

ሕፃናት የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶችን አብዝተው ሲጠቀሙ ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይዳርጋቸዋል
ማኅበራዊ የልማድ ባርነት በሕፃናት
ቀን: October 30, 2024
በሱራፌል አሸብር
የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በየዘመኑ የዕውቀት አድማሱን እያሰፋ፣ የማወቅ ጉጉቱን እየጨመረ፣ ከዓመት ዓመት ችግሮቹን እየፈታና እያቃለለ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ታዲያ ጊዜው እየዘመነ በሄደ ቁጥር ወቅቱን መዋጀት በወቅቱም ልክ እራስን መስፋት ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም እዚህ ሊረሳ የማይገባው አንድ ነገር አለ፡፡ እሱም ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ጥንቃቄ ስለማድረግ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምድራችን የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶች ማለትም ቴሌቪዥን፣ ላፕቶፕ፣ ስልክ፣ ታብሌትና የመሳሰሉት በሕፃናት ልጆች ዘንድ በየቤቱ ሲዘወተሩ ይስተዋላል፡፡
ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ከሚሆኑባቸው ጊዜ ይልቅ ከስልካቸው ጋር የሚያጠፉት ሰዓትም እየጨመረ ስለመምጣቱ አንዳንድ ወላጆች ነግረውናል፡፡ ምግብ ቤት፣ መጽሐፍት ቤት፣ የመጓጓዣ ታክሲ ውስጥ ከስልክና መሰል ነገሮቻቸው ጋር የሚያወሩ፣ አንገታቸውን አቀርቅረው የሚነጋገሩ ሕፃናትን ሆነ አዋቂዎች ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ታዲያ የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶች ላይ ለረጅም ሰዓት አፍጥጠው የሚመለከቱ ልጆች ምን ያጋጥማቸው ይሆን?
ነፃነት መረተ ትባላለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ ስትሆን፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ናት፡፡ የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች እናት የሆነችው ነፃነት፣ ስለልጆቿ የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁስ (Digital Screen) አጠቃቀም ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ ልጆቿ ከእሷ ፈቃድ ውጪ ምንም ነገር አያደርጉም፡፡ ነገር ግን በአንድ ወቅት ስድስት ዓመት የሆናት ትንሿ ልጇ በስልክ ጌም መጫወት ለመደች፡፡ በመሆኑም ልጇ ስልኳ አጠገቧ ካልሆነ አንዳች ምግብ አትቀምስም ነበር፡፡
ምግብ እንድትበላ ሲነገራት ሆዷን እንዳመማትና እንቅልፏ እንደመጣ ትናገርም ነበር፡፡ ስልክ ሲሰጣት ደግሞ በደስታ ምግቧን አጠናቃ ትበላለች፡፡ ምግቧን በአግባቡ እንድትመገብ በማሰብ በዚህ ሁኔታ ዝም ተባለች፡፡ እናም ቀስ በቀስ ዓይኖቿ እየቀሉና እያመማት መጣ፡፡ ሆስፒታልም ለመሄድ እስከሚያደርሳት ድረስ ክፉኛ ታመመች፡፡ ያከማት ዶክተርም ልጇ ስልክ ባትጠቀም መልካም እንደሚሆን በመከራት መሠረት፣ ለልጇ ስልክ መስጠት እንዳቆመች ነፃነት ትገልጻለች፡፡
ከልምዷ በመነሳትም ልጆች የሚጠይቁትን ሁሉ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነም ትመክራለች፡፡
እንደ ነፃነት፣ ልጆች በበጋ ትምህርት ቤት በሚማሩበት ወቅት ከትምህርታቸው ጋር ምንም ነገር እንዳይጋጭ ተብሎ የትኛውም የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁስ እንዳይጠቀሙ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ክረምት የተማሪዎች የዕረፍት ወቅት ነውና ስልክና መሰል ነገሮች ያለገደብ ለልጆች ይፈቅዳሉ፡፡
