

በግጭት ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች
ዜና ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚቀርብላቸው ዕርዳታ በመቀነሱ የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ
ቀን: October 30, 2024
- ማንነትን መሠረት ያደረገ በኃይል ማፈናቀል መባባሱን ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚቀርብላቸው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በዓይነት በመቀነሱ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ሦስተኛ ዓመታዊ ሪፖርቱን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡
የተፈናቃዮችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ በቂ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፎች ወቅቱን ጠብቀው ባለመቅረባቸው፣ ሴቶችና ወጣቶች ራሳቸውን ለጥቃትና ለጉልበት ብዝበዛ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሥራዎች ውስጥ እንዲሰማሩ መገደዳቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ከአንድ በላይ ቤተሰቦች በተጣበበ ሁኔታ ለዓመታት በፀሐይና በዝናብ በተጎዱ በጋራ የመጠለያ ሸራዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች በተዘጋጁ ንፅህና በጎደላቸው መጋዘኖችና ጅምር ሕንፃዎች ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውንና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችና ለደኅንነት ሥጋት መጋለጣቸው ተገልጿል፡፡
የተፈናቃዮችን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘቡ በመንግሥት አካላት የሚተላለፉ ሕጋዊ፣ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ያልሆኑ የተለያዩ ውሳኔዎች መብቶቻቸውን በማጣበብ ችግሮችን ሲያባብሱ እንደሚስተዋሉ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ኃላፊነትን መወጣትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለመቻሉን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ነዋሪዎችን ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው በኃይል በማፈናቀል የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ቡድኖችና ግለሰቦች በሕግ ባለመጠየቃቸው የተፈናቃዮችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚነፍግ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ይህም በአገሪቱ በስፋት የሚስተዋለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ሰዎችን በኃይል ማፈናቀል ድርጊት ተባብሶ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ ማድረጉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ተፈናቅለው በመቂ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አራቱን በአንድ አካባቢ መግደላቸውን፣ በዚህም ምክንያት ተፈናቃዮች በነፃነት በፈለግነው ሰዓት ለመንቀሳቀስ ሥጋት ፈጥሮብናል ሲሉ ለኮሚሽኑ እንደገለጹለት በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ እንዲኖር የሚያደርገውን የአፍሪካ ኅብረት የካምፓላ ስምምነት ጨምሮ ብሔራዊ የማስፈጸሚያ ረቂቅ ሕግ መንግሥት እንዲያፀድቅ፣ ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተሟላ ድጋፍና ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስተባብር በግልጽ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም በአፋጣኝ እንዲቋቋም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኃይል በተቀላቀለባቸው ግጭቶችና ጦርነት፣ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት መፈናቀል እየተከሰተ መሆኑን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ ለተፈናቃዮች መደረግ ያለባቸውን ሰብዓዊ ድጋፎች ጊዜያዊና የአደጋ ጊዜ ብቻ አድርጎ መውሰድ ትልቅ ክፍተት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ግጭቶችን በአፋጣኝ በሰላማዊ መንገድ መፍታትና እንዳይባባሱም አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲል በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡
መፈናቀልን ለመከላከል፣ ለተፈናቃዮች ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ መቅረቡን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት የፖለቲካ ፈቃደኝነትንና ቁርጠኝነትን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ መንግሥት ለችግሩ በቂ ትኩረት በመስጠት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል ብሏል።
ተፈናቃዮች እንደ ማንኛውም ዜጋ ወይም ነዋሪ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጠቅሶ፣ እነሱን በዘላቂነት ለማቋቋም ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው መመለስ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሲባል፣ የጥበቃና የድጋፍ ተግባራትን ማቋረጥና ተጠልለውባቸው የነበሩ ቦታዎችን መዝጋት ወይም ማፍረስ ለዳግም መፈናቀል ይዳርጋቸዋል ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተባብሶ ቀጥሏል ባለው ግጭት ምክንያት በተሽከርካሪ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው በሚኖሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በሚፈለገው መጠን ክትትልና ምርመራ ማድረግ እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት በሸፈነው ከሰኔ 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ፣ የአገር ውስጥ መፈናቀል አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