ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ

ከ 9 ሰአት በፊት

ከሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ አሊ መሐመድ አደን የተባሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ከአገሯ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።

በኢትዮጵያ ኤምባሲ በአማካሪነት እያገለገሉ ያሉት አሊ መሐመድ አደን “ከዲፕሎማሲ ሚናቸው ጋር በማይሄዱ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ነው” ሲል የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በሞቃዲሾ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት አሊ መሐመድ አዳን ይህ ማስታወቂያ በደረሳቸው በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸዋል።

የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ አሊ ከዲፕሎማሲ ተልዕኳቸው ውጪ ስለተሳተፉበት ተግባር ዝርዝር ባይሰጥም ድርጊታቸው “በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተደረሰውን የቪየና ስምምነትን የሚጥስ ነው” ብሏል።

ሚኒስቴሩ በቪየና የተደነገገውን ዲፕሎማቶች የሚሰማሩባቸውን አገራት ሕግ እንዲያከብሩ እና በውስጥ ጉዳዮች ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚደነግጉ አንቀጾችን ጥሰዋል ሲል ከሷቸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማቱ መባረር ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

ሶማሊያ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ተቀማጭ የነበሩትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሐመድ ዋሬ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ ይታወሳል።

የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ወሰድኩት ባለችው እርምጃ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር ከማባረር በተጨማሪ አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን ጠርታለች።

በ72 ሰዓታት ከሶማሊያ እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው አሊ መሐመድ አደን
የምስሉ መግለጫ,በ72 ሰዓታት ከሶማሊያ እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው አሊ መሐመድ አደን

በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ እንዲሁም በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በአንድ ሳምንት እንዲዘጉ በወቅቱ የሶማሊያ ምክር ቤት ውሳኔ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ፣ ሐርጌሳ የሚገኘውን የቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማሳደጓን የሶማሊላንድ የመረጃ፣ የባህል እና የብሔራዊ መመሪያ ሚኒስትር አሊ ሐሰን መሐመድ (አሊ ማርሃን) ከጥቂት ወራት በፊት ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ሶማሊላንድ ነጻነቷን በማወጅ እንደ አገር የተመሠረተችበትን ዕለት ግንቦት 10/2016 ዓ.ም. 33ኛ ዓመት ስታከብር ሐርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸውን በሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎ እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “የኢትዮጵያን ጥሰቶች በማውገዝ ከሶማሊያ ጎን እንዲቆም” በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ “የባሕር በር መዳረሻን ሽፋን በማድረግ የሶማሊያን ግዛቶች ለመጠቅለል እየሞከረች ነው” ሲሉም ከሰዋል።

በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሶማሊያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት ውድቅ አድርገው “የኢትዮጵያ ስም ከየትኛውም ውንጀላ ጋር በፍጹም ሊያያዝ አይችልም” ብለው ነበር።

በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ የመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ እንዲሁም በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረቶች ነግሰዋል።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩ እየተገለጸ በሚገኝበት ወቅት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሶማሊያ እና ከግብፅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ነው።

በቅርቡም የግብፅ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንቶች በአሥመራ ከተማ የጋራ የሦስትዮሽ ጉባዔ በማድረግ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር እየተወዛገበች ያለችው ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል።

ግብፅ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት ዙር በአውሮፓላን እና በመርከብ የተጫኑ የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካረዋል።

የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።

የሶማሊያ መንግሥትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።