
ከ 5 ሰአት በፊት
መንካ ጎሚስ የተወለደው ፈረንሳይ ነው። ነገር ግን ወደ ወላጆቹ ሀገር ሴኔጋል ተመልሶ የመኖር ህልሙን ለማሳካት ቆርጦ ተነስቷል።
የ39 ዓመቱ መንካ ብቻ ሳይሆን በርካታ ፈረንሳዊ አፍሪካውያን ያሳደገቻቸውን ሀገር ጥቀለው ለመሄድ ቆርጠዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዘረኝነት፣ መገለል እና የሀገር ናፍቆት ነው።
ቢቢሲ አፍሪካ አይ ይህን ሲመረምር ቆይቷል። “ሳይለንት ኤክሶደስ” አሊያም “ድምፅ አልባው ፍልሰት” ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥሯል።
እንደ መንካ ያሉ ሰዎች ለምንድ ነው የፈረንሳይ ሕይወት ያንገሸገሻቸው?
የፓሪሱ መንካ አነስ ያለ የጉዞ እና አስጎብኚ ድርጅት አለው። አብዛኛው ጉዞ ወደ አፍሪካ ነው። ወደ ወላጆቻቸው ሀገር መመለስ ለሚፈልጉ የሚሆን መረሃ ግብር አዘጋጅቷል። ሴኔጋልም ቢሮ ከፍቷል።
“የተወለድኩት ፈረንሳይ ነው። ያደግኩትም እዚያው ነው። ብዙውን ጊዜ የዘረኝነት ጥቃት ይደርስብኛል። ገና የስድስት ዓመት ሕፃን እያለሁ ነው ትምህርት ቤት ውስጥ ‘ባሪያ’ ተብዬ የተሰደብኩት” ይላል መንካ።
መንካ ትምህርቱን የተከታተለው በደቡባዊ ፈረንሳይ የወደብ ከተማ ማርሴይ ነው።
“ፈረንሳዊ ነኝ። ነገር ግን የመጣሁት ከሌላ ቦታ ነው።”
የመንካ እናት በልጅነቷ ነው ወደ ፈረንሳይ የሄደችው። ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹን ጥሎ ለምን ወደ ሴኔጋል መመለስ እንደፈለገ አልገባትም።
“በህልም ዓለም ያለችውን አፍሪካ ብዬ አይደለም የምመለሰው” ይላል። የወላጆቹ ሀገር ሲመለስ ሁሉም ነገር ቀላል እንዳልሆነ ይረዳል። ነገር ግን ብዙ ዕድል አለ ይላል።
“አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ልክ አሜሪካ በአንድ ወቅት እንዳለፈችበት ያለ ጊዜ ላይ ናት። የወደፊቱ አህጉር ናት። የሚገነባ፤ የሚለማ ያለበት አህጉር ናት።”
በፈረንሳይ እና በሴኔጋል መካከል ያለው ግንኙነት ውስብስብ ነው። በአብዛኛው ሙስሊም ማኅበረሰብ ያላት ሴኔጋል የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት እና የባሪያ ንግድ መተላለፊያ ነበረች።

በቅርቡ ቢቢሲ አፍሪካ አይ በርካታ ሴኔጋላውያን አደገኛ የሚባለውን ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አውሮፓ እንደሚገቡ የምርመራ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል።
አብዛኞቹ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ናት። የፈረንሳይ የስደተኞች እና ሀገር አልባ ሰዎች ጥበቃ ቢሮ እንደሚለው ባለፈው ዓመት በርካታ ሰዎች ጥገኝነት ጠይቀዋል።
በጠቅላላው 142 ሺህ ሰዎች ጥገኝነት የጠየቁ ሲሆን፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል።
የፈረንሳይ ሕግ የዜጎችን ዘር፣ ሃይማኖት እና ጎሳ መጠየቅ ስለሚከለክል ምን ያህል ሰዎች ወደ አፍሪካ ተመልሰው እየፈለሱ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም።
ነገር ግን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የተማሩ እና እምነታቸው እስልምና የሆነ ዜጎች በተለይ ደግሞ የስደተኞች ልጆች ድምፅ ሳያሰሙ እየፈለሱ ነው።
ቢቢሲ ያናገራቸው ፈረንሳውያን እንደሚሉት በፈረንሳይ ለስደተኞች ያለው አመለካከት እየመረረ መጥቷል። አልፎም ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የበለጠ ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ ናቸው።
ባለፈው ወር ሥልጣን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሼል ባርኒዬ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ብሩኖ ሬታይሊያው ስደተኞችን ለመግታት ጠንክረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
- ካናዳ በስደተኞች ላይ በሯን እንድታጠብ ያደረጋት ምክንያት ምንድን ነው?28 ጥቅምት 2024