ከሁለት ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ጠዋትና ማታ ስልክና መሰል ቁሶች ላይ ያሳልፋሉ፡፡ የበጋው የትምህርት ጊዜ ሲደርስም ከገጠማቸው የዓይን ሕመም በተጨማሪ በክረምት ከለመዱት ሱስ ለመላቀቅ ይቸገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት ያህል የልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራምን በማዘጋጀትና አሁንም የኢትዮጲስ ፕሮግራም በመምራት ላይ የምትገኘው ወ/ሮ አንድነት አማረ ከሪፖርተር ጋር በነበራት ቆይታ፣ እንደ ልጆች ፕሮግራም አዘጋጅነቷም ሆነ እንደ እናትነቷ፣ ልጆች የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁስ የሚባሉትን በየቤታቸው በብዛት እንደሚጠቀሙ መታዘብ መቻሏን ገልጻለች፡፡
በዚህም ምክንያት የማስታወስ ችሎታቸው እንደሚቀንስ፣ ከሰዎች ጋር የነበራቸው ማኅበራዊ መስተጋብር እንደሚላላ ይባስ ሲልም እንደሚጠፋ አክላለች፡፡
እንደ ወ/ሮ አንድነት፣ ወላጆች ከሥራ ወደ ቤት ሲገቡ ምንም እንኳን ቢደክማቸውም ጊዜያቸውን ለልጅ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
ልጆች ስልክን መሰል ቁሶች አብዝተው እንዳይጠቀሙም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች፣ የትምህርት ቤት መምህራን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ጎረቤት፣ የሕክምና ባለሙያዎች ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁማለች፡፡
‹‹ልጆች የሚነግሯቸውን ነገሮች በደምብ ያዳምጣሉ›› የምትለው ወ/ሮ አንድነት፣ ልጆች ወላጆቻቸውን እንደሚፈልጉ፣ ከወላጆቻቸው ጋር መጫወት፣ ጥያቄ መጠየቅና አብዝቶ ማወቅ እንደሚያጓጓቸው ወላጆች በመገንዘብ፣ ልጆቻቸው ዝም እንዲሉላቸው ብቻ ስልክ እንዳይሰጧቸው ትመክራለች፡፡
በብሩህ ቪዥን የዓይን ሕክምና ማዕከል የዓይን ስፔሻሊስትና የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዘላለም እሸቱ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕፃናት ልጆች የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶችን ሲጠቀሙ በተመጠነ ጊዜ መሆን አለበት፡፡ ወላጆችም ለዚህ ኃላፊነት በመውሰድ ለልጆች የሚጠቅሟቸውን ነገሮች ብቻ መርጦ በመስጠት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ዘላለም (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ ሕፃናት የዲጂታል መመልከቻ መሣሪያዎችን አብዝተው በሚመለከቱበት ጊዜ ለተለያየ በሽታ ይጋለጣሉ፡፡ ይህም ለዓይን መድከም (Digital Eyestrain)፣ ለዓይን መድረቅ (Ocular Surface Diseases)፣ ለአጭር ርቀት ብቻ የተገደበ ዕይታ መኖር (Short Slightness)፣ የዓይን መቆርቆር፣ ማቃጠል፣ መቅላት ይዳርጋሉ፡፡
የፀሐይ ብርሃን (Solar Light) ለዓይን ዕድገት ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ጨለማ ውስጥ ለረጅም ሰዓት ስልክና መሰል ቁሶችን መጠቀም ለዓይን ሕመም መንስዔ ይሆናል፡፡
ከዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁስ ውስጥ የሚወጣው ሰማያዊ ጨረር (Blue Light) በዋነኝነት ዓይን እንዲደርቅና እንዲቆጣ ብሎም የዕንባ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ የዓይን መድረቅ ደግሞ በቀላሉ ለዓይን አለርጂ ያጋልጣል፡፡ ይህንን ጨረር ለመከላከልም በሕክምና የታዘዙ እንደ ብሉ ከት፣ ፎቶ ሶላር፣ ግሌር ፍሪ የተሰኙ መነጽሮች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ሕፃናት የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶችን አብዝተው ሲጠቀሙ፣ አካላዊ ብቻም ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያ (ሳይኮሎጂስት) ማክዳ ገዛኸኝ በዚህ ዙሪያ ለሪፖርተር እንዳብራራችው፣ ልጆች ስልክና መሰል ቁሶች ላይ አብዝተው ጊዜ ሲያጠፉ ከሰዎች ጋር ያላቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ይቀንሳል፣ ንቁ አይሆኑም ክብደታቸው ስለሚጨምር በራሳቸው ለመተማመን ይቸገራሉ፣ የእንቅልፍ ጊዜያቸው ይዛባል፣ በቂ ዕረፍት ባለማድረጋቸው ለራስ ምታት ሕመም ይዳረጋሉ፣ ድብርትና ድባቴ መሰማት ያጋጥማቸዋል እንዲሁም ደስታንም ሆነ ሐዘናቸውን የሚያገኙት፣ ራሳቸውን የሚያነቃቁት በዲጂታል ማያ ገጽ ላይ ነው፡፡ ይበልጡኑም የቴክኖሎጂው ጥገኛ ይሆናሉ፡፡
በመማሪያና በመጠያየቂያ ጊዜያቸው ከተፈጥሮ፣ ከሰው፣ ከማኅበረሰቡ፣ ከፈጣሪያቸውም፣ ከራሳቸውም ጋር ይራራቃሉ፡፡ ራሳቸውን ለመግለጽም ሆነ መረዳት ብሎም የሌሎች ሰዎች ሐሳብ በትክክል የመገንዘብ አቅማቸው ደካማ ይሆናል፡፡
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ይከሰትባቸዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ያለመቻል (Social Anxiety) ያጋጥማቸዋል፡፡ ከወላጆቻቸው በመንፈስ ይራራቃሉ፡፡ ሲበሉ፣ ሲዝናኑ ሲደሰቱ፣ ሲከፉም ስልካቸውን ከመጠን በላይ ይለምዳሉ፡፡ በመሆኑም ወላጆች ለልጆች ስልክ ሲሰጡ ወይም ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ሲያደርጉ ዓላማውን ጠንቅቀው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ዶክተር ዘላለም እንዳሉት፣ ሕፃናት ለዓይን ሕመም እንዳይዳረጉ የዓይን ሕመም ከመከሰቱ በፊት ዓይንን መመርመር፣ ኮምፒዩተር ሲጠቀሙ መነጽሮች ማድረግ እንዲሁም ደግሞ የ20፣20፣20 ሕግን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የ20፣20፣20 ሕግ ማለት፣ ለ20 ደቂቃ ያህል የዲጂታል አንፀባራቂ መመልከቻ ቁሶች ላይ አብዝቶ የተጠቀመ፣ ለ20 ሰከንድ 20 ፊት (6 ሜትር) የሚሆን ርቀት ላይ መመልከት እናም ለ20 ጊዜ ዓይንን እየጨፈኑ መግለጥ ነው፡፡ ይህም ለዓይን ጤንነት ጥሩ እንደሆነ ዘላለም (ዶ/ር) የነገሩን ሲሆን፣ በዋነኛነት ግን የስልክና መሰል ቁሶችን አጠቃቀም መመጠን ከዓይን ሕመም እንደሚታደግ ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕፃናት ለዓይን ሕመም ከተጋለጡ ዓይናቸው እንዳይደርቅ በሐኪም የሚታዘዝ ጠብታ መድኃኒትና መነጽር ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ልጆችን ማንኛውንም ዲጂታል ስክሪን እንዳያዩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚመክረው የአሜሪካ የፔዲያትሪክ አካዴሚ ከሁለት ዓመት በላይ ያሉ ልጆችን ደግሞ በቀን ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ብቻ ቴሌቪዥን፣ ስልክ፣ ኮምፒውተር ላይ እንዲያጠፉም ይመክራል፡፡
ይህንንም ሲዘረዝረው ከሁለት እስከ 12 ዓመት ያሉ ልጆች በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ እንዲሁም ከ12 ዓመት በላይ እስከ ጎልማሶች በቀን ለሁለት ሰዓት መጠቀም እንዳለባቸው በማስገንዘብ ነው፡፡