በትግራይ የተዘሩ እና የተበተኑ የጦር መሳሪያዎች
የምስሉ መግለጫ,በትግራይ የተዘሩ እና የተበተኑ የጦር መሳሪያዎች

ከ 21 ደቂቃዎች በፊት

በትግራይ ገጠራማ መንደር ነዋሪ የሆነው ብርሃነ ኃይሌ ከትምህርት ቤት ሲመለስ አንዲት ቅጽበት መላ ሕይወቱን ላይመለስ ቀየረችው።

የ16 ዓመቱ ታዳጊ የረገጠው መሳሪያ ፈንድቶ ግራ እግሩን መታው።

ስጋና አጥንቱ ተለያይቶ በደም አበላ ተጥለቀለቀ። ከፍተኛ ሕመም ሰቅዞ ያዘው።

“ፍንዳታው ወደ ኋላ አሽቀነጠረኝ። ስፍራው በደም ተጥለቀለቀ። የአካባቢው ነዋሪዎች ድምጹን ሰምተው እየተቻኮሉ መጡ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

አባቱ እና ሌሎቹ የመንደር ነዋሪዎች ተሸክመው ወደ አድዋ ከተማ ለመሄድ ተራራማውን መንገድ ለሁለት ሰዓታት ያህል ሲጓዙም ብርሃነ ሕመሙን መቋቋም ነበረበት።

በመንደራቸው አቅራቢያ ያለው ሆስፒታል አድዋ በመሆኑም ነው ሕመምተኛ ተሸክመው ለሰዓታት በእግራቸው የተጓዙት።

ሆስፒታል ከደረሱም በኋላ የሕክምና ባለሙያዎቹ የታዳጊውን ሕይወት መታደግ ቢችሉም እግሩ መቆረጥ ነበረበት።

የተወሰነው የእጆቹ ክፍልም በፍንዳታው ተጎድቷል።

ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ፈንጂ መሬት ላይ ተዘርቷል። መሬት ላይ ተጥለው ወይም ተቀብረው ሳይፈነዱ በቀሩ የጦር መሳሪያዎች በብዛት ከሚገኙባት መካከል የእነ ብርሃነ ሳያቦ ተራራማ የገጠር መንደር አንዷ ናት።

በዚህች ገጠራማ መንደር በዋነኝነት የእጅ ቦምቦች፣ ተተኳሾች እንዲሁም ታጣቂዎች ሲሸሹ የተዋቸው የጦር መሳሪያዎች ይገኛሉ።

ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ እጅግ አስከፊ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤት አልባ እንዲሁም በእርዳታ ጥገኛ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል።

ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀው ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች በአንድ ወገን ሆነው የትግራይ ኃይሎች በሌላኛው ጎራ ሆነው የተፋለሙበት ነው።

በፍንዳታ እግሩን ያጣው ብርሃነ ኃይሌ
የምስሉ መግለጫ,በፍንዳታ እግሩን ያጣው ብርሃነ ኃይሌ

አፍሪካ ሕብረት በዚህ ጦርነት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን እንደሚደርስ ግምቱን ያስቀመጠ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ተዳርገዋል።

አፈሙዞችን ጸጥ ያሰኘው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ሁለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁንም በጦርነቱ ቅሪት የሚገደሉ እና የሚቆስሉ ሰዎች እንደቀጠሉ ነው።

ብርሃነ በዚያች ዕለት ከተለመደው የእግር መንገዱ የወጣው ሳር ሲግጡ ያያቸው የቤተሰቡን በጎች እና ፍየሎች ወደ ሌላ ሰው መሬት እንዳይሄዱ ለመከልከል ነበር። በዚያ ወቅት ነበር ሳያውቀው የረገጠው መሬት የነበረው መሳሪያ የፈነዳው።

ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ ቀይ መስቀል ወደ 400 የሚጠጉ የፍንዳታ ተጎጂዎችን መርዳቱን ገልጾ ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው ብሏል።

የእርዳታ ድርጅቱ ይህ ቁጥር አናሳ እንደሆነ ገልጾ መሬት ላይ ያለው አኃዝ ከፍተኛነቱን አስረድቷል።

ባለቤቷ በአድዋ አቅራቢያ በምትገኘው ኒዊ ወረዳ በደረሰበት ፍንዳታ ሲገደል ንግሥት ግደይ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች።

በመንደራቸው የነበረ የግንባታ ስራን ለማገዝ በሄደበት ወቅት ነው የተጣሉ መሳሪያዎችን የረገጠው። በወቅቱ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

“መሳሪያዎች በየስፍራው ወድቀው ይገኛሉ” ትላለች ንግስት

አክላም “ባለስልጣናቱ በመንገድ ላይ ማንኛውንም ብረት እዳንነካ ያስጠነቅቁናል” ብላለች

በአንዳንድ አካባቢዎች ያልፈነዱ የጦር መሳሪያዎችን ለመሰብሰብ ጥረት ተደርጓል። ከነዚህም ስፍራዎች አንዷ ከአድዋ ዋና መንገድ ዳር በምትገኘው ጎሬሮ በተሰኘችው ትንሽ መንደር እርሻዎችን እና ማሳዎችን ለመመንጠር ሞክረዋል።

ነገር ግን ሰፊ የሆነ ምንጠራ ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ አቶ ሀዱሽ ገብረመድህን ይህንንም ለማከናወን አለቆቻቸውን ተጨማሪ ድጋፍ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የፖሊስ አዛዡ እስካሁን ምላሽ ያላገኙ ሲሆን ምናልባትም የፈንጅ አወጋገድ ባለሙያዎች እጥረት እና የሃብት ውስንነት ጋር ሊያያዝ ይችላል።

የትግራይ መንደር

አቶ ሐዱሽ እንደሚናገሩት ያገኟቸውን መሳሪያዎች መቆጣጠሪያቸውን (ፊውዝ) ማውጣት ቢችሉም ከፍተኛ ሙቀት ወይም ድንገተኛ እሳት ሊያፈነዳቸው እንደሚችሉ ይናገራሉ።

የተቀበሩ እና የተጣሉ ቦምቦችን፣ ፈንጅዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን ከአገራት በማጽዳት የተሰማሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በትግራይ ሊመጡ ቢችሉም ትልቅ ቅንጅት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

በአድዋ ከተማ ተቀጣጣይ የጦር መሳሪያዎችን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለማስወገድ አማራጮች ያጡ ባለስልጣናት ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወደ ከተማዋ የሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እያከማቹ ይገኛሉ።

በነ ብርሃነ መንደር በተራሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ ሲያስገመግም የሚያንዳቸው ያ ፍርሃት ጠፍቷል።

በጦርነቱ ወቅት እንዲቋረጡ የተደረጉ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ እና ኢንተርኔት ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች የስያቦን፣ የሌሎች መንደሮች እንዲሁም የከተሞችን ሕይወት መልሶታል።

ጦርነቱ ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር ብርሃነ ወደ ትምህርት ቤት የተመለሰው። ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ከደረሰበት አደጋም በፊት ቢሆን ቤተሰቡ ከባድ ኃዘን ላይ ነበሩ።

በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ታጋይ የነበረው ታላቅ ወንድሙን አጥቷል። እንዲሁም ሌላኛዋ ታጋይ እህቱም በደረሰባት ከባድ አደጋ የአካል ጉዳተኛ የሆነች ሲሆን አሁንም በመቀለ የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል።

ሌላኛዋ በምዕራብ ትግራይ ትኖር የነበረች እህቱ በአስገዳጅ ሁኔታ ከቤቷ እንድትፈናቀል የተደረገች ሲሆን አሁንም ቢሆንም አካባቢው የትግራይ እና አማራ ክልሎች እየተወዛገቡበት በመሆኑ መመለስ አልቻለችም።

ብርሃነን ለመርዳት ከመውጣቷ በፊት በአድዋ ከተማ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ጣቢያ ትኖር ነበር።

ብርሃነ በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት እርዳታ ሰው ሰራሽ እግር እና ክራንች በማግኘቱ እንደገና እንዲራመድ አስችሎታል።

ከባድ ተራራማ የእግር ጉዞ ማድረግ ፈታኝ ስለሆነበት ወደ ተራራማዋ ስያቦ መንደር መመለስ አልቻለም። ከዚህ ቀደም 20 ደቂቃ የሚወስድበት ከመንደሩ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚያደርገው ጉዞ አሁን አንድ ሰዓት ያህል ይወስዳል።

የትግራይ መንደር

በዚህም ምክንያት አድዋ ከተማ ሄዶ ከእህቱ ጋር ቤት ተከራይተዋል። እህቱ አሁንም የእርዳታ ጥገኛ በመሆኗ ሁሉንም ወጪያቸውን እንዴት እንደሚሸፍኑ ባያውቁትም ለብርሃነ ትምህርቱን ለመቀጠል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህ ነው ይላል።

ፍንዳታው ጣቶቹን ስለጎዳቸው የክፍል ጓደኞቹ በመጻፍ ያግዙታል።

“የተቀላቀለ ስሜት ይሰማኛል” ይላል ብርሃነ ስላለበት ሁኔታ ሲናገር

“አንዳንድ ጊዜ እናደዳለሁ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሕይወት እንዳለሁ አስቤ አመሰግናለሁኝ” ይላል።

አንድ ቀን አርሶ አደር የመሆን ህልሙ ተቀጭቷል። ከአደጋው በፊት አባቱን በቆሎ፣ ማሽላ እና ሌሎች እህሎች በሚያመርቱበት የቤተሰብ እርሻ ላይ ያግዛቸው ነበር።

ብርሃነ የጦርነቱ መከራ የተደራረባቸው ወላጆቹን ትቶ ወደ ከተማ በመሄዱ ማዘናቸው አልቀረም።

ብርሃነ በበኩሉ አንድ ቀን እረዳቸዋለሁ በሚል ተስፋ በጽናት ትምህርቱን ለመከታተል እና የመንግሥት ሰራተኛ የመሆን አላማን አንግቧል።