
6 ህዳር 2024
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ የመንግሥት ኃይሎች በርካታ ሰዎችን ቤት ለቤት እና መንገድ ላይ መግደላቸውን ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከክልሉ መዲና ባሕር ዳር 104 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ከተማዋ ከአንድ ሳምንት በፊት እሁድ ጥቅምት 17/2017 ዓ.ም. በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ውጊያ መደረጉን ተከትሎ ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ 23 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቱ መካሄዱን አረጋግጠው ንጹሃን ሰዎች አልተገደሉም ሲል አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ጥቆማ ደርሶት እያጣራ እንደሆነ፣ ነገር ግን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ ገና እንዳላረጋገጠ እና የተጎጂዎችን መጠን እንዳላወቀ ለቢቢሲ ገልጿል።
ክስተቱን በተመለከተ ቢቢሲ መረጃ ለማግኘት ለቀናት ጥረት ቢያደርግም በተፈጠረው ስጋት እና ሐዘን ምክንያት ነዋሪዎች ስለሁኔታ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቆይተው ነበር።
የፋግታ ለኮማ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ ቅዳም ጥቅምት 17 ጠዋት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጡ መጀመሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የተኩስ ልውውጡ በከተማዋ ዙሪያ ከተጀመረ በኋላ “. . . እየጠነከረ ሲሄድ ወደየ ሰፈራችን ገባን” ያሉ አንድ ነዋሪ የተኩስ ልውውጡ “ከባድ” እንደነበር ገልጸዋል።
ነዋሪዎች ረፋድ 5፡00 አካባቢ ላይ የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን “አብዛኛውን ክፍል” እንደተቆጣጠሩ ጠቁመው፤ የተኩስ ልውውጡ ያዝ ለቀቅ እያለ እስከ 10፡00 ሰዓት ድረስ መቆየቱን አመልክተዋል።
“[የተኩስ ልውውጡ] ‘ኳኩራ መውጫ’ የሚባለው ላይ ተጀመረ። ከዚያ ወደ መሀል [ከተማ] የፋኖ ኃይል እየገፋ መጣ። ሌላ [ተጨማሪ መንግሥት] ኃይል ሲመጣ ደግሞ [ፋኖ] ለቆ ወጣ። በዚህ መሀል ነው በርካታ ንጹሃን የተገደሉት” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
“[ወታደሮቹ] ቦታቸውን ለቀው ሲሄዱ ያገኙትን ሰላማዊ ሰው መሀል ከተማ ላይ አስፓልት ላይ ሲገድሉ ነበር” ሲሉ እማኝነታቸውን የሰጡ ሌላ ነዋሪ፤ ግድያውን “የበቀል ይመስላል” በማለት ገልጸዋል።
“ያገኙትን ወጣት በለው፣ ድፋው፣ አስተኛው እያሉ ነው [የገደሏቸው]። ህጻናት ናቸው፤ የ18 ዓመት፣ የ20 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶች ናቸው። በአጋጣሚ ተኩሱ ያባራ መስሏቸው ወደ ውጭ የወጡትን አስፓልት ላይ እንዲሁም ቤት ገብተው መቷቸው” ብለዋል።
የመንግሥት ኃይሎች ‘አድጓሚ ተራራ’ ወደ ተባለ ስፍራ ሲያፈገፍጉ ግድያው ተጽሟል ያሉ ሌላ ነዋሪ፤ የስድስት ሰዎችን አስከሬን በዓይናቸው ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
‘ታግታ እና ደለከስ መገንጠያ’ በተባሉ አካባቢዎች ላይ አብዛኞቹ ግድያዎች መፈጸማቸውን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ በጥቃቱ ወጣቶች አና ሽማግሌዎች መገደላቸውንም ጠቅሰዋል።
ሌላ ነዋሪም ግድያው “በሦስት ዓይነት መልክ” እንደተፈጸመ ተናግረው፤ ቤት ለቤት እና መንገድ ላይ ከተገደሉት በተጨማሪ አዝመራቸው ውስጥ የተገደሉ አርሶ አደሮችም እንዳሉ አመልክተዋል።
“ሻይ ቤት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችን በር ከፍተው አውጥተው ረሽነዋል። መንገድ ላይ ያገኙትን ረሽነዋል። መኖሪያ ቤትም ተከትለው ገብተው በር ከፍተው ጊቢ ውስጥ ያገኙትን ገድለዋል” ሲሉ ስለ ግድያው ተናግረዋል።
የጥቅምት 17ቱ ተኩስ ልውውጥ ከወትሮው የተለየ “ሞቅ ቀዝቀዝ” ያለ ነበር ያሉ አንድ ሌላ ነዋሪ፤ ይህም በመሆኑ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ አልተገደበም ነበር ብለዋል።
“. . . መኪና [የሕዝብ ትራንስፖርት] አልቆመም ነበር። ያልሰሙ ከመኪና ላይ የወረዱ ሰላም መስሏቸው ሲሄዱ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
- የትግራይን ጦርነት ስላስቆመው የፕሪቶሪያው ድርድር ያልተሰሙ ታሪኮች5 ህዳር 2024
- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ በርካታ ሠዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ2 ህዳር 2024
- በምሥራቅ ወለጋ የጦር መሳሪያ አስረክቡ የተባሉ የአማራ ተወላጆች ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናገሩ1 ህዳር 2024
ከዳንግላ ከተማ ወደ አዲስ ቅዳም እየመጣ ነበር ያሉት ቤተሰባቸው ከመኪና ወርዶ እየተጓዘ እያለ መንገድ ላይ እንደተገደለባቸው አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
መታወቂያው ታይቶ መርዶ እንደተነገራቸው የገለጹት ቤተሰብ፤ ሟቹ የ23 ዓመት ወጣት እና ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ እንደነበር ነዋሪው ተናግረዋል።
ሌላ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነ የሰፈሩ ልጅ እንዲሁ “ቀለብ ለመውሰድ ወደ ