October 29, 2024 – Konjit Sitotaw
‹‹ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ብቁ አይደሉም›› ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
‹‹ዶ/ር ጌዲዮንን በጥቅሉ ብቁ አይደሉም ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይደለም›› ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ
በዛሬው እለት ሹመታቸው የጸደቀው የ5 ሚኒስትሮች የሹመት ሂደት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ዘንድ ቅሬታን አስነስቷል፡፡
የአካሄድ፤የስነስርአትና መሰል ህጋዊ አካሄዶች ተጥሰዋል በሚል በአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ከተነሱ ቅሬታዎች ባላፈ የተሿሚዎች የግል አቅምን በማንሳት ተቋውሞ የቀረበበት ነበር፡፡
የአብን አባልና የፓርላማ እንደራሴ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስን በማንሳት ለቦታው ብቁ አይደሉም ሲሉ ሞግተዋል፡፡
ተቋማዊ ገለልተኝነትን አስጠብቆ ከመጓዝ አንጻር በፍትህ ሚኒስትር የሰሩት ስራ ጥያቄ የነበረበት ነበር ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ አሁንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተሹመው ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አላስብም ብለዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ እንዴት አዲስ የካቢኔ ሹመት ማግኘት አለባቸው የሚለው ሂደትም ተገቢ ግምገማ ሳይከናወንበት የተደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
የመንግስት ተጠሪ ሚንስትር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በተሸሙት ዶ/ር ጌዲዮን ላይ የተሰነዘረው አስተያየት ጥቅል ፍረጃ ያለበትና ተገቢው ምርመራ ያልተከናወነበት ነው ሲሉ ተከላክለዋል፡፡
ተሿሚን ብቁ አይደሉም በሚል የተሰጠው ጥቅል ፍረጃም ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ ነው ለማለት ይከብደኛል ሲሉም በዶ/ር ደሻለኝ ጫኔ የቀረበውን ቅሬታ አጣጥለውታል፡፡