
ከ 3 ሰአት በፊት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለሹመቱ “ብቁ አይደሉም” የሚል ትችት አቀረቡ።
የምክር ቤት አባላቱ ትችቱን ያቀረቡት የዶ/ር ጌደዮንን ጨምሮ ፓርላማው አምስት ሚኒስትሮችን ሹመት ባጸደቀበት ስብሰባው ላይ ነው።
የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ባካሄደው ስብሰባ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምጽ በአንድ ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል።
ሹመታቸው የጸደቀላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ እና የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ናቸው።
የሚኒስትሮቹ ሹመት ከመጽደቁ በፊት ሰባት የምክር ቤት አባላት በሹመቱ ላይ ያላቸው ጥያቄ እና አስተያየት አቅርበዋል። ከሰባቱ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ሦስት ብልጽግና ፓርቲ ተመራጮች ሹመቱን “አካታች”” እና “ታሪካዊ” በሚሉ ቃላት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ቀሪዎቹ አራቱ የተቃዋሚ ፓርቲ እና የግል ተመራጭ የፓርላማ አባላት ደግሞ የሥነ ሥርዓት እና ከሹመቱ ሂደት ጋር ተያያዙ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
በግል ተወዳድረው ፓርላማ የገቡት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ ዶ/ር ጌዲዮንን “በሕግ እውቀታቸው” እና በፍትህ ሚኒስትርነት ባከናወኑት ተግባር አድንቀው የውጭ ሚኒስትር የሚሆኑ ተሿሚ “ዲፕሎማሲውን የሚያውቁ እና ልምድ ያላቸው…” ቢሆኑ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ኡስታዝ ካሚል አክለውም “ዶ/ር ጌዲዮን ለዚህ የታጩበት ወይም ይሄ ሹመት የተሰጣቸው ሌላ ያላየነው [እና] የማናውቃቸው ነገሮቸ ካሉ ቢገለጹ” ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ “በዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ላይ ስጋት አለኝ” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ካላቸው የትምህርት ዝግጅት [አንጻር] በፍትህ ሚኒስቴር ሲሾሙ የፍትህ ዘርፉ ላይ የተሻለ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ ተስፋ አድርጌባቸው የነበሩ ወጣት ሚኒስትር ነበሩ” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ “ነገር ግን ከዶ/ር ጌዲዮን በፊት ከነበሩ ፍትህ ሚኒስትሮች የተለየ ምን አሳኩ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
- በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ውስጥ የፓርቲ አባላትን የሚያግደውን አንቀፅ የሚሽር ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ28 ጥቅምት 2024
- በነቀምቴ ከተማ ሁለት ታዳጊ ሴቶችን በቡድን የደፈሩ ወጣቶች እየተፈለጉ መሆኑን ፖሊስ ገለጸከ 4 ሰአት በፊት
- በጉራጌ ዞን “ከፋኖ ጋር በተያያዘ” ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተነገረከ 8 ሰአት በፊት

የምክር ቤት አባሉ አክለውም “በፍትህ ሚኒስትርነት የነበራቸው የሥራ ልምድ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ብቁ ያደርጋቸዋል ወይ የሚለውን አልገመገምነውም። ዶ/ር ጌዲዮን የእውቀት ችግር አለባቸው ብዬ አይደለም። ሙያቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። ነገር ግን አፈጻጸማቸውን ካየነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ሲጠይቅ ነበረውን የፍትህ ጥማት ከማስታገስ እና ያንን ከማርካት ይልቅ አሁንም የፍትህ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆን አድርገዋል የሚል ወቀሳ ማቅርብ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ደሳለኝ፤ “የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታችን ሳይነሳ ተጎትተን እንደ ሽፍታ ስንታሰር እና ለወራት ስንቀመጥ ሌሎችም ተገቢ ፍትህ ሳያገኙ ለዓመታት ሲንገላቱ የፍትህ ሚኒስቴር ምንም የሠራው ሥራ የለም፣ ከሳሹ ፍትህ ሚኒስቴር ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ዶ/ር ጌዲዮንን “ የፍትህ ዘርፉን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ” ሲሉ የከሰሱት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ስለሆነም ለዚያ ቦታ [ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት] ብቁ አይደሉም (unqualified)። [ሚኒስትር ሆነው] ለዚያ ቦታ መቅረብ የለባቸውም የሚል ሃሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ጌዲዮን የገዢው የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ወደ መንግሥት ኃላፊነት ከመጡ ወጣት ተሿሚዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ዶ/ር ጌዲዮን የቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶሪያ ተደረገው ድርድር የመንግሥት አንደኛው ተደራዳሪ ነበሩ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህርነት ሰፊ ልምድ ያላቸው ዶ/ር ጌድዮን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርስቲ፣ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ እና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተለያዩ የሕግ ዘርፎችን አስተምረዋል።
በሕግ ዘርፍ ከሚጠቀሱ ምሁራን መካከል የሆኑት ጌዲዮን (ዶ/ር) ለረጅም ጊዜ ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት የረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ላይ ከቀረቡት ትችቶች በተጨማሪ ሚኒስትሮቹ የተሾሙበት ሂደት ላይም ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ባርጠማ ፍቃዱ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ የተሰኑት ሚኒስትሮች ሹመታቸው ሳይጸድቅ ወደ ሥራ መግባታቸውን በማስታት የሥነ ሥርዓት ጥያቄ አቅርበዋል።
ለተነሱ ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ፤ “ዶ/ር ጌድዮንን በተመለከተ እንደ መሪ ፓርቲ እና መንግሥት የሚያሰማራቸውን አመራሮች የሚገመግምበት እና ውጤታቸውን የሚመዝንበት ሥርዓት አለው። በእኛ ግምገማ ዶ/ር ጌዲዮን በተሰማሩበት በፍትህ ዘርፍ በጣም ውጤታማ አመራር መሆናቸውን በተጨባጭ ገምግመናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የመንግሥት ተጠሪው አክለውም “ዶ/ር ጌዲዮን ጠንካራ ብቃት ያላቸው ሪፎርሚስት አመራር ናቸው፤ ስለሆነም አሁን በተመደቡበትም ቦታ በብቃት ኢትዮጵያን እና ሕዝቡን ማገልገል ይችላሉ” ብለዋል።
ከሥነ ሥርዓት እና ሂደት ጋር በተያያዘ ለቀረበው ጥያቄም ዶ/ር ተስፋዬ “አመራሮችን በተመለከተ በተመደቡበት ጊዜ ክረምት መግቢያ ላይ እና ምክር ቤቱ ወደ ምርጫ ክልል የተሰማራበት ጊዜ ስለነበር ነው። ከመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በኋላ እጅግ በርካታ የምክር ቤት አባላት ሥልጠና ላይ ነበሩ” ሲሉ መልሰዋል።
የመንግሥት ተጠሪው አክለውም “ሚኒስትሮች የተሾሙበት ቦታ ላይ የአመራር ክፍተት ኖሮ ማሳደር ከአገር እና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር አስፈላጊ እንዳልሆነ ከታየ በኋላ፤ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እና አመራሮች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመነጋጋር እና በመወያየት የተሠራ ነው” ብለዋል።