የማነ ብርሃኑ

October 30, 2024

በወላይታ ሶዶ ከተማ የተገነባው የዱቄትና የዳቦ ፋብሪካ

በወላይታ ሶዶ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የዱቄትና የዳቦ ፋብሪካ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ፣ ምርቱን ለከተማው ማኅበረሰብ እያቀረበ አለመሆኑን ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ በከተማዋ የተገነባው ፋብሪካ የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ካቆመ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ፋብሪካው ከተመረቀ በኋላ ለተወሰኑ ወራት ብቻ ዳቦ ለነዋሪዎች ማቅረቡን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ በፋብሪካው መቋቋም በአካባቢው የሚታየውን የዳቦ ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንደታሰበው አይደለም ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚገልጹት፣ ፋብሪካው ከተመረቀ ጊዜ ጀምሮ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ ነው ለማለት ይቸግራል። ፋብሪካው እንደ አሁኑ የማምረት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ከማቆሙ በፊትም ቢሆን ወጥ የሆነ ዳቦ ምርት አለማቅረቡን አክለው ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የዳቦና የዱቄት ምርቱን ለነዋሪዎች ማቅረብ ያልቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲጠይቁ፣ አንዴ የማሽን መበላሸት በሌላ ወቅት ደግሞ የአቅርቦት ችግር በማጋጠሙ የሚል ምላሽ ከሥራ ኃላፊዎች እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

በፋብሪካው የሚመረተውን ዳቦ ለማከፋፈል በከተማው በሰባት ቀበሌዎች መደብሮች ቢከፈቱም፣ አንዳቸውም አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል።

የሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ቶማስ ገብረየሱስ ፋብሪካው የዳቦና ዱቄት ምርቶችን ለከተማው ማኅበረሰብ ለማቅረብ ታቅዶ መገንባቱን፣ ሆኖም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በፋብሪካው በተከሰተ የማኔጅመንት ችግር ምክንያት የማምረት ሥራው ተቋርጧል ብለዋል፡፡

ፋብሪካው ከተቋቋመ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተብሎ የሚቀርበው አቤቱታ ትክክል አለመሆኑን፣ ፋብሪካው በከተማው ውስጥ በሚገኙ ሰባት ቀበሌዎች ባሉት የማከፋፈያ መደብሮች ለነዋሪዎች ዳቦ ሲያቀርብ መቆየቱን አስረድተዋል።

የስንዴ አቅርቦት ችግርም ሆነ የማሽን ብልሽት አጋጥሞ ፋብሪካው ሥራ ያቆመበት ጊዜ የለም ያሉት አቶ ቶማስ፣ በማኔጅመንት ችግር ለጥቂት ወራት ሥራ በማቆሙ እንደገና ለማስጀመር ስለሚቻልበት ሁኔታ አዲሱ የከተማ አስተዳደር ካቢኔ በጀት መድቦና ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለኅብረተሰቡ የዳቦና የዱቄት ምርት ማቅረብ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።

በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አማካይነት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተገነባው የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ታኅሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የተመረቀ ሲሆን፣ በቀን ሦስት ሺሕ ዳቦና 420 ኩንታል ዱቄት ያመርታል ተብሎ ነበር፡፡