October 31, 2024

ትራምፕን ምረጡ!!
ይህ አሜሪካ ለሚኖሩ አበሾች የምርጫ ቅስቀሳ ነው!!  ( አሌክስ አብርሃም )

የአሜሪካ ምርጫ አንድ ሳምንት ቀረው። ታዲያ እኛ ምናገባን የምትሉ እንዳላችሁ አውቃለሁ። ይህ ፅሁፍ ለእናንተ ስላልሆነ ልክ ናችሁ አያገባችሁም። በአሜሪካ ለሚኖሩና የመምረጥ መብት ላላቸው አበሾች የተፃፈ ነው። በተለይም የአበሻ ወላጆችን ለቅሶ ጭንቀትና መከራ እንዳየ ሰው ይህን እላለሁ።

ምናልባት እስከአሁን ማንን እንደምትመርጡ ካልወሰናችሁ እኔ በግልፅ ትራምፕን እንድትመርጡ ለመቀስቀስ ነው ይህን የምፅፈው። በዘረኝነት እና ወዘተ ስሙ በክፉ እንደሚነሳ ግልፅ ነው። ይህም ቢሆን ባስተዳደረባቸው አመታት ከነጆ ባይደን የባሰ የሚወራውን ያህል የከፋ ነገር አልታየበትም። ለሀብታሞች ያደላል የሚል ቅሬታም ይነሳል። ኮቪድን ጨምሮ በተከሰቱ ሁነቶች ድሆችን ከተራ ምግብ ጀምሮ መክፈል እስካቃታቸው ሞርጌጅ በተለያየ መንገድ የደገፋቸው የትራምፕ አስተዳደር ነበር። እውነታው ትራምፕ አሜሪካን ከልብ ይወዳል፣ ከነጉድለቱ በፈጣሪ መኖር ያምናል። ከምንም በላይ ግን …

ብዙሀኑ አበሻ የመጨረሻ ህይወቱ ልጆቹ ናቸው። ለልጆቹ እድሜውን፣ ጤናውን ፣ ጉልበቱን ያልከፈለ አበሻ የለም። እንቅልፍና አምሮቱን ሁሉ ለልጆቹ ያልሰዋ ወላጅ አይገኝም። ህልሙም የልጆቹ የነገ ስኬት ነው። ልጆቹ ነፍሱ ናቸው “ሰው አለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ያደርግለታል” እንዲል መፅሐፉ ካሜላና ፓርቲዋ በቀጥታ የአበሻም ይሁን ሌሎች ልጆች እጣ ፋንታ ላይ አደገኛ ካርድ የመዘዙ የጥፋት ደቀመዝሙሮች ናቸው። አሜሪካን ወደአሳዛኝ ገደል እየገፉና በዴሞክራሲ ስም የመጨረሻውን የዴሞክራሲ አስኳል እሱንም “ልጅን በራስ ባህል በራስ እምነትና ማንነት የማሳደግ መብት” ለመንጠቅ እየታገሉ ነው። ቤተሰብን የሚበትን መርገምት። ፅንስ መግደልን እንደትልቅ የዴሞክራሲ ስጦታ እየሰበኩ ነው፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ጉዳዮችም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል እቅድ የላቸውም። እንደውም አሜሪካ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የኑሮ ውድነት ላይ ጥደዋታል። ቤት ህልም ሁኗል፣ ምግብ ተትረፍርፎ ገንዳዎችን የሚሞላባት አሜሪካ የምግብ ወጭ እስከማሳሰብ ደርሷል።

ትራምፕ ሐብታሞችን መደገፉ ፍፁም ጤነኛ መንገድ ነው። ሁላችንም ወደአሜሪካ የመጣነውና ሚሊየኖችም አሜሪካን የሚመኙት ለፅድቅ አይደለም! ሐብታም አገር ስለሆነች ነው። ሰርቶ ተምሮ ለመለወጥ፣ የተሻለ ኑሮ ለመኖር። የሀብቷ ምንጭ የብዙ ሀብታም ግለሰቦች ድምር አገር መሆኗ ነው። ለማንም አገር ቢሆን ሀብታም ማብዛት ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የህልውናው ጉዳይ ነው። የውጭ ፖሊሲያቸው ላይ አገራችንን ጨምሮ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ከራሳቸው አንፃር ስለሚያዮት ማንም አገር የራሱን ጥቅም ካላስከበረ ሌላው ለርሱ ብሎ ፖሊሲ ሊቀርፅለት አይችልም።

የሆነ ሆኖ ለልጆቻችሁ እጣ ፋንታ፣ ለሰበአዊነት፣ እንዲሁም ለቆማችሁለት ሞራላዊም ይሁን ሐይማኖታዊ እምነት የሚበጃችሁ ትራምፕ ነው። በነገራችን ላይ መምረጥ መቻላችሁን እንደቀልድ አይታችሁ እንዳታሳልፉት ። ለዚህ መብታችሁ ብዙዎች ነፍሳቸውን ከፍለዋ፣ ፊዳ ሆነዋል። ምረጡ! ፍላጎትና ማንነታችሁን በድምፃችሁ አስከብሩ። ድምፃችሁ ለልጆቻችሁ የምትመዙት የዋስትና ካርድ ነው። ትራምፕ ጥቁር ብሎ ሰደባችሁ የሚሉት ሕይወታችሁን ጨለማ እንዲዘሩበት አትፍቀዱ። ከልጆቻችሁ የሚቀድም አንድ ነገር አስቡ …አለ?

ድል ለጓድ ዶናልድ ትራምፕ
ሰላም ፣ፍቅር ፣ሰርቶ ልጆችን በራሱ ወግና ባህል ፣ እምነትና ስርዓት ማሳደግ፣ ለቁም ነገር ማብቃት፣ ቤተሰብን መርዳት ለመላው አበሻ፣ ለመላው ቤተሰብ!!