በሩሲያ ካዛን የብሪክስ አባል አገሮች መሪዎች የታደሙበት ጉባዔ (ቪኦኤ)

ዓለም የብሪክስ ጡንቻ መፈርጠምና የጡቦቹ መበራከት

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: October 30, 2024

ባለፈው ሳምንት የዓለምን ትኩረት ከሳቡ ክስቶች፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት (እስራኤል በኢራን በተመረጡ ወታደራዊ ዒላማዎች ያደረገቻቸውን መብረቃዊ የበቀል ጥቃቶች ጨምሮ) እና ከአሜሪካው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ፉክክር በመከተል በሩሲያ የተካሄደው 16ኛው የብሪክስ አባል አገሮች የመሪዎች ጉባዔ ይገኝበታል፡፡

የብሪክስ ጡንቻ መፈርጠምና የጡቦቹ መበራከት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የብሪክስ አባል አገሮች በፋይናንስ ትብብርና አባላትን በመጨመር ዙሪያ መክረዋል (ዴይሊ ኒውስ
ኢጅፕት)

ይህ ከጥቅምት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በመካከለኛው ሩሲያ በምትገኘው ካዛን ከተማ የተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ፣ በአዲስ አባልነት የተካተቱ አገሮች መሪዎች የተካፈሉበትና ለአዲስ ገቢ አገሮቹም ይፋዊ የ‹‹እንኳን በደህና ተቀላቀላችሁ›› አቀባበል የተደረገበት ነበር፡፡ ከመሥራቾቹ ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ሩሲያና ደቡብ አፍሪካ በተጨማሪም፣ እ.ኤ.አ. በ2023/24 አርጀንቲና፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ኢራን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የደኅንነት ትብብር ማዕቀፍ የሆነውን በይነ መንግሥታት ድርጅት ተቀላቅለዋል፡፡

‹‹የሐሳብ አድማሳችን በፈቀደው መጠን የሉላዊውን (Global) ደቡብና ምሥራቅ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚኖራቸው ወሳኝነት እንዲረጋገጥ፣ ብሎም ዓለም ባለብዙ ዋልታ (Multi Polar) በሆነው ሥርዓት እንድታድር ጥረት እናደርጋለን፤›› ሲሉ ነበር፣ የአስተናጋጇ አገር ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፒቲን ለተሰብሳቢዎች የብሪክስ አባል አገሮችና ሌሎች መሪዎች ባደረጉት ታላቅ የራት ግብዣ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት፡፡ በካዛኑ የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በራስ ቅል ሕመም ምክንያት ሊገኙ ያልቻሉት የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ደ ሲልቫ ብቻ ሲሆኑ፣ የተጨመሩትን አባል አገሮችን ጨምሮ ሁሉም መሪዎች ታድመዋል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶዋንን ጨምሮ የሌሎች አባል ያልሆኑ፣ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ማዕቀፉን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ አገሮች መሪዎች ወይም ተወካዮቻቸው ጉባዔውን በተለያዩ ደረጃዎች ከታደሙት መካከል ይገኙበታል፡፡ የራት ግብዣው በኮንሰርት ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን፣ ታዋቂ በሆነ የሩሲያ ሲንፎኒ አባላት የአዲስ ገቢ አገሮችን ሙዚቃዎች በሙሉ ባንድ መድረክ ላይ ተጫውተዋል፡፡

ለመሆኑ ብሪክስ ምንድነው? ሊያሳካ የተነሳላቸው ዓላማዎች ምንድናቸው? የዓለምን ማኅበረሰብ ቀልብ በዚህ ደረጃ የመሳቡ ሚስጥርስ?

