
ከ 2 ሰአት በፊት
በወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች በመምህርነት እንዳይሰማሩ የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
“የአጠቃላይ የትምህርት አዋጅ” በሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥቅምት 19፤ 2017 ዓ.ም. የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ በመምህርነት ሥራ ተሰማርቶ የወሲባዊ ጥቃት ወንጀል መፈጸሙ የተረጋገጠበትን ሰውንም በመምህርነት ሥራ እንዳይሰማራ ይከለክላል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው ይህ አዋጅ በወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሰዎች የግል ትምህርት ቤት እንዳያቋቁሙም ይከለክላል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎች እንዲማሩ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ይደነግጋል።
በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ስለሚደረግ ምደባ በሚደነገግገው የረቂቅ አዋጁ ክፍል ወሲባዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ወንጀሎች መፈጸሙ ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑ የተረጋገጠበት ሰው በማንኛውም የአጠቃላይ ትምህርት ተቋም ውስጥ መምህር ሆኖ መቀጠርን ይከለክላል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ የግል ትምህርት ቤት ለማቋቋም ስለመከልከል በሚያትትበት ክፍል ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም ፍቃድ የሚጠይቀው አመልካች አሊያም ተደራጅተው ከሚያመለክቱ ግለሰቦች መካከል አንዱ በወሲባዊ ጥቃት ወይም በሕፃናት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ የተወሰነበት ከሆነ እንደሚከለከል አስፍሯል።
የአጠቃላይ የትምህርት አዋጅ ማክሰኞ ጥቅምት 19፤ 2017 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
በአዋጁ መግብያ ላይ የአጠቃላይ የትምህርት አዋጅ ያስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል የትምህርትን ጥራት፣ አግባብነትና ፍትሐዊነት በተለይም የትምህርት ደረጃን የማውጣት ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
- በጉራጌ ዞን “ከፋኖ ጋር በተያያዘ” ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተነገረከ 8 ሰአት በፊት
- በነቀምቴ ከተማ ሁለት ታዳጊ ሴቶችን በቡድን የደፈሩ ወጣቶች እየተፈለጉ መሆኑን ፖሊስ ገለጸከ 4 ሰአት በፊት
- ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት “ብቁ አይደሉም” የሚል ትችት ቀረበባቸውከ 3 ሰአት በፊት
በ16 ክፍሎች እና በ97 አንቀጾች የተከፋፈለው ይህ ረቂቅ አዋጅ በማንኛውም የመንግሥት አጠቃላይ የትምህርት ተቋም በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ከሚካፈል ተማሪ፣ ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳሪዎቹ የትምህርት ክፍያ፣ የመማሪያ መጻሕፍት ዋጋ ወይም የመመዝገቢያ ክፍያ መቀበል የተከለከለ መሆኑንም ደንግጓል።
ከዚሁ አንቀጽ በመቀጠል ክልሎች በሚያወጡት ሕግ መሰረት ለሌሎች የትምህርት መሣሪያዎች የሚውል መጠነኛ ክፍያ ከተማሪ ወላጆች የመክፈል አቅም ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ አስፍሯል።
ነገር ግን ይህን ያላሟሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲለዩ ማድረግ እንደማይቻል ተቀምጧል።
ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎች ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎች እንዲማሩ ይደረጋል ያለው ይህ ረቂቅ አዋጅ እንግሊዝኛ ቋንቋ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እንደሚሰጥ ይገልጻል።
አክሎም አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪ ወይም የወላጅ ምርጫን ታሳቢ በማድረግ በየደረጃ ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ እንደ አንድ ትምህርት ዓይነት ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 10ኛ ክፍል የሚሰጥ ይሆናል ሲል አስፍሯል።
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን አንድ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ ክልሉ በሚመርጠው መሠረት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በአማራጭነት እንዲሰጥ ይደረጋል ሲል ይደነግጋል።