

የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ
ማኅበራዊ የኩላሊት እጥበት ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ሕሙማን ከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸው ተነገረ
ቀን: October 30, 2024
የኩላሊት እጥበት ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ በሳምንት ሦስት ጊዜ እጥበት የሚያደርጉ ሕሙማን ከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን፣ የኩላሊት ሕክምና እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የኩላሊት ሕክምና እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉም የሕክምና ተቋማት የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል፡፡
ከዚህ በፊት አንድ ታካሚ የኩላሊት እጥበት ለአንድ ጊዜ ሲያደርግ ይፈጸም የነበረው ክፍያ 2,000 ብር እንደነበር፣ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ሲደረግ አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ተቋማት ከ3,000 እስከ 4,100 ብር እያስከፈሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ከውጭ ስለሚገቡ፣ የአገልግሎት ክፍያው በእጥፍ መጨመሩንና በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚጠቀም ታካሚ አንድ ጊዜ ብቻ ለማድረግ መገደዱን አክለው ገልጸዋል፡፡
በሞት ከተለዩ ሰዎች ኩላሊት እንዲወሰድ የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ድርጅቱ ጥረት ማድረጉን፣ ጉዳዩም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ በሕግ ማዕቀፍ ሲታገዝ በርካታ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ በቀላሉ እንደሚያደርጉ፣ እስከዚያው ግን ማኅበረበሰቡ ለኩላሊት ሕሙማን የተሻለ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በዘውዲቱ፣ በምኒልክና በጳውሎስ የሕክምና ተቋማት የሚገኙ 210 ሕሙማን በድርጅቱ ድጋፍ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ በግል ሆስፒታሎች አገልግሎት የሚያገኙ ሕሙማን በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ እጥበት ሲያደርጉ፣ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
የኩላሊት እጥበት ዓላቂ ግብዓቶች መወደድና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩና የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልጉ ሕሙማን ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን፣ የጽጌሬዳ የዲያሌሲስ ስፔሻሊስት ክሊኒክ ባለቤት አበበ ደምስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ብሔራዊ ባንክ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለሚሰጠው የሕክምና ተቋማት የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ቅድሚያ ይሰጥ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሆስፒታሉ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ለባንኮች ደብዳቤ ቢያስገባም ምላሽ አለማግኘቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ በቀን ለ18 ሕሙማን አገልግሎቱን እየሰጠ ቢሆንም፣ ሥራው አዋጪነት ስለሌለው ወደ ሌላ ሥራ ለመግባት እያሰቡበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ በኩላሊት እጥበት አላቂ ግብዓት ላይ የስድስት መቶ ብር ጭማሪ መደረጉን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ታካሚ እጥበት ለማድረግ ሲፈልግ 3,700 ብር ከፍሎ እንዲታከም እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሆስፒታሉ ለአንድ ታካሚ እጥበት ሲያደርግ 3,300 ብር ያስከፈል እንደነበር፣ አሁኑ ግን 3,700 ብር እያስከፈለ መሆኑንና ይህም አዋጭ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የኩላሊት እጥበት የሚያደርጉ ሕሙማን ችግር ውስጥ መግባታቸውን፣ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ እናቱ የኩላሊት እጥበት ማድረግ ከጀመሩ ስድስት ዓመታት ማስቆጠራቸውን፣ በእነዚህ ዓመታት ለሕክምና የሚያወጡት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት እናቱ በሳምንት ሦስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት ያደርጉ እንደነበር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁሉም የሕክምና ተቋማት ክፍያ በመጨመራቸው በሳምንት ሁለት ጊዜያት ለማድረግ መገደዳቸውን አክሏል፡፡
