October 28, 2024 

በክፍለ ሀገራት የሚሰሩ የኮሪደር ልማቶችን ተችተው የነበሩት የፓርላማ አባል ፅሁፋቸውን አጥፍተው ሚድያዎችን ከሰሱ

(መሠረት ሚድያ)- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ኬፈና ኤፋ “ደጋግሜ ብጽፍም አትሰልቹኝ” በማለት የዛሬ ሳምንት ገደማ ባቀረቡት ፅሁፋቸው በክልሎች በኮሪደር ልማት ስም የሚተገበረው ፕሮጀክት እንደ ደርግ የመንደር ምስረታ አደገኛ እየሆነ መጥቷል ብለው ነበር፡፡

ዶ/ር ኬፈና አያይዘውም “ወፍ እንኳን ጎጆ አላት፣ ምነዉ ክቡር የሆነውን የሰዉ ልጅ ከወፍ አሳነስን? እኔ ፀረ-ልማት አይደለሁም። የመንግሥትን የልማት አቅጣጫ ለማደናቀፍም አይደለም። አጉል ተወዳጅነትም ለማትረፍ አልሞክርም፣ ተረዱኝ” ብለው አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር።

የፓርላማ አባሉ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለውን የኮሪደር ፕሮጀክት እደግፋለሁ ያሉ ሲሆን “በክልሎች ያለው ግን እኔ አጅግ አላማረኝም፡፡ ሀገር እየፈረሰ ነዉ፡፡ በልማት ስም እየተኬደበት ያለ መንገድ ለዜጋ ሲኦል ሆኗል” ብለው መረጃ አጋርተው ነበር።

ይሁንና ዶ/ር ኬፈና ይህን ፅሁፍ ማጋራታቸውን ተከትሎ መሠረት ሚድያን ጨምሮ በርካታ ሌሎች ሚድያዎች ጉዳዩን መዘገባቸው ከመንግስት ጫና እንዳስከተለባቸው ሰምተናል።

በመጀመርያ ፅሁፉን ያቀረቡበትን የፌስቡክ አካውንታቸውን የቆለፉ ሲሆን ቆይተው ደግሞ ይህን ከላይ ያቀረብነውን አቋማቸውን ከገፃቸው ላይ ማጥፋታቸውን ተመልክተናል።

ከአምስት ቀን በፊት ደግሞ መሠረት ሚድያን እና ሌላ አንድ ሚድያን በስም በመጥቀስ ወቅሰዋል።

“ማሳበቅ የጋዜጠኝነት ሥነምግባር አይደለም” በማለት ፅሁፋቸውን የፌስቡክ አካውንታቸው ላይ ያሰፈሩት የፓርላማ አባሉ “ከሰሞኑ በሰጠሁት አስተያየት ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ውጭ ፅሑፌን ሆን ብለው ለራሳቸው እንዲመቻቸው አድርጎ በሚዲያቸው በማቅረብ ችግር ለመፍጠር ያደረጉት እኩይ ተግባር ተነጋግረንበታል” በማለት በጉዳዩ ዙርያ ከመንግስት አካላት ጋር ንግግር እንዳደረጉ ጠቁመዋል።

አክለውም “ኢትዮ ፎረምና መሠረት ሚዲያ የሚባሉ ሚዲያዎች የሠራችሁት ሥራ እጅግ ትክክል እንዳልሆነ መቀበል አለባችሁ። ዘመኑ ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት የብልፅግና ዘመን እንጂ እንዳለፉት ዘመናት ሰበብ አስባብ እየተፈለገ የአይንህ ቀለም አላማረኝም ተብለህ የሚትሰወርበት፣ የምትታሰርበት፣ የምትሰቃይበት ዘመን አይደለም” ያሉት አቶ ኬፈና “ጊዜው የሐሳብ ዘመን ነው። በኃላፊነት መንፈስ የምትንቀሳቀስበትና ስህተት እንኳን ከተፈጠረ እርስ በርስ የምትተራረምበት ዘመን እንጂ የደርግ ወይም ኢህአዲግ ዘመን አይደለም” ብለዋል።

ዶ/ር ኬፈና ይህንን ሚድያዎች የተቹበት ፅሁፍ በድጋሜ ከፌስቡክ ገፃቸው ላይ ማጥፋታቸውን ተመልክተናል።

ዶ/ር ኬፈና በዚህ ሁሉ ፅሁፋቸው ውስጥ ግን በምን መልኩ መሠረት ሚድያም ሆነ ሌሎች ሚድያዎች ሀሳባቸውን እንዳዛቡባቸው አልገለፁም፣ ወይም ያልፃፍኩትን አቀረቡ ብለው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውንጀላ አላቀረቡም።