October 30, 2024 – Konjit Sitotaw 

‹‹በተወሰኑ ክልሎች ላይ የተከሰተው የወባ እና ኮሌራ ወረርሽኝ የጤና መብትን አሳሳቢ አድርጎታል›› ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው ሪፖርት የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታን መዳሰሱን አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሸፈነ ሲሆን የጤና ፖሊሲው ሰብአዊ መብቶች ተኮር በሆነ መልኩ መቀረጹ፤ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ የተከራዮችን አቅም ባገናዘበና የመኖሪያ ቤት መብትን ለማረጋገጥ በሚያግዝ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋሉ በሪፖርቱ ከተካተቱ ቁልፍ እመርታዎች መካከል መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ከተከሰተው የትጥቅ ግጭት እና በሌሎች ክልሎችም ከቀጠለው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቤትና የመተዳደሪያ ንብረቶችን ጨምሮ በመሠረተ ልማቶችና የአገልግሎት ተቋማት ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን በተለይም በምግብ፣ በጤና፣ በንብረት፣ በትምህርት፣ በሥራና ተያያዥ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጻል።

በተጨማሪም አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ከግጭትና ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከሚከሰት የምርት መቀዛቀዝ እንዲሁም የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ በርካታ ሰዎችን ለምግብ እጥረት መዳረጉም ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ በተወሰኑ ክልሎች የተከሰተው የወባ፣ ኮሌራና ኩፍኝ ወረርሽኝ የጤና መብት ሁኔታን አሳሳቢ ማድረጉ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በርካታ የንግድና መኖሪያ ቤቶች ሕጋዊ ሂደትን ባልተከተለ መልኩ እንዲፈርሱ መደረጋቸው እና የሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱና በአግባቡ ባለመከፈሉ ምክንያት ሠራተኞች ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸው በሪፖርቱ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በመሆኑም መንግስት በተነሱ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ በማጤን እና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችና እርምጃዎች ሕጋዊ ሁኔታን በተከተለ መልኩ ከባለመብቶች ጋር ተገቢው ውይይት ተደርጎ እንዲወስን ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