October 28, 2024 

በርካታ ነዳጅ የሚጠቀሙ ቅንጡ እና ውድ መኪናዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ እንደሆነ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በታገደበት በአሁኑ ወቅት በርካታ ነዳጅ የሚጠቀሙ ቅንጡ እና ውድ መኪናዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ እንደሆነ መሠረት ሚድያ ያደረገው ምርመራ ያሳያል።

ታድያ ከሁሉም በላይ መነጋገርያ የሆነው በታዋቂው የንግድ ሰው አቶ ሻቃ ጉርሜሳ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ፕሮሰስ ላይ የሚገኙት 700 ይደርሳሉ የተባሉት V8 መኪናዎች ጉዳይ ነው።

የ Shaka Mall ባለቤት የሆኑት አቶ ሻቃ መኪና በማስመጣት እና በመሸጥ ከበርካታ አመታት በፊት ጀምሮ ልምድ ያላቸው ቢሆኑም በዚህ ወቅት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ማስገባት መቻላቸው ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ሰምተናል።

በቅርቡ 700 V8 ላንድ ክሩዘር መኪናዎችን ሊያስገቡ ሂደት ላይ እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ላይ ጥሩ የአመራር ብቃት ላሳዩ የመንግስት ተሿሚዎች በስጦታ መልክ የሚበረከቱ መሆናቸው ተሰምቷል።

“መድሃኒት ፈልጎ ማግኘት ከባድ በሆነበት፣ ብታገኝም ዋጋው በማይቀመስበት አገር እንዲህ አይነት የሃብት ብክነት እየተፈፀመ ይገኛል” ያሉት አንድ ጉዳዩን የሚያውቁ የመረጃ ምንጫችን ናቸው።

የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን የተሽከርካሪ አጠቃቀም አስመልክቶ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዛሬ ስድስት አመት ያወጣው መመሪያ በበርካታ ተቋማት እየተተገበረ አለመሆኑ ተደጋግሞ እየተነሳ ይገኛል።

በመመሪያው ቁጥር 4 ንዑስ ቁጥር 1 ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ የፋይናንስ አጠቃቀም እንዲኖር ለከተማ ውስጥ ስራ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ ተደንግጓል።

በዚህ መሰረት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ቪ8፣ ቪ9፣ ፕራዶና ፓጃሮ ተሽከርካሪዎችን ከሚጠቀሙ ይልቅ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎችን ቢጠቀሙ ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ተገልፆ ነበር።

ይሁንና አሁን ድረስ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ቪ8 እና ሌሎች ተመሳሳይ መኪናዎችን ከተማዎች ውስጥ እንደሚጠቀሙ መሠረት ሚድያ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።