ዝነኛው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ፈረሰ፣ ምትኩ በስፍራው ሊገነባ እንደሆነም ተሰምቷል

(መሠረት ሚድያ)- ለካዛንችስ አካባቢ ለአመታት ድምቀት ሆኖ የቆየው ፈንድቃ በኮሪደር ልማት ምክንያት መፍረሱ ታውቋል።
የባህል ማእከሉን ለማፍረስ ከ2015 ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቢቆዩም በስተመጨረሻ ባሳለፍነው ሳምንት እንደፈረሰ ታውቋል።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ ፈንድቃ የትዝታ ቦታ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች፣ ሙዚቀኞች እና ተወዛዋዦች መኖሪያ መሆኑ የሚነሳ ሲሆን በርካቶች ትዝታቸውን ያሳለፉበት ስፍራም ነበር።
“ፈንድቃ በካዛንቺስ ውስጥ አስፈላጊ የኢኮኖሚ ሞተር ነበር፣ በየዓመቱ ወደ 200 ሺህ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ይመጣሉ” የሚለው የባህል ማእከሉ ባለቤት አርቲስት መላኩ በላይ በጣሊያን ስታር 2022፣ በቲኤዲ ኅብረት 2022፣ በፕሪንስ ክላውስ ሎሬት 2020፣ ለሙዚቃ ቪዛ 2019 እና በፈረንሣይ ሜዳሊያ 2015 መሸለሙን ገልጿል።
“አዲስ አበባ ልማት እንደሚያስፈልጋት በመረዳት በፈንድቃ ደመቅ ያለ ኢትዮጵያዊ ባህል እየተጋራን አካባቢውን ለማልማት የቢዝነስና የሕንፃ ፕላን አዘጋጅተን ነበር” ብሎ ከዚህ በፊት ለሚድያዎች ተናግሮ የነበረው አርቲስት መላኩ አሁን ላይ ካዛንቺስ በተመሳሳይ ቦታ ፈንድቃን እንዲገነባ መንግስት ፍቃድ እንደሰጠው በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና በፈንድቃ ባህል ማዕከል ላይ የተሰራው “Take Me to Fendika” የተሰኘ ደክመተሪ ፊልም በአሜሪካ ቴክሳስ፣ ሂዩስተን በተደረገው 2ኛው የአፍሪካ የባህል ፊልም ፌስቲቫል (AFFRICUFF) ላይ በምርጥ ደክመንተሪ ዘርፍ አሸናፊ መሆኑ ታውቋል።
ዳይሬክተሩ ሲስኮ ብራድሌይ “ይህ እውነተኛ የቡድን ጥረት ነበር፤ በፈንድቃ የባህል ማዕከል ላሉ አርቲስቶች በሙሉ ፍቅር እና ምስጋና ይድረሳቸው ። እንደገና ለመገንባት በዚህ ትግል ውስጥ ቆመናል፣ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ እናመሰግናለን።” ሲል በማህበራዊ ድረገጹ ጽፏል።