ብሪክስ እ.ኤ.አ. ጁን 16 ቀን 2009 ተመሠረተ፡፡ ለመጠሪያው የአራቱን መሥራች አገሮችና በኋላም ተከትላ የተቀላቀለችውን ደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝኛ ስማቸውን የመጀመሪያ ፊደላት ተጠቀመ፡፡ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት በዓለም ላይ ሁነኛ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ መውጣት እንደቻለ፣ ‹‹ካውንስል ኦን ፎሬይን ሪሌሽንስ›› የተባለ ድረ ገጽ አትቷል፡፡ ዓላማውን ሲገልጽም፣ ‹‹በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ለመገዳደር የሚያስችል ብቃት ለመፍጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ›› የተፈጠረ ኃይል እንደሆነ ጨምሮ ያወሳል፡፡ ከአንድ ዓመት ጀምሮ እየተስተዋለ የመጣው የቡድኑን ጡንቻ መስፋፋትና መፈርጠም አመላካች እንደሆነ ሲገልጽ፣ ሆኖም በቡድኑ አባል አገሮች መካከል እንደ ዩክሬን ጦርነት ባሉ ጉዳዮች አለመስማማት እንደነበር አስገንዝቧል፡፡

የሆነው ሆኖ በተለያዩ ስታትስቲካዊ ምዘናዎች ሲታይ ቡድኑ አሌ የማይባል ተፅዕኖ እንደሚኖረው አያጠያይቅም፡፡ ከዓለም ሕዝብ አጠቃላይ ቁጥር 45 በመቶ በአባል አገሮች የሚኖር ነው፡፡ ይህም ማለት 3.25 ቢሊዮን ሕዝብ በብሪክስ አገሮች ይኖራል፡፡ በዓለም የሕዝብ ብዛት አንደኛና ሁለተኛ የሆኑትን ህንድንና ቻይናን ጨምሮ፣ ከዓለም አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) 25.83 ትሪሊዮን ዶላር (የዩኤስ) የሚገኘውም በብሪክስ ቡድን አባል አገሮች ቢሆንም፣ በሀብት መጠን አገሮቹ በእጅጉ የሚበላልጡ ናቸው፣ እንደ ስታቲስታ (Statista) ድረ ገጽ መረጃ፡፡ አባል አገሮቹ ደግሞ በበርካታ አኅጉራት የሚገኙ ሲሆን እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አፍሪካንና ደቡብ አሜሪካን ያካትታል፡፡ እነዚህ አባል አገሮች በአጠቃላይ በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች (Emerging Economics) በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡

ዶላርን ማክተም

ይህ የብሪክስ ጥረት በእንግሊዝኛው ‹‹De-Dollarization›› የሚል ስም የወጣለት ሲሆን፣ ‹‹አገሮቹ በየራሳቸው ገንዘብ በመገበያየት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ90 በመቶ በላይ የአገሮች የወጪ ንግድ መገበያያ የሆነውን የአሜሪካ ዶላር በተቻለ ደረጃ ገሸሽ ማድረግን፣ እንደ አንድ ሥልት መጠቀም እንደሚኖርባቸው ያምናሉ፤›› ሲል ፋይናንሻል ኤክስፕረስ ዘግቧል፡፡ ይህ የቡድኑ ፍላጎት እ.ኤ.አ. በ2022 የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ላይ በቤጂንግ፣ እንዲሁም በ2023 በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ ላይ በተደረገው ተመሳሳይ ስብሰባ ወቅት የተንፀባረቀ ነበር፡፡ አሜሪካ መር የሆነው የምዕራቡ ዓለም በጣለባቸው የጉዞ ማዕቀብ (የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸዋል ምክንያት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጆሃንስበርጉ የመሪዎች ጉባዔ በአካል ከመገኘት ይልቅ፣ በዘመኑ የቴሌ ኮንፈረንስ ቻናል መካፈልን መርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በሩሲያ የካዛኑ የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የወጣው የጋራ መግለጫ እንደገለጸው፣ አባል አገሮቹ ድንበር ዘለል ለሆኑ ክፍያዎች የየአገራቸውን ገንዘብ በመጠቀም እንደሚገበያዩ በኦፊሺያል ውሳኔ ተላልፏል፡፡ እንደ ፋይናንሺያል ኤክስፕረስ ከሆነ ይህ ውሳኔ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ግብይቶች ላለባቸው ዶላርን የመመርኮዝ የውዴታ ግዴታ ለመቀነስ ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ የካዛኑ የጋራ መግለጫ፣ ‹‹በብሪክስ አገሮችና በንግድ አጋሮቻቸው መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች የየአገሮቹን መገበያያ ገንዘቦችን ተጠቅመው እንዲፈጽሙ እንጋብዛለን፤›› ይላል፡፡