- ለሥራ ፈላጊ ስደተኞች በሯ ክፍት የሆነው የአሜሪካዋ ግዛት26 ጥቅምት 2024
- “አውሮፓ መግባት፤ ወይም ሞት” – ካናሪ ደሴት ለመግባት የቆረጠው ሞሐመድ15 ጥቅምት 2024
ፋንታ ጉዊራሲ ተወልዳ ያደገችው ፈረንሳይ ነው። ከፓሪስ ወጣ ብላ ባለች ክፍለ ከተማ በነርሲንግ ሙያ ተሰማርታ ትሠራለች። እሷም እንደ አጋሮቿ ወደ እናቷ ሀገር ሴኔጋል ለመመለስ ዕቅድ ይዛለች።
“በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደኅንነታችን እያሳሰበን መጥቷል። እርግጥ ነው እንዲህ ባልል ደስ ባለኝ ነበር፤ እውነታው ግን ይህ ነው” ስትል የ34 ዓመቷ ፋንታ ለቢቢሲ ትናገራለች።
“ልጄን ብቻዬን ነው የማሳድገው። የ15 ዓመት ታዳጊ ልጅ አለሽ ማለት ሁሌም ሆድሽን የሚቦረቡረው ነገር አለ ማለት ነው። ሁሌም ፍርሃት ይሰማሻል።”
ልጇ በቅርቡ መንገድ ላይ ከጓደኞቹ ጋር እያወጋ ሳለ በፖሊስ መፈተሹ የበለጠ የመሄድ ፍላጎቷ እንዲበረታ አድርጎታል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ትውልደ አልጄሪያዊው ናሄል ሜርዙክ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በመላው ፈረንሳይ ከባድ ነውጥ መነሳቱ ይታወሳል።
ፈረንሳይን ባናወጣት አመፅ ምክንያት በርካታ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል። በተለይ ከሌሎች ሀገራት የመጡ ስደተኞች በፈረንሳይ ያላቸው ቦታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ፈረንሳይ ውስጥ የሚኖሩ ጥቁሮች የተሳተፉበት አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ከጥናቱ ተሳታፊዎች 91 በመቶው የዘረኝነት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የሰኔውን አመፅ ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ፈረንሳይ “ሕግ አስከባሪዎቿ የሚፈፅሙትን ዘረኝነት መቆጣጠር አለባት” ብለው ነበር።
ለዚህ ምላሽ የሰጠው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቀሳውን አስተባብሎ “የፈረንሳይ ፖሊስ ዘረኛ እና አግላይ ነው የሚባለው መሠረት የሌለው ወሬ ነው። ፈረንሳይ እና ፖሊሶቿ ዘረኝነት እና የትኛውንም ዓይነት ማግለል ይቃወማሉ” ብሏል።
ቢሆንም የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ጥናት እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት የዘረኝነት ጥቃት በሦስት እጥፍ ሲጨምር 15 ሺህ ሰዎች በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው እና በጎሳቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ትውልደ ኮንጓዊቷ ኦድሪ ሞንዜምባ በዘረኝነት ምክንያት ሒጃብ ለማድረግ እንደምትሳቀቅ ትናገራለች።
ሒጃብ መልበስ ፈረንሳይ ውስጥ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። ከ20 ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሒጃብ መልበስ ተከልክሏል። ኦድሪ ወደ ሴኔጋል ለመሔድ የቆረጠችበት አንደኛው ምክንያት ይህ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2015 ኢስላማዊ ታጣቂዎች በፈረንሳይ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረሱት ጥቃት 130 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በሙስሊሞች ላይ የሚደርሰው ሃይማኖታዊ ጥቃት በርክቷል።
የ34 ዓመቷ ሶፍትዌር ዴቬሎፐር ፋጢማ ሲላ በሚቀጥለው ወር ሴኔጋል ለመመለስ ቆርጣለች። ወደ ምዕራብ አፍሪካ ተመልሳ ቢዝነስ መጀመር ነው ሐሳቧ። ነገር ግን ፓሪስ የተወለደው ወንድሟ አብዱል በዚህ ዕቅዷ አልተስማማም።
“እኔ ባህሌም ቤተሰቤም እዚህ ነው። አፍሪካ የወላጆቻችን አህጉር ናት። የእኛ ናት ብዬ አላስብም” ይላል።
ወደ ሴኔጋል የተመለሰው መንካ የሴኔጋል ዜግነቱን የሚያውጅበት ወረቀት ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።