
ከ 9 ሰአት በፊት
የኬንያ ፍርድ ቤት ኡጋንዳዊውን አትሌት ቤንጃሚን ኪፕላጋትን ባለፈው ዓመት ታህሳስ ገድለዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ 35 ዓመት እንዲቀጡ ወስኗል።
የኦሎምፒክ ተሳታፊው የመሰናክል ሯጩ የአትሌቶች መፍለቂያ በመባል በምትታወቀው በኤልዶሬት ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት በስለት ተወግቶ ተገድሏል።
በኤልዶሬት በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ዳኛ ሩበን ኛኩንዲ “ራሱን መከላከል በማይችል ሰው ላይ የወሰዳችሁት እርምጃ ጭካኔ የተሞላበት ነበር” ሲሉ ፒተር ኡሹሩ ካሉሚ እና ዴቪድ ኤካይ ሎኬሬ ለተባሉት ወንጀለኞች ተናግረዋል።
የኪፕላጋት ግድያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሌሎች በርካታ አትሌቶች በተገደሉባት ኬንያ ብዙዎችን አስደንግጧል።
ዳኛው አክለውም ካሉሚ እና ሎኬሬ በመኪናው ውስጥ የነበረውን ኪፕላጋትን ከመከታተላቸውም በላይ በደህነነት ካሜራ ምስል እንደታየው ከሆነ ሆን ተብሎ በታሰበበት መልኩ ገድለውታል።
የግድያው ትክክለኛ ምክንያት ግልጽ ባይሆንም ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ጊዜ ፖሊስ ዘረፋ ነው ብሎ ነበር።
- በአማራ ክልል አዊ ዞን ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ6 ህዳር 2024
- ናታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትሩን ማባረራቸውን ተከትሎ በእስራኤል ተቃውሞ ተቀሰቀሰከ 9 ሰአት በፊት
- የትግራይን ጦርነት ስላስቆመው የፕሪቶሪያው ድርድር ያልተሰሙ ታሪኮች5 ህዳር 2024
የአትሌቱ እናት ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ዳኛው የዕድሜ ልክ እስራት እንዲያስተላልፍ ስሜታዊ በሆነ መልኩ ጠይቀዋል።
ሩጫን በባዶ እግሩ መሮጥ የጀመረው ልጇ ዓለም አቀፍ ሯጭ ለመሆንና የቤተሰቡን ኑሮ ለማሸነፍ ጠንክሮ እንደሠራ መናገራቸውን ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
“ልጄ 62 ዶላር እና ውድ ሞባይል ይዞ ነበር። ገዳዮቹ ግን ምንም አይነት ንብረት አልወሰዱበትም። ተልዕኳቸው እርሱን አሰቃይተው መጨረስ ነበር” ማለታቸውን ጋዜጣው አክሏል።
የቤተሰቡ የዕድሜ ልክ እስራት ጥያቄ ተቀባይነት ባያገኝም በውጤቱ መደሰታቸውን እና ፍትህ መስፈኑን ተናግረዋል።
በ34 ዓመቱ የተገደለው ኪፕላጋት በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ለፍፃሜ ደርሷል። በቀጣዮቹ ሁለት ኦሎምፒኮች ከመሳተፉም በላይ የርቀቱ የኡጋንዳ ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።