በእስራኤል የተነሳው ተቃውሞ
የምስሉ መግለጫ,በእስራኤል የተነሳው ተቃውሞ

ከ 9 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮአቭ ጋላንትን ማባረራቸውን ተከትሎ በእስራኤል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ናታንያሁ በእሳቸው እና በመከላከያ ሚኒስትራቸው መካከል የተፈጠረው “የመተማመን ቀውስ” ወደዚህ ውሳኔ እንዳመራቸው ገልጸው በጋላንት ላይ ያላቸው እምነት በቅርብ ወራት ውስጥ “ተሸርሽሯል” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ እሳቸውን እንደሚተኩ ገልጸዋል።

ጋላንት በበኩላቸው ከስልጣን የተነሱት በሶስት ጉዳዮች ላይ በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል እስራኤል የቀሩትን ታጋቾች ከጋዛ ለመመለስ ስምምነቶችን ለመቀበል መሸከም የምትችለው ስምምነት ውስጥ ልትገባ ይገባል የሚለውን ጨምሮ ነው።

አደባባይ ላይ የወጡ በርካታ ተቃዋሚዎች ናታንያሁ ከስልጣን እንዲወርዱ የጠየቁ ሲሆን አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ታጋቾችን የማስለቀቅ ስምምነት እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ናታንያሁ እና ጋላንት ለረጅም ጊዜ ልዩነት በተሞላበት የስራ ግንኙነት ቆይተዋል። እስራኤል በጋዛ ላይ በምታደርገው የተቀናጀ ጥቃት ላይ ልትከተለው ስለሚገባ የጦርነት ስልት ላይ ከፍተኛ አለመግባባት እንዳሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል አክራሪ የሚባሉ የይሁዲ እምነት ተከታዮች በውትድርና ከመሰማራት ነጻ መደረጋቸው መቀጠሉ ደስተኛ አልነበሩም።

የጋዛ ጦርነት ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ከመጀመሩ ከወራት በፊት ናታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትሩን በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት አባረዋቸው ነበር። ሆኖም ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞን ተከትሎ ወደ ኃላፊነት ስፍራቸው እንዲመለሱ ተደርገው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮአቭ ጋላንት
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮአቭ ጋላንት

ነገር ግን ማክሰኞ ዕለት ናታንያሁ “በጦርነት መካከል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ መካከል ሙሉ እምነት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ምንም እንኳን በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ መተማመን እና “ፍሬያማ ስራዎች” ቢሰሩም ባለፉት ወራት ይህ እምነት “ተሸርሽሯል” ብለዋል።

ናታንያሁ አክለውም “በእኔ እና በጋላንት መካከል ወታደራዊ ዘመቻውን አስመልክቶ ጉልህ ክፍተቶች ታይተዋል” ብለዋል።

እነዚህም “ከመንግሥት ውሳኔዎች ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶች እና መግለጫዎች ታክለውባቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

የመባረራቸውን ዜና ተከሎ ጋላንት “የእስራኤል መንግሥት ደህንነት የህይወቴ ተልዕኮ ሆኖ ይኖራል” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለጥፈው ነበር።

ከስልጣናቸው የተነሱት “በሶስት ጉዳዮች ላይ ባለመግባባት የተፈጠረ ነው” ሲሉ በኋላ ማክሰኞ ምሽት ባወጡት መግለጫ አትተዋል። በውትድርና ላይ ለመሰማራት ልዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደማይገባ፣ ብሔራዊ ምርመራዎች እንዲካሄዱ እና ታጋቾች በተቻለ ፍጥነት መመለስ ይኖርባቸዋል የሚሉ ናቸው።