በህንድ የሚታተመው ፋይናንሺያል ኤክስፕረስ ድረ ገጽ፣ እንዲሁም በርካታ ሌሎች የዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሒደቶች ተንታኞች እንደሚስማሙት የየአገሮችን መገበያያ ገንዘብ ለውጭ ንግድ ልውውጦች ክፍያ እንዲውሉ በማስቻል ረገድ ህንድ ቁልፉን ሚና ተጫውታለች፡፡ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በጉባዔው ወቅት እንደተናገሩት፣ ‹‹ይህ አዲስ ክስተት/አዝማሚያ በብሪክስ አገሮች መካከል የሚኖረውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠናክራል፣ ለንግድ ልውውጥ ደግሞ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ብቃት ያለው መሠረት ይጥላል››፡፡ በዓለም ላይ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋዜ ከሚታወቁ አገሮች የፊት ተርታ ተሠላፊ ለመሆን የበቃችው ህንድ፣ ከሩሲያና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ (UAE) ጋር በራሷ ገንዘብ ‹ሩፒ› መገበያየት ከጀመረች ውላ ያደረች ሲሆን፣ ከኢንዶኔዥያ ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት ለመመሥረት በንግግር ላይ እንደምትገኝ ተዘግቧል፡፡

የሩሲያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን በጉባዔው ላይ እንደገለጹት ደግሞ፣ የብሪክስ አባል አገሮች ከምንም ተነስተው ዶላርን የሚገፉ ሳይሆን፣ በዶላር የመገኘት ሁኔታ ላይ የቀጠለው ክልከላ ግን አማራጮች እንዲያፈላልጉ አስገድዷል፡፡ ‹‹በሉላዊው የፋይናንስ ሥርዓት ዶላር ግንባር ቀደም ጠቀሜታ ይዞ ቀጥሏል፡፡ ሆኖም ዶላርን የፖለቲካ መሣሪያ በማድረግ እንደ ዓለም አቀፍ መገበያያ የሚተማመኑበት ሆኖ አይቀጥልም፤›› ብለዋል ፑቲን፡፡ እንደ እሳቸው አባባል ብሪክስ ከዶላር በተፃፃሪ ትግል አይገጥምም፣ ሆኖም ዶላር የአገሮች መድፈሪያ ተደርጎ ሲቀጥል ግን ቡድኑ አማራጭ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡

የኒው ዴቭሎፕመንት ባንክ (ኤንዲቢ) ሊቀመንበር ዲልማ ሮሴፍ ይህንኑ የፑቲንን አቋም ያስተጋባሉ፡፡ ዶላር እንደ ፖለቲካ መሣሪያነት ውሏል፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ግንኙነቶች ተዓማኒነቱን እያጣ መጥቷል፡፡

