋል። ኢራን ለሚፈጸምባት ውስን የእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንደማትሰጥ የሚነገረው “በጣም አሳሳች እና መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል።
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ከጥቃቱ በኋላ ወደ ጦር ሰፈራቸው ሲመለሱ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 51 ላይ እንደተገለጸው” ራስን የመከላከል መብት እንዳላቸው አመልክቷል። መግለጫው ኢራን ለውጭ ጥቃቶች ምላሽ የመስጠት መብት እና ግዴታ እንዳለባት ታምናለች ብሏል።
- እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን የአየር ጥቃት የሚያሳይ ቪዲዮ27 ጥቅምት 2024
- እስራኤል በኢራን ላይ ሌሊቱን ስለፈጸመችው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው26 ጥቅምት 2024
- እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቢገቡ ምን ይከሰታል? በወታደራዊ አቅምስ ይመጣጠናሉ?4 ጥቅምት 2024
አደገኛው የአጸፋ ጥቃት ምልልስ
ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ከ1,200 በላይ ሰዎችን የተገደሉበትን እና ከ250 በላይ የሚሆኑ ታግተው ከተወሰዱበትን የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ እስራኤል ኢራንን የጥቃቱ ዋነኛ ደጋፊ አድርጋ ነው የምትመለከታት። በዚህም ነገሮች እየተባባሱ ባለበት ሁኔታ እስራኤል ኢራን እስራኤል ልታጠቃት አጋጣሚ እየጠበቀች ነው በሚል ስጋት ከእስራኤል ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት መግባት እንደማትፈልግ ደጋግማ ስትገልጽ ነበረ።
ያ ማለት ግን በእስራኤል እና በአጋሮቿ ላይ በአብዛኛው አደገኛ የሆነውን እና የማይቋረጠውን ነገር ግን በዝቅተኛ ደረጃ የምታሳድረውን ጫናዋን ለማቆም ተዘጋጅታለች ማለት አይደለም።
የቴህራን ባለሥልጣናት ከሁሉን አቀፍ ጦርነት ይልቅ የተሻለ ሀሳብ እንዳላቸው አስበው ነበር። በዚህም ኢራን እስራኤልን ለማጥቃት “የትግል ትብብር” የተባሉትን አጋሮቿን እና ወኪሎቿን ተጠቅማለች። የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የመርከብ ጉዞን አግደው ጥቃት ፈጽመዋል። ከሊባኖስ በሄዝቦላህ የሚተኮሱት ሮኬቶች ቢያንስ 60 ሺህ እስራኤላውያንን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።
እስራኤል ወደ ሊባኖስ በፈጸመችው የአጸፋ ጥቃት በስድስት ወራት ውስጥ ምናልባት በእጥፍ የሚበልጡ የደቡብ ሊባኖስ ነዋሪዎች ከቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። ሄዝቦላህ የሚፈጽምባትን ጥቃት አቁሞ ከድንበሩ አካባቢ ወደኋላ ካልተመለሰ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቃ ነበር።
ይህ ሳይሆን ሲቀር እስራኤል ኢራን በእጅ አዙር ከምታካሂደው የተራዘመ እና አሰልቺ ጦርነት ለመውጣት ወሰነች። በዚህም የኢራን እስላማዊ መንግሥት ሚዛኑን እንዲስት ያደረገ እና ዕቅዱን የበታተነ ተከታታይ ኃይለኛ ጥቃቶችን አድርሳለች። ለዚህም ነው ከአሁኑ የእስራኤል ጥቃት በኋላ የኢራን መሪዎች ምርጫቸው እጅግ አስቸጋሪ የሚሆነው።
እስራኤል በኢራን እና በአጋሮቿ ላይ የምታሳድረውን ጫና አጠናክራለች።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሙሉ ድጋፍ እና ግዙፍ የጦር መሳሪያዎች አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤልን ለመከላከል የአሜሪካ የባሕር እና የአየር ኃይልን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በመላክ ጭምር አስተማማኝ አጋር ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የእስራኤል ጦር አዛዦች የሚመጣውን አደጋ ለመጋፈጥ ወስነዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ የእስራኤል የአየር ጥቃት በሶሪያ ዋና ከተማ በደማስቆ የሚገኘውን የኢራን ዲፕሎማሲያዊ ጽህፈት ቤት በከፊል አውድሟል። በዚህም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ ከፍተኛ የኢራን አዛዥ የሆኑት ብርጋዲየር ጄኔራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲን ተገድለዋል።

