October 28, 2024

“28 ሰዓት በፈጀው ውጊያ የአገዛዙ ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ ሁኗል፤ ከፋኖ ጉዳት አልተመዘገበም።” አርበኛ ከፍያለው ደሴ

የአማራ ፋኖ በጎንደር የዘመቻ መምሪያ ኃላፊና የገብርዬ ክፍለጦር ዋና አዛዥ አርበኛ ከፍያለው ደሴ በደቡባዊ ጎንደር እየተደረጉ ባሉ ውጊያዎች ዙሪያ ከኢትዮ 251 ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጧት 12 ሰዓት የጀመረው ውጊያ እስከ ዛሬው ዕለት ረፋድ 4 ሰዓት የተደረገ ሲሆን በዚህ ውጊያ አገዛዙ ከባድ መሳሪያዎችን የተጠቀመ ሲሆን በከባድ መሳሪያም የመምህራን ቤትና የአርሶ አደሮችን ቤት አቃጥሏል፤ በአየር ኃይሉም ድብደባ ፈጽሟል፤ ሶስት ቦታዎች ላይም የድሮን ጥቃት በንጹሃን ላይ ፈጽሟል፣ የፋኖ ሰራዊት አንድም ጉዳት ሳይደርስበት በገብርዬ ክፍለጦር ብቻ 7 አምቡላንስ ሬሳ ጭኖ ወጥቷል፤ አሁንም ያልተነሳ ሬሳ አለ ሲል አርበኛ ከፍያለው ደሴ ለኢትዮ 251 ሚዲያ ገልጿል።

አርበኛ ከፍያለው ደሴ አገዛዙ ጀነራል መሐመድ ተሰማ፣ ጀነራል አለምሸት ደግፌን የጦር መሪ አድርጎ በርካታ ጀነራሎችንና ኮሎኔሎችን አሰልፎ ቢመጣም አብዛኛው ሰራዊቱ በምርኮ አስቀርተነዋል፣ ለሁለቱ ያቀደውን እቅድ በ28 ሰዓት ውስጥ እቅዱን መና አድርገንበታል፤ ተጋድሏችን አሁንም ይቀጥላል ብሏል።