October 29, 2024

‹‹የመምህራን ችግር ሳይፈታ የትምህርት ጥራት ይመጣል ተብሎ አይጠበቅም›› ዶ/ር አበባው ደሳለው

የመምህራን አቅም ሳያድግ የትምህርት ጥራት ለማምጣት የሚሰራው ስራ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል የገለጹት የአብን አባልና የፓርላማ እንደራሴ የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው ናቸው፡፡

እንደራሴው ይህን ያሉት የአጠቃላይ የትምህርት አዋጅን መርምሮ ለቋሚ ኮሚቴ ለመላክ በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡

የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ ሳይስተካከል፤ደሞዝ ክፈሉኝ ያለ መምህር እየታሰረ እንዲሁም አጠቃላይ የትምህረት ግብአቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ አዋጅ ማሻሻል ጥቅሙ እንብዛም ነው ያሉት ዶ/ር ደሳለው አዲስ የሚጸድቀው አዋጅ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይገባዋል ብለዋል፡፡

አዋጁ በጸጥታ ችግር ምክንያት በትምህርት ገበታቸው ያልተገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ ረገድም ጉልህ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ በማንሳትም አሁን ላይ አዋጁ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ከመላኩ በፊት ዳግም ሊጠና ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱት ሀሳቦች መካከል የንግድ እና የመጠጥ ቤቶች በትምህር ተቋማት አካባቢ ላይ መበራከት እና የተማሪዎች አለባበስ እና የወላጅ ክትትልን በተመለከተ የሚያነሳው አዋጅ መታየት እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የስራ እድል ሁኔታ ተማሪዎችን ለትምህርት ሊያነሳሳ የሚችል ነው የሚለውን መገምገም እና የየክልሉን የሰላም ሁኔታ ዘላቂ መፍትሄ የመፍጠር አቅጣጫ ሊቀመጥ እንደሚገባ በአባላቱ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰጥ ትምህርት ገደብ እንዳይደረግበት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጎን ለጎን መሰጠት እንደሚገባም ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል ተብሏል፡፡