የ16ኛው የብሪክስ አባል አገሮች ጉባዔ ባወጣው መግለጫ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የብሬተን ውድስ ተቋማት በመባል የሚታወቁት አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ አሁናዊ የዓለም ሁኔታዎችን በሚያንፀባርቅና አካታች በሆነ መልኩ የአደረጃጀትና አሠራር እድሳት እንደደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ መግለጫው አክሎም የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ተመሳሳይ መሻሻሎችን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዶላር ምንዛሪ ተለዋዋጭነትና መዋዠቆች፣ እንዲሁም የብሪክስና ሌሎች አዳጊ አገሮች ያላቸው የውጭ ምንዛሪ ክምችት አቅም ውስንነቶች፣ ብሪክስ አማራጭ የገንዘብ ዝውውርና ግብይት ዘዴዎችን እንዲያፈላልግ ከሚያስገድዱ ሁኔታዎች እንደሆኑ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የዓለምን 28 በመቶ የኢኮኖሚያዊ የምርት ውጤት ብሎም 47 በመቶ የዓለምን ድፍድፍ ነዳጅ ባለቤት የሆኑ አገሮች በአንድ በይነ መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ሲሰባሰቡ፣ የተቀረውን ዓለም አትኩሮት ላይስብ አይችልም፡፡ የቡድኑ መሥራቾችና ቀንደኛ ተዋንያን ቻይናና ሩሲያ የመሆናቸው ነገር ደግሞ ለምዕራባውያን ባይመርም መጎምዘዙ አይቀርም፡፡ ምዕራባውያን በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችና የፖለቲካና ዲፕሎማሲዊ ማግለል ላደረሱባት ሩሲያ ዓይነተኛ መድረክ ነው ሲሉ ይደመጣሉ ተንታኞች፡፡ ለቻይና ደግሞ የአሜሪካ መሩን የምዕራባውያን እጅግ የተለጠጡ ተፅዕኖዎች መገዳደሪያ፡፡

ትችቶች

ቡድኑን ደቡብ አፍሪካ ከመቀላቀሏ አስቀድሞ እ.ኤ.አ. በ2011 የጎልድማን ሳክስ ኢኮኖሚስት የሆነው ጂም ኦኔል ብሪክስ ሲል የጠራውና በጽሑፍ አንድ ፊደል ቢጎድለውም፣ ቃሉ በአፍ ሲጠራ ግን ‹‹ጡብ›› የሚለውን ትርጉም (Bricks) ስለሰጠው ነበር፡፡ ሪፖርቱም ‹‹ሉላዊ ኢኮኖሚያዊ ጥናታዊ ጽሐፉ ቁጥር 66›› በሚል የቀረበ ሲሆን፣ ለሪፖርቱ የተሰጠው ርዕስ በደምሳሳ ትርጉሙ ‹‹የተሻለ ኢኮኖሚዊ ጡቦችን መገንባት›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ታዋቂ ኢኮኖሚስት የቡድኑን ምሥረታ በማድነቅ እነዚህ ኢኮኖሚዎች እ.ኤ.አ. በ2050 የዓለምን ዕድገት ‹‹ይመራሉ፣ ይቆጣጠሩማል›› ብሎ ያምን ነበር፡፡ ሆኖም ጂም በስተኋላ በቡድኑ ላይ ትችቶች ከሚያቀርቡት ጎራ ተቀላቅሏል፡፡ በይፋ ከመመሥረቱ አስቀድሞ ጎልድማን ሳክስ ባለፀጎችን ከብሪክስ ኩባንያዎች የሚያገናኝ የኢንቨስትመንት ፈንድ አደራጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ግን እንዲከስም ተደርጓል፡፡ የብሪክስ አባል የራሳቸው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (NDB) በቤጂንግ አቋቁመዋል፡፡ የቀድሞው የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ የባንኩ ገዥ ናቸው፡፡

በቡድኑ ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች አንዱ ቡድኑ በጂኦ ፖሊካዊ መሥፈርት የተበታተነ መሠረት ላይ የተገነባ፣ አባላቱም የዓላማና የርዕዮተ ዓለም ውህደት የሌላቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ረዥም ርቀት አይዘልቅም የሚል ይገኝበታል፡፡  

ዳሮን አችሞግሉ ‹‹አገረ መንግሥታት ለምን ይጨነግፋሉ›› የተሰኘ በዓለም በሰፊው ተነባቢነትን ያተረፈ መጽሐፍ (ከጽሑፍ አጋሩ) ጋር ደራሲ ነው፡፡ ‹‹ዓለም ተጨማሪ አገሮች በቻይናና በሩሲያ ተፅዕኖ እንዲያርፉ ወይም ከዩናይትድ ስቴትስ በተፃራሪ ጎራ እንዲሠለፉ አይሻም፡፡ የሚያስፈልገው ሁለቱን ተፃራሪ ጉራዎች የሚያመዛዝን ሦስተኛ አማራጭ አሠላለፍ ነው፤›› ብሏል፡፡

