October 28, 2024 

“አብያተ እምነት የሰማያዊ መንግሥት ተልዕኮ ማስፈጻሚያ ኤምባሲዎች በመሆናቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል”

(መሠረት ሚድያ)- እናት ፓርቲ አብያተ እምነት የሰማያዊ መንግሥት ተልዕኮ ማስፈጻሚያ ኤምባሲዎች በመሆናቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብሎ መግለጫ አውጥቷል።

መንግሥት የወንዝ ዳር፣ ጫካ፣ ኮሪደር… ወዘተ ፕሮጀክት በሚሉ መጠሪያዎች የሚያከናውነውን ፈረሳና የማፈናቀል ተግባር አስመልክቶ በቅርቡ የአገራችን የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥትና የሚመለከታችውን አዋጆች ጠቅሰን በትብብር ፓርቲዎች የጸና አቋማችንን መግለጻችን ይታወቃል ያለው ፓርቲው ከዚኹ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች የአምልኮ ሥፍራዎች ሕጋዊ ይዞታዎች ድንበር በማን አለብኝነት እየፈረሰ እንዳለና እንደሚፈርስ ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው መገንዘብ ችለናል ብሏል።

ፓርቲው አክሎም እየፈረሱ ካሉት በዋቢነት የሰበታ ጌቴሴማኒ ቤተደናግል ጠባባት የሴቶች ገዳም ይዞታ ከክብር በወረደ አኳኋን እንዲፈርስ ተደርጓል በማለት የከሰሰ ሲሆን ከየካቲት 12 አደባባይ ከፍ ብሎ ያለውና ከአምስቱ ዓመት የፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥ ታሪክ ያለው የአገር ባለውለታው የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ይዞታም ጠባብ የሆነውን ዐውደ ምሕረት የበለጠ በማጥበብ ከፊት ለፊቱ የገዳሙና የገዳሙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ፈረሳ እንደሚከናወንባቸው ፓርቲያችን መረጃ ደርሶታል ብሏል።

እናት ፓርቲ በመግለጫው ባለፉት ጥቂት ተከታታይ ዓመታት በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጅዶች እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሱ ቃጠሎዎች፤ በአገልጋዮችና ምእመናን ላይ የደረሱ አሰቃቂ ግድያዎች በኢትዮጵያ በትልቁ አገራዊ እሴታችን በሆናው ሃይማኖት ላይ የተጋረጠውን ኹለንተናዊ ጥቃት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብሏል።

ከዚኹ የቀጠለ በሚመስል አኳኋንና በተቀናጀ መልኩ በአዲስ አበባና አካባቢው አብያተ ክርስቲያን ይዞታዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የማፍረስ ተግባር ከውጭና ከውስጥ ተናቦ የሚተገበር መኾኑን መጠርጠር አያዳግትም በማለት ፓርቲው አቋሙን አጋርቶናል።