ካማላ ሃሪስዴሞክራት
ዶናልድ ትራምፕሪፐብሊካን
ለማሸነፍ የሚያስፈልገው 270
223 279
66,443,509 ድምጽ(47.4%)
71,491,756 ድምጽ(51%)
https://www.bbc.com/amharic/articles/cr5m82zrv00o

4 ህዳር 2024
አሜሪካዊያን ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አምርተው ለፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ድምፃቸውን ይሰጣሉ።
እርግጥ ነው በዩናይትድ ስቴትስ ሰዓት አቆጣጠር መሠረት ምርጫው በአብዛኛዎቹ ግዛቶች ማክሰኞ ከሰዓት አካባቢ ነው የሚጀምረው።
የድምፅ መስጫው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላም አሸናፊው ወይም አሸናፊዋ ለሰዓታት ላይታወቁ ይችላሉ። ሰዓታት ብቻ አይደለም፤ ቀናት አሊያም ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።
እነሆ ስለምርጫው ውጤት ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮች።
የምርጫው ውጤት መች ነው የሚታወቁት?
የወቅቱ ምክትል ፕሬዝደንት ዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስ እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ለሳምንታት አንገት ለአንገት ተናንቀው ቆይተዋል።
የምርጫው ቀን ቢቃረብም በብሔራዊው እና ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች ያለው የነጥብ ልዩነት አሁንም ጠባብ ነው። በሁለቱ ዕጩዎች መካከል ያለው የውጤት ልዩነት እጅግ ጠባብ ከሆነ ድምፅ ድጋሚ ሊቆጠር ይችላል።
የምርጫውን ውጤት ለመውሰን ወሳኝ ናቸው የሚባሉት ሰባት ግዛቶች እንዴት ነው ድምፅ የሚቆጥሩት? የሚለውም ወሳኝ ነው።
በሌላ በኩል እንደ ሚሺጋን ያሉት ግዛቶች የድምፅ ቆጠራቸውን እያፋጠኑት ነው። በርካታ ግዛቶች በኮቪድ ጊዜ በፖስታ ነበር ድምፅ የሰበሰቡት። ነገር ግን ይህ አሁን እየቀነሰ ይገኛል።
የምርጫ አሸናፊ በድምፅ መስጫው ምሽት፣ አሊያም በነጋታው ካልሆነ ደግሞ ከቀናት ወይም ከሳምንታት በኋላ ሊታወጅ ይችላል ማለት ነው።
- የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ ዓለምን እንዴት ሊቀይር ይችላል?30 ጥቅምት 2024
- ትራምፕ ለአሜሪካ ከፈጣሪ የተላኩ መሪ ናቸው ብለው የሚያምኑት ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖች28 ጥቅምት 2024
- የካማላ ሃሪስ እና የዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ የፖሊሲ አቋሞች ምን ይመስላሉ?3 ጥቅምት 2024

የምርጫ 2020 ውጤት
ያለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ በአውሮፓውያኑ 2020 ማክሰኞ ኅዳር 3 ነው የተደረገው። ነገር ግን ጆ ባይደን አሸናፊ መሆናቸው የተሰማው ቅዳሜ ኅዳር 7 ቀን ነበር።
በድምፅ መስጫው ቀን የትራምፕ ደጋፊዎች ዕጩው ፕሬዝደንት እንዳሸነፉ እርግጠኛ ነበሩ። ሁለቱም ዕጩዎች ፕሬዝደንት መሆን የሚያስችላቸውን ድምፅ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰው ነበር።
አብዛኞቹ ግዛቶች ድምፅ በተሰጠ በ24 ሰዓታት ውስጥ ውጤት ቢያሳውቁም ፔንሲልቬኒያ እና ኔቫዳን ጨምሮ በተወሰኑ ግዛቶች ቆጠራው ቀናት ወስዷል።
19 ኢሌክቶራል ኮሌጅ ያላት ፔንሲልቬኒያ ወደ ዲሞክራቶች ማድላት ጀመረች። ቅዳሜ ጥዋት ነው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጆ ባይደን አሸናፊ መሆናቸውን ያወጁት።
ሲኤንሲኤን ባይደን ማሸነፋቸውን ያወጀ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ 15 ደቂቃዎች ሌሎች ጣቢያዎችም ይህን ዜና ሰበሩ።
ውጤት የሚታወቀው መቼ ነው?
ለወትሮው የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የሚታወቀው በድምፅ መስጫው ምሽት አሊያም ግፋ ቢል በነጋታው ጠዋት ነው።
ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2016 ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ ውጤት የታወቀው ከድምፅ መስጫው ቀጥሎ ባለው ቀን ነበር።
በ2012 ደግሞ ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ ውጤቱ ይፋ የተደረገው በድምፅ መስጫው ቀን እኩል ለሊት ገደማ ነው።
ነገር ግን በ2000 በጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና አል ጎር መካከል የተደረገው ምርጫ ከሌሎቹ ለየት ይላል።
በፍሎሪዳ ግዛት ሁለቱ ዕጩዎች የነበራቸውን ጠባብ ውጤት ተከትሎ ድምፅ ድጋሚ እንዲቆጠር ቢታዘዝም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ በመግባት በግዛቲቱ በውጤት እየመሩ የነበሩት ቡሽ አሸናፊ እንዲሆኑ ወስኗል።

