ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ጫንጮ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ልዩ ስሙ ቆሬ ሮባ በተባለ ቦታ ትናንት ምሽት ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ሠራተኞቹን አፍነው መወሰዳቸውን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።
በታጣቂዎች የታገቱት ሠራተኞች በአዲስ አበባ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ መኾናቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
ተሽከርካሪው ጥቃት የተፈጸመበት፣ ገሚሶቹን ሠራተኞች ሱሉልታ ከተማ ላይ ካወረደ በኋላ የቀሩትን ጫንጮ ለማድረስ በጉዞ ላይ ሳለ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቆሬ ሮባ፣ ካሁን ቀደምም ታጣቂዎች የእገታ ወንጀል ሲፈጽሙባት እንደቆዩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።