October 29, 2024 

“ሲዳማ፣ አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ጾታን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው”-ጥናት

በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (ኢ.ሴ.ማ.ቅ) አማካኝነት በመላው ኢትዮጵያ ከ36,000 በላይ ቤተሰቦች ላይ ለ 22 ወራት የተካሄደ ጥናት ይፋ ተደርጓል።

የሴቶችን ሁኔታ እና ፍላጎት በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በፆታ እና በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት፣ ስነ-ልቦናዊ ጤና፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ ሰላም እና ደህንነት፣ እንዲሁም ፍትህ ማግኘት ላይ መረጃ ለመሰብሰብ እና ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆን ለማስቻል ታቅዶ የተሰራው የጥናቱ ውጤት በትላንትናው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

ለጥናቱ ከ 12 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከ 36,330 በላይ ቤተሰቦች መረጃ መሰብሰቡን ተነግሯል።

ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ አንድ ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ከ ኦክስ ፋም ኢትዮጵያ (Oxfam Ethiopia) እንዲሁም ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ጥናቱ የተካሄደው።

የጥናቱ ውጤት ምን ሆነ?

የሴቶች የትምህርት ተደራሽነት

በኢትዮጵያ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሴቶች ቁጥር 55.1 በመቶ ሲሆን ይህም ከሌሎች ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው ተብሏል።

እንደ ምሳሌ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካን የጠቀሰው ጥናቱ ከ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ መሆናቸውን በንጽጽር አቅርቧል።

ማንበብ እና መጻፍ ከሚችሉት ሴቶች ውስጥ 76.3 በመቶዎቹ እድሜያቸው ከ15-29 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሲሆን እድሜያቸው ከ 50 በላይ ከሆኑ ሴቶች ውስጥ ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉት 17.1 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።

ዲጂታል መሳሪያዎችን በመጠቀም ረገድ ሲታይ ኮምፒውተር መጠቀም የሚችሉ ሴቶች 15 በመቶ ብቻ ሲሆኑ 21.8 በመቶ ሴቶች ኢንተርኔት መጠቀም እንደሚችሉ ጥናቱ አሳይቷል።

53.8 በመቶ በጥናቱ የተካተቱ ሴቶች የሞባይል ስልክ ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል።

45.3 በመቶ ሴቶች የሚፈልጉት የትምህርት ደረጃ እንዳይደርሱ የቤተሰብ ድጋፍ እጦት እና የገንዘብ እጥረት እንቅፋት ሆኖባቸዋል ተብሏል።

የቤተሰን ምጣኔን በሚመለከት

መረጃው 60.7 በመቶ ሴቶች አንዳንድ የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ያሳያል።

የደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሽፋን 80.4 በመቶ ሲሆን በአዲስ አበባ 73.5 በመቶ በመያዝ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

የሶማሌ ክልል በአንጻሩ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሽፋን 20.5 በመቶ ብቻ በመያዝ ዝቀተኛው ሆኗል።

የዳሰሳ ጥናቱ ከ 15-49 ዓመት የ እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች አገልግሎት ላይ ስለሚውሉ የንፅህና መጠበቂያዎች አካቷል።

ውጤቱም እንደሚያሳየው 57.7 በመቶ ሴቶች የሚጣሉ የንጽሕና መጠበቂያዎችን (ሞዴሶችን) ሲጠቀሙ 9.3 በመቶዎቹ ሴቶች ደግሞ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ የንጽሕና መጠበቂያዎችን ይጠቀማሉ ብሏል።

29.2 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ግን በቤት ውስጥ የሚሰሩ የንጽሕና መጠበቂያዎችን ይጠቀማሉ።

የሚጣሉ የንፅህና መጠበቂያዎችን ከማይጠቀሙባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥም የተደራሽነት ማነስ፣ ተመጣጣኝ ዋጋ አለመኖር እና የግንዛቤ ማነስ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።

በጾታ እና በጾታ ላይ ከተመሰረተ ጥቃት አንጻር

ከዳሰሳ ጥናቱ በፊት ባሉት 12 ወራት ውስጥ:-

° 20.2 በመቶ ሴቶች ሁሉም ዓይነት ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች።

° 9.3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች አካላዊ ጥቃቶች።

° 6 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች አንድ ወይም ከዚያ በላይ ወሲባዊ ጥቃቶች ደርሰውባቸዋል።

ሲዳማ፣ አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ጾታን መሰረት ባደረገ ጥቃቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

በጥናቱ መሰረት አካላዊ ጥቃት ፈጻሚዎች የቅርብ አጋሮች ወይም ባሎች ናቸው።

ጥናቱ እንዳመለከተው 14 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ጥቃት ካጋጠማቸው በኋላ እርዳታ ለመጠየቅ የሞከሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ ማለትም 55.2 በመቶዎቹ ጥረታቸው ምንም ውጤት አለማምጣቱን ተናግረዋል።

በጥናቱ ከተካተቱት ሴቶች ውስጥ በአጠቃላይ 81.0 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ስለ ሴት ልጅ ግርዛት ሰምተው እንደሚያውቁ የተናገሩ ሲሆን 48.5 በመቶዎቹ ደግሞ መገረዛቸውን ተናግረዋል።

የሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛውን የሴት ልጅ ግርዛት ስርጭት ያሳያሉ።

ከፖለቲካ እና ህዝባዊ ተሳትፎ አንጻር

ሴቶች ስለህጎች እና ፖሊሲዎች ያላቸውን ግንዛቤ በተመለከተ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ከፍተኛውን የግንዛቤ ደረጃ ያገኘ ሲሆን 52.4 በመቶ ምላሽ ሰጪዎች በውስጡ የተካተቱ አንዳንድ መብቶችን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ ግኝት የሚያመላክተው ግማሽ ያህል ሴቶች ስለሕጎች ግንዛቤ እንዳላቸው ነው።

ጥናቱ እንዳመለከተው

° 84.1 በመቶ ሴቶች የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ስም

° 35.8 በመቶ የፕሬዚዳንቱን ስም

° 44.5 በመቶ የገዥውን ፓርቲ ስም ያውቃሉ።

■ ከፖለቲካ አመለካከት አንፃር 53.1 በመቶ ሴቶች ወንዶች የተሻሉ መሪዎች ናቸው የሚለውን አመለካከት የሚቃወሙ ሲሆን 34.4 በመቶ ሴቶች ወንዶች የተሻሉ መሪዎች መሆናቸውን ይምናሉ።

እንዲሁም 67.2 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ለሃገራዊ መሪነት ሴት ብትመረጥ ጠቃሚ ነው ብለው ያምናሉ ተብሏል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው 77.1 በመቶ ሴቶች በሚቀጥለው ምርጫ  ድምጽ ለመስጠት ያቀዱ ሲሆን 71.6 በመቶዎቹ ደግሞ ባለፈው ምርጫ መመዝገባቸውን እና መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

በ 240 ገጾች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የቀረበው ጥናቱ በአራት ቋንቋዎች እየተዘጋጅ መሆኑም ተገልጿል።

ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ሰሜን እና ምዕራብ የትግራይ አካባቢዎች ፣ወለጋ (ምዕራብ ፣ምስራቅ ፣ቄለም እና ሆሮ ጉዱሩ) አካባቢዎች ፣አማራ ክልል የደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ጎጃም አካባቢዎች በጥናቱ አለመካተታቸው ተገልጿል።