ቁልፍ ግዛቶች
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የሚወሰነው በጥቂት ግዛቶች በሚገኝ ድምፅ ነው።
ለዚህ ምክንያቱ ኢሌክቶራል ኮሌጅ የተባለው ሥርዓት ነው። ይህ ማለት አሜሪካ ፕሬዝደንቷን የምትመርጠው ዕጩዎች በሚያሸንፉት ግዛት መሠረት ነው። አብዛኛዎቹ ግዛቶች ዲሞክራት አሊያም ሪፐብሊካን ናቸው።
ዘንድሮ በጣም ወሳኝ የሚባሉት ግዛቶች ሰባት ናቸው። እነሱም አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ዊስኮንሲን፣ ፔንስሊቪኒያ እና ሚሸጋን ናቸው። ባለፈው ምርጫ ባይደን በአሪዞና እና ጆርጂያ ግዛቶችም ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ኔቫዳ ግዛትም እንዲሁ ለሁለቱም ያላደላች ብትሆንም የሕዝብ ብዛቷ አነስተኛ መሆኑ አስፈላጊነቷን ዝቅ ያደርገዋል።
ፍሎሪዳ እና ኖርዝ ካሮላይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ አድልተዋል። ቨርጂኒያ እና ኮሎራዶ ደግሞ ወደ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አዘንብለዋል።
ድምፅ የሚቆጠረው እንዴት ነው?
ብዙውን ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጠው በምርጫው ቀን ለሚሰጡ ድምፆች ነው። ቀጥሎ ደግሞ ከድምፅ መስጫው ቀን በፊት የመረጡ እና በፖስት ድምፃቸውን ያስገቡ ሰዎች ቆጠራ ይካሄዳል።
ከውጭ ሀገራት እና ከወታደራዎ ካምፖች የሚላኩ እንዲሁም ድጋሚ እንዲቆጠሩ የተደረጉ ድምፆች ይከተላሉ።
የአካባቢ የምርጫ ባለሥልጣናት አንዳንዶቹ የተሾሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ተመርጠው የመጡ ናቸው። እነዚህ የምርጫ አስተባባሪዎች ናቸው
አስተባባሪዎች የተሰጠውን ድምፅ እና የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ያመዛዝናሉ፤ መረጃዎችን ያጣራሉ፤ ጉዳት የደረሰባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ይፈትሻሉ፤ አለመመሳሰል ካለበት ደግሞ ምርመራ ያደርጋሉ።
ወረቀቶቹ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ገብተው ውጤታቸው እንዲቆጠር ይደረጋል። አንዳንዶቹ ድምፆች ደግሞ በእጅ ሊቆጠሩ ይችላሉ።
ድምፁ ትክክለኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ መጀመሪያ በክፍለ-ግዛት ቀጥሎ ወደ ግዛት ይሸጋገራል።
አዲስ የሚመረጡት ፕሬዝደንት በአውሮፓውያኑ ጥር 20/2025 ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ።