የኢኳቶሪያል ጊኒ ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ማንጉ
የምስሉ መግለጫ,ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ማንጉ

ከ 6 ሰአት በፊት

በሥራ ቦታቸው ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ የሚያዙ የመንግሥት ሠራተኞች “ከባድ እርምጃ” እንደሚጠብቃቸው የኢኳቶሪያል ጊኒ ምክትል ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁ።

ይህ የምክትል ፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው በመቶዎች የሚቆጠሩ የወሲብ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሰራጩ በኋላ ነው።

ቪዲዮዎቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን የሆነውን ባልታዛር ኢባንግ ኢንጎንጋ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሚስቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ሴቶች ጋር በቢሮው ውስጥ ወሲብ ሲፈጽም የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።

ኢንጎንጋ የአገሪቱ ብሔራዊ የፋይናንስ ምርመራ ኤጀንሲ ኃላፊ እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዘመድ መሆናቸው ተነግሯል።

በጉዳዩ ላይ የተከሰሱት ባለሥልጣን አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ጥያቄ አቀርቧል።

ኢንጎንጋ በፌስቡክ ገጹ ላይ የእሱን የአንዲት ሴትን እና የልጆችን ፎቶ በመለጠፍ “ቤተሰብ ሁሉም ነገር ነው” የሚል ጽሁፍ አስፍሯል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ማንጉ እንደተናገሩት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ቦታ ወሲብ ሲፈጽም ከተገኘ “የሥነ ምግባር ደንቡን በመጣስ” ምክንያት ከሥራው ይታገዳል ብለዋል።

“ሥነ ምግባር የጎደላቸውን እና ሕገወጥ ድርጊቶችን” ለመከላከልም የደኅንነት ካሜራዎች በፍርድ ቤቶች እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲተከሉ አዘዋል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው ውሳኔው የተላለፈው “የአገሪቷን ገጽታ የሚያንቋሽሹ ቪዲዮዎች” በሰፊው በመሰራጨታቸው ነው።

ምርመራ እንዲጀመር ምክረ ሃሳብ መቅረቡንም አክሏል።

እነዚህ ጥያቄ የተነሳባቸው ቪዲዮዎች ሾልከው የወጡት ኢንጎንጋ በሙስና ክስ ከታሰሩ በኋላ መሆኑን መንግሥታዊው መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ ባለፈው ሳምንት “የወሲብ ምሥሎች” በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ “እየጎረፉ ነው” በማለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ሥርጭቱን እንዲገቱ አዘዋል።

ከዚያ ወዲህ በአገሪቱ የኢንተርኔት ፍጥነት (በተለይም ምሥሎችን የማውረድ ፍጥነት) ክፉኛ ቀንሷል ሲሉ የኢኳቶሪያል ጊኒ ነዋሪዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

ኤንጎንጋ የብሔራዊ የፋይናንስ ምርመራ ኤጀንሲ ኃላፊ እንደመሆኑ ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ወንጀሎችን በመዋጋት ላይ ይሠራል።

በቪዲዮዎቹ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ ተከትሎ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ዐቃቤ ሕግ አናቶሊዮ ንዛንግ ንጉዌማ ለመንግሥታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት ኢንጎንጋ “በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መያዙ” ከተረጋገጠ “በሕዝብ ጤና” ላይ በፈጸመው ጥፋት ይከሰሳል ብለዋል።

የመንግሥት ባለሥልጣን የሆነው ግለሰብ በመልከ መልካምነቱ ምክንያት “ቤሎ” (በስፓኒሽ ቆንጆ ማለት ነው) የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል ተብሏል።