

October 30, 2024
ኦርቢስ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ በዓይን ጤና ላይ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1982 በአሜሪካ ኒውዮርክ የተመሠረተው ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው የተወሰኑ የዓይን ሕክምና እና የአቪዬሽን ሠራተኞችን በመያዝ፣ በትንሽ አውሮፕላን ወደ ፓናማ ላቲን አሜሪካ የመጀመሪያውን በረራ በማድረግ ነበር፡፡ ዓለማየሁ ሲሳይ (ዶ/ር) የዓይን ሐኪም፣ የማኅበረሰብ ጤና ኤክስፐርትና የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በዓይን ጤና ዙሪያ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ወደ ሥራ በገባበት ጊዜ የዓይን ጤና ችግሮችን እንዴት አገኛቸው?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- በወቅቱ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የዓይን ጤና ትረኩት እንዳላገኘ ግልጽ መረጃ ተገኘ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱ ጥራቱን ያልጠበቀ እንደነበር፣ ብዙ የዓይን ጤና ባለሙያዎች መሠልጠን እንደሚገባቸው፣ ሥርዓቱ መጠናከር እንዳለበትና ሀብት ማሰባሰብም እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ መረጃዎች ተገኙ፡፡ በሥራ ላይ የነበረው አውሮፕላን በትልቅ ተተክቶ ሥራው በስፋት ቀጠለ፡፡ የትልቁ አውሮፕላን መምጣት የዓይን ሕክምናው ከአገር አገር እየተዞረ እንደሚሰጥ ወይም በራሪ የዓይን ሆስፒታል እንዲሆን አስችሏል፡፡ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ብቸኛው በራሪ የዓይን ሆስፒታል የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ፍላይንግ ዓይን ሆስፒታል ነው፡፡ ድርጅቱ በተዘዋወረባቸው አገሮች ሁሉ የዓይን ጤና ገዳይ ስላልሆነ የሚገባውን ትኩረት እንዳላገኘ ተገንዝቧል፡፡ ይህም የዓይን ጤና በልማት አጋሮች የሚታገዝ የጤና ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ ለምሳሌ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ከፍተኛ የጤና ችግሮች ምንድን ናቸው ከተባለ ገዳይና ተላላፊ በሽታዎች ናቸው፡፡ እነሱም ኤችአይቪ፣ ወባ፣ ቲቢና የመሳሰሉት ገዳይ የማኅበረሰብ ጤና ችግሮች ናቸው፡፡ የዓይን ጤና ስለማይገድል ትኩረት አላገኘም፡፡ ከዚህ አኳያ የዓይን ጤና በመንግሥታት ትኩረት እንዲያገኝ በአውሮፕላኑ የሚሰጠው ሕክምና ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ሚናውንም ሊጫወት የቻለው ከአገር ወደ አገር በበረረ ቁጥር ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ላይ የመውጣት ዕድል ስላጋጠማቸው የዓይን ጤና ትኩረት የሚሻ መሆኑን ለመገንዘብ ችለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በራሪ የዓይን ሆስፒታሉ በውስጡ የያዛቸውን መገልገያ መሣሪያዎችና የዓይን ጤና ባለሙያዎችን በተመለከተ ቢያብራሩልን?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- አውሮፕላኑ በውስጡ ዘመኑን የዋጁና በጣም ውድ የሆኑ ልዩ ልዩ የዓይን ሕክምና መሣሪያዎችን አካቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተውጣጡና በሙያቸውና በክህሎታቸው አንቱ የተባሉ የዓይን ሐኪሞችን ይይዛል፡፡ ሐኪሞቹ በጎ ፈቃደኞችና ለሳምንታት ያህል አውሮፕላኑ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ ለስንት ጊዜ መጥቷል? ማን ጎበኘው?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- አውሮፕላኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዓመታት አምስት ጊዜ መጥቷል፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ሆነው አውሮፕላኑ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ወቅት በአውሮፕላኑ ውስጥ የሚሰጠውን የዓይን ሕክምና ተመልክተዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የዓይን ጤና በምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ሕክምናው በሰው ኃይል፣ በመሣሪያና በግብዓት አቅርቦት ምን እንደሚመስል እንዲረዱ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ ውይይትና ትልቅ የጉትጎታ ሥራ እንደሚያስፈልገውም ለመገንዘብ ችለዋል፡፡ በተለይም በውሳኔ ሰጪ አካላትና በፖለቲከኞች ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያውያን የዓይን ሐኪሞች ምን ዓይነት የሙያ ልምድ ቀስመዋል?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- ወደ ልምዱ ከመግባቴ በፊት አንድ ነገር አስረግጬ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የዓይን ጤና በተፈጥሮ መሣሪያ ያስፈልገዋል፡፡ የዓይን ጤና ከተባለ ያለ መሣሪያ የሚሠራ ነገር የለም፡፡ ዓይን ትንሽ ኦርጋን ናት፡፡ የውስጧን ክፍል እያንዳንዱን አብጠርጥሮ ለማየት ልዩ ልዩ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በዓለም ላይ በዓይን ጤና አሉ የተባሉ መሣሪያዎች አውሮፕላኑ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በተረፈ አውሮፕላኑ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ቁጥር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች ወረፋ አስይዘው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያኑ ሐኪሞች አውሮፕላኑ ውስጥ ካሉት ሐኪሞች ጋር እየተጋገዙ ሕክምና ይሰጣሉ፡፡ ይህም ሁኔታ ለኢትዮጵያውያኑ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ምቹ መንገድ ይፈጥርላቸዋል፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ ካሉት መሣሪያዎች መካከልም አንዳንዶቹን በዕርዳታ የማግኘት አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አውሮፕላኑ የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ የአድቮኬሲና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ አውሮፕላኑ በየአገሩ በመብረር ብቻ የዓይን ጤናን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ማስኬድ ይቻላል ብሎ ያምናል? ወይስ ሌላ የተሻለና ቋሚ የሆነ አማራጭ አመቻችቷል?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- የዓይን ጤናን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለማራመድ ከተፈለገ ካንትሪ ፕሮግራሞች፣ ካንትሪ ኦፊሶች መከፈት አለባቸው ከሚል ስምምነት ላይ በመድረሱ ከአውሮፕላኑ ቀጥሎ እ.ኤ.አ. በ1998 የኢትዮጵያ ኦፊስ የመጀመሪያው ካንትሪ ኦፊስ ሆኖ ተከፈተ፡፡ ከዚያ በኋላ በሕንድ፣ በባንግላዴሽ፣ በቻይና፣ በሞንጎሊያ፣ በዛምቢያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጋናና በላቲን አሜሪካ ያሉት የኦርቢስ ካንትሪ ኦፊሶች ተከፈቱ፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ካንትሪ ኦፊስም ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የዓይን ጤና እክሎችን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ካንትሪ ኦፊስ ከተቋቋመም ዘንድሮ 26ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡
ሪፖርተር፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል በአውሮፕላን እየታገዘ በመላው ዓለም በዓይን ጤና ዙሪያ ካበረከተው አገልግሎት ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአውሮፕላኑ ውጪ ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎችን ቢያብራሩልን?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- ከአውሮፕላኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሳይበር ሳይት የሚባል የቴክኖሎጂ ቱል አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የሚንቀሳቀሱ የዓይን ጤና ባለሙያዎች በቀላሉ መረጃ የሚያገኙበት ፕላትፎርም ነው፡፡ ፕላትፎርሙ ፈቃደኛ የሆኑ የዓይን ጤና ባለሙያዎች በዓይን ጤና ዙሪያ ዓለም የደረሰበትን ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ በዓለም ላይ ሳይበር ሳይትን ከ100 በላይ አገሮች ይጠቀሙበታል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የዓይን ሕሙማኑን ጤና ችግር ባይታወቅና ችግሩ ከባድ መሆኑ በሐኪሞች ወይም በማኔጅመንት ከረተጋገጠ የታማሚውን መረጃ፣ ፎቶግራፍና ስለታማሚው ታሪክ ጽፈው ሳይበር ሳይቱ ላይ በመጫን አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ ካሉና በዓይን በሽታ ዕውቀትና ልምድ ካካበቱ ሐኪሞች መካከል ከአንዱ ጋር ለመመካከር ይችላሉ፡፡ በዚህም የሕመምተኛው ትክክለኛ ችግር ይገኛል፡፡ ለሕክምናውም ምክክር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በርቀትም ቢሆን ክህሎት ለማስተላለፍ ቁልፍ ሚና አለው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ለዓይን ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ተከታታይ ፊሎውሽፕ ይሰጣል፡፡ ሆስፒታልን መሠረት ያደረጉ አጫጭር ሥልጠናዎችም ይሰጣሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቢሮውን ሲያቋቁም እንደ ችግር የገጠመው ነገር አለ ወይ?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡-ችግሮች ገጥመውን ነበር፡፡ ከገጠሙንም ችግሮች አንዱና ቁልፍ የነበረው የዓይን ጤና መረጃ አለመኖር ነው፡፡ ቢኖርም ትንንሽ ጥናቶች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩን እንዴት ፈታችሁት?
ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ከትንንሽ ጥናቶች በመነሳት በጉራጌ ዞን የመጀመሪያውን የዳሰሳ ጥናት አካሄድን፡፡ በዚህም መሠረት የዓይን ማዝ፣ የዓይን ሞራና በመነፅር ሊስተካከል የሚችል ዝቅተኛ የዕይታ ችግሮች ግንባር ቀደም የዓይንን ሕመሞች ነበሩ፡፡ ከጥናቱም በመነሳት ኦርቢስ ኢንተርናሽናል የመጀመሪያውን ፕሮግራም በዞኑ ማከናወኑን ተያያዘው፡፡ ይህንንም እየሠራን ዝም አላልንም፡፡ በዓይን ጤና ዙሪያ ላይ እንደ አገር ጥናት ያስፈልገዋል የሚል ቅስቀሳ ማካሄድ ጀመርን፡፡ ይህንንም ያካሄድነው ብቻችንን ሳንሆን በዓይን ጤና ላይ ከሚሠሩ አጋር ድርጅቶች፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቅስቀሳው ምን ውጤት አስገኘ?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- ከቅስቀሳው በኋላ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዓይነ ሥውርነት፣ የዝቅተኛ ዕይታና የዓይን ማዝ በሽታዎች አገር አቀፍ ጥናት እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2006 አካሄደች፡፡ በጥናቱም ኢትዮጵያ 1.6 በመቶ ያህል ሕዝቧ ዓይነ ሥውርነት እንዳለበት ታወቀ፡፡ ይህም ማለት ከ100 ሰዎች ከአንድ ሰው በላይ ዓይነ ሥውር ነው፡፡ በተጨማሪም 3.7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ጤነኛ ያልሆነ፣ ያልተሟላና ሊስተካከል የሚገባው ዝቅተኛ ዕይታ አለው፡፡ ይህም ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረትም ዋና ዋና የዓይን ችግሮች ምንድናቸው? ከተባሉ አንደኛ የዓይን ሞራ በሽታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ በሽታ ለዓይነ ሥውርነት ግንባር ቀደም መንስዔ ነው፡፡ በብዛት ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ይመጣል፡፡ ሁለተኛው የዓይን ማዝ (ትራኮማ) ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ በመነጽር የሚስተካከል ዝቅተኛ ዕይታ ወይም ዓይነ ሥውርነትን የሚያመጣ ችግር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የዓይን ግፊት ሲጨምር የሚከሰት ግላኮማ አንዳንዴም በዕድሜ ምክንያት ወይም በእርጅና ጊዜ የሚከሰት የብርሃን መቀበያ ማርጀትና መዳከም ሌሎች ችግሮች ናቸው፡፡ የዓይን በሽታ በእርጅና የሚመጣ ነው ተብሎ ዝም አይባልም፡፡ ሕክምናዎች አሉት፡፡ ኦርቢስ አንተርናሽናል የተጠቀሱትን መረጃዎች መሠረት ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የዓይን ፕሮግራሞችን እንዲተገብር ጥናቱ ረድቶታል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥናቱን ስታካሂዱ በኢትዮጵያውያን የዓይን ሐኪሞች ቁጥር ምን ያህል ነበር?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ የዓይን ሐኪሞች ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005/2006 በነበረው መረጃ መሠረት 65 የዓይን ሐኪሞች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 75 ከመቶ ያህሉ የሚገኙት በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ 84 በመቶ ያህሉ ያለው ገጠር ነው፡፡ ስለዚህ በባለሙያውና ችግሩ ባለበት ኅብረተሰብ መካከል ከፍተኛ ክፍተት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሥልጠናዎችን ያከናወነው፡፡ ከዚህም ሌላ በጎንደር፣ በሐዋሳ፣ በጅማና ሌሎችም ከተሞች የዓይን የጤና ባለሙያዎች እንዲሠለጥኑ ግፊት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከ260 በላይ የዓይን ሐኪሞች አሏት፡፡ ምናልባት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህ ቁጥር አሁን ካለው ዕጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኦርቢስ ከሥልጠናዎቹ በዘለለ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ፕሮግራሞች ቀርፆ ሲሠራ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ፕሮግራም የተቀረፀው ገጠርን ማዕከል ያደረገ የዓይን ጤና ይባላል፡፡ በጉራጌ፣ በወላይታ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ ወዘተ በመከላከል ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ተከታታይ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ደግሞ የሠለጠኑ ነርሶችን የመጀመሪያውን የዓይን ሕክምና እንዲያደርጉ ማስቻል፣ ሌሎች ችግር ያለባቸውንና ከአቅም በላይ የሆነውን እያጣሩ ወደ ሚቀጥለው ጤና ተቋም እንዲልኩ የሚያስችል ሥልጠና ተከናውኗል፡፡
ሪፖርተር፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቢሮ ከተቋቋመበት ዓመት አንስቶ እስካሁን ድረስ በዓይን ጤና ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ቢገልጹልን?
ዓለማየሁ (ዶ/ር)፡- ቢሮው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ4,154,947 በላይ ለሆኑ ታካሚዎች የዓይን ጤና ምርመራና ልየታ፣ 25,574,496 ለሚሆኑ ሰዎች የሕክምናና የመነፅር ድጋፍ፣ 297,383 ለሚጠጉ ታካሚዎች የዓይን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ 1,389 ሰዎች የሳይበር ሳይት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በበራሪ የዓይን ሆስፒታል ውስጥ አምስት የሥልጠና ፕሮግራሞች ተከናውነዋል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የዓይን ሕክምና እንዲጀመርና የግላኮማ ክሊኒክ እንዲከፈት አድርገናል፡፡ የአክሎፕላስቲክ ክሊኒክ እንዲከፈት አድርገናል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች የመጀመሪያ የሆነውን የዓይን ብሌን ባንክ እንዲቋቋምም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