አሜሪካኖች ከጥቃቱ በኋላ ለሚከሰት ሁኔታ ኃይሎቻቸውን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ለማድረግ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በእስራኤል ስላልተሰጣቸው ተቆጥተው ነበር። ነገር ግን እስራኤል እርምጃዋ ያስከተለውን መዘዝ ስትጋፈጥ የጆ ባይደን ድጋፍ አልተለያትም። ኢራን ለተፈጸመባት ጥቃት ምላሽ ከቀናት በኋላ የድሮኖች እና ሚሳዔሎች ውርጅብኝ በእስራኤል ላይ ስታዘንብ በአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስ ጉዳት እንዳይደርስባት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውላታል።
እየተባባሰ ያለው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወደ ባሰ ደረጃ ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት የገባቸው ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤልን “አሸናፊ መሆኗን ተቀብላ” ጦርነቱን እንድታቆም ጠይቀው ነበር።
እስራኤል ግን ከኢራን እና ከአጋሮቿ ጋር የምታደርገውን ጦርነት በተደጋጋሚ አጠናክራ ቀጥላለች። ዋነኛው ጥቃትም የኢራን በጣም ወሳኝ አጋር በሆነው በሊባኖሱ ሄዝቦላህ ላይ የፈጸመቸው ነው። ኢራን የሄዝቦላህን የጦር መሳሪያ የፊት መስመር መከላከያዋ ቁልፍ አካል አድርጋ ለዓመታት ስትጠቀም ቆይታለች። ዕቅዱም እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም ሄዝቦላህ ከሊባኖስ ድንበር እስራኤልን እንደሚመታ ስለሚታወቅ ጥቃት እንዳትፈጽም ሊያግዳት ይችላል የሚል ነው።
እስራኤል ሄዝቦላህን በማጥቃት በኩል በአውሮፓውያኑ 2006 የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ ያዘጋጀችውን ዕቅድ አሁን ተግባራዊ በማድረግ ቀድማ እርምጃ በመውሰድ ቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳትን አድርሳለች።
በዚህም ሄዝቦላህ ሳያውቅ ለአባላቱ እንዲገዛ ያደረጋቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የመልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያዎችን (ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ) አፍንድታለች፣ ደቡባዊ ሊባኖስን ወራለች በተጨማሪም እስራኤልን ለአስርት ዓመታት አምርረው በመቃወም የሚታወቁትን የቡድኑን መሪ ሐሳን ናስራላህን ገድላለች።
እስካሁንም በቀጠለው የአየር ድብደባዋም ከ2,500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ያሳወቁ ሲሆን፣ ምጣኔ ሀብቷ ተሽምድምዶ ባለችው አገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
መሪውን እና አብዛኛውን የጦር መሳሪያ ክምችቱን በማጣቱ እየተንገዳገደ ያለው ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ አሁንም እየተዋጋ የእስራኤል ወታደሮችን እየገደለ እና በርካታ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል እየተኮሰ ነው።
ዕቅዷ ሊንኮታኮት የተቃረበባት ኢራን መልሶ ማጥቃት እንዳለባት ደምድማለች። ምንም ዓይነት አጸፋ ሳትሰጥ አጋሮቿ ተዋግተው እንዲሞቱ ብቻ የምታደርግ ከሆነ በቀጣናው ባሉ ፀረ እስራኤል እና ፀረ ምዕራባውያን ኃይሎች መካከል ያላትን የመሪነት ሚና የሚያሳጣት ይሆናል። አገሪቱ ባለፈው ጥቅምት ወር ከፍተኛ የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል ላይ ፈጽማ ነበር።
ባለፈው አርብ ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም. ሌሊት እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት አጸፋ ነበረ። ይህ እርምጃ ብዙዎች ከጠበቁት በላይ የዘገየው የእስራኤል ዕቅድ መረጃ አፈትልኮ በመውጣቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ላይም ከፍተኛ ጥቃት እየፈፀመች ነው። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ ቮልከር ተርክ የእስራኤል ጦር መላውን ሕዝብ ለቦምብ ጥቃት፣ ለከበባ እና ለረሃብ አደጋ የዳረገበት የጋዛው ጦርነት እጅግ ጨለማው ጊዜ ነው ብለውታል።
እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው የአሁኑ ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን ከሰሜን ጋዛ ለማራቅ የነደፈችው መሆኑን ከእስራኤላውያኑ ውጪ ማንም ሊያውቅ አይቻልም። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ምናልባት የእስራኤል ስሌት አካል ሊሆን ይችላል።
ጦርነቱ ከቁጥጥር እንዳይወጣ ማድረግ
አገራት ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምላሽ ካልሰጡ እንደ ደካማ እና ስጋት እንዳልሆኑ እንደሚታዩ ካመኑ ተከታታይ ዙሮችን እና የአጸፋ ጥቃቶችን ማቆም ከባድ ነው። ጦርነቶች ከቁጥጥር ውጪ የሚወጡትም በዚህ ምክንያት ነው።
አሁን ጥያቄው ኢራን ቢያንስ በዚህ የጦርነቱ ደረጃ ለእስራኤል አጸፋ እንደማትመልስ የመጨረሻውን ቃል ለመስጠት ተዘጋጅታለች ወይ የሚለው ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤል በመስከረም መጨረሻ ላይ የወሰደችውን የአጸፋ እርምጃ ደግፈዋል። ነገር ግን በድጋሚ እስራኤል የኢራንን ወሳኝ ተቋማት ማለትም የኑክሌር፣ የነዳጅ ዘይት እና የጋዝ ማዕከላትን እንዳትመታ በመንገር አደገኛው ግጭት እንዳይባባስ ሞክረዋል። ለዚህም እስራኤልን ለመከላከል የሚያስችል ፀረ ሚሳዔል ሥርዓት በማሰመራት ኔታኒያሁ ምክራቸውን እንዲሰሙ ለማድረግ ሞክረዋል።
ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ የሁለቱም የእስራኤል እና የኢራን ቀጣይ ስለሚሆነው ነገር የሚያስቡት ስሌት አካል ነው። ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ከተመረጡ፣ የኢራንን አጸፋ ለመመለስ እስራኤል በኑክሌር፣ በነዳጅ ዘይት እና በጋዝ ተቋማቷ ላይ ጥቃት ብትፈጽም እንደ ባይደን ስጋት ላይኖራቸው ይችላል።
አሁን መካከለኛው ምሥራቅ ከሁለቱም በኩል የሚወሰደውን እርምጃ እየጠበቀ ነው። እስራኤል የኢራንን ወሳኝ ተቋማት ላለመምታት መወሰኗ ቴህራን አጸፋዋን ለሌላ ጊዜ እንድታስተላለፍ ሊያደርጋት ይችላል።
ይህም ባለፈው መስከረም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢራን ለአዲስ ዙር የኑክሌር ንግግር ዝግጁ መሆኗን መግለጿን ተከትሎ ቢያንስ ዲፕሎማቶች ሥራቸውን እንዲሠሩ በቂ ጊዜ ይሰጣል።
ይህ ሁሉ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ ባሻገር ላለው ዓለም ትልቅ ውጤት ያለው ነገር ነው። ኢራን ሁልጊዜ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የመታጠቅ ፍላጎት እንዳላት የሚቀርብባትን ክስ ታስተባብላለች።
ነገር ግን በእጇ ያለው የኑክሌር እውቀቱ እና የዩራኒየም ማበልፀግ አቅም መሳሪያው በቀላሉ በእጇ እንዲገባ ያደርጋታል። መሪዎቿ ጠላቶቻቸውን ለመከላከል አዲስ መንገድ መፈለግ ስላለባቸው ለባለስቲክ ሚሳዔሎቻቸው የሚሆኑ የኑክሌር አረሮችን ማዘጋጀት አጀንዳቸው ሊሆን ይችላል።