የጋራ መገበያያ

እ.ኤ.አ. በ2023 የጆንሃንስበርግ ጉባዔ ወቅት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ብሪክስ የጋራ መገበያያ ገንዘብ እንዲኖረው አሳስበው ነበር፡፡ ጉዳዩ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለየዩ መድረኮች መከራከሪያ ከመሆን ባለፈ ወደ ተጨባጭ ዕርምጃነት የተሸጋገረበት ዕድል አላገኘም፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሴሪል ራማፎዛም እንደሚሉት በጉዳዩ ላይ የብሪክስ አባል አገሮች መሪዎች በይፋ የተወያዩበት መድረክ አልነበረም፡፡

ሆኖም በካዛኑ ጉባዔ ወቅት የላንቲካ/ትዕምርታዊ (Symbolic) ገንዘብ ምሥል ለተሰብሳቢዎች ተዋውቋል፡፡ ምሥሉ የብሪክስ ቀደምት አባል አገሮችን ሰንደቅ ዓላማዎች ያማክላል፡፡ ይህ ላንቲካ ገንዘብ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የተሠራጨ ሲሆን፣ አንዳንዶች የብሪክስ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ ይፋ እንደሆነ አስመስለው የሐሰት ዘግበዋል፡፡ የሐሰት ዘገባውን ተከትሎም አስተያየት ሰጪ ኢትዮጵያውያን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማስ የታለ?›› እና ሌሎች መሰል አስተያየቶች ጽፈዋል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት የብሪክስ አባል አገሮች በካዛን ያደረጉትን ጉባዔ ሲያጠናቅቁ ውሳኔ ካስተላለፉባቸው ቁምነገሮች አንዱ፣ አገሮች በራስ የመገበያያ ገንዘብ ክፍያዎች መስጠትና መቀበል አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚለው ይገኝበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሌሎች አባል አገሮች መንግሥታት እንደሚያደርጉት፣ የአገሪቱን የብሪክስ አባልነት ተጨባጭ ወደ ሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ለማምራት ይችል ዘንድ አስፈላጊ የፖለሲ፣ የአሠራርና የሕግ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉትና ሒደቶቹንም ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ማስፈን እንደሚጠበቅበት አያጠያይቅም፡፡

ኢትዮጵያ ትኩረት ልትሰጣቸው ከምትችላቸው መካከል የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ይዞ የመጣውን ዕድሎች በተገቢው መጠቀም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ባንኩ ስለከፈታቸው ዕድሎች ሲገልጽ የተቋቋውም፣ ‹‹… ለመሠረተ ልማቶች መስፋፋትና ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን በአዳጊ አገሮች ለማሳለጥ አስፈላጊ የሆኑ ገንዘብና ሌሎች ግብዓቶች ማቅረብ ነው፤›› ይላል፡፡

ባንኩ አክሎ እንደገለጸው፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለሁሉም እንዲዳረስና የአካባቢ ንፅህና አገልግሎቶች እንዲስፋፉ፣ የውኃ ሀብቶች ዘላቂና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲተዳደሩ፣ ብሎም ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ አደጋዎችን ለመከላል የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ትኩረት አድርጎ ይደግፋል፡፡

ባንኩ እነዚህን ተግባራት ለመደገፍ እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2026 የሚተገበርና መጪውን ጊዜ ዘላቂ ለማድረግ የልማት መዋዕለ ንዋይ ማሳደግ በሚል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይህ ከኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ጥያቄ አኳያ በእጅጉ የተጣጣመ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህም ከብሪክስ አገሮች ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር ጥረት ከማድረግ ባሻገር፣ ባንኩ በፈጠራቸው ዕድሎች ዙሪያ ሰፊ ሥራ መከናወን እንደሚገባው የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ባንኩ በመሥራች አገሮች የተቋቋመው በ100 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ነበር፡፡

በጉባኤው ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በጉተሬዝ መገኘት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወቃል፡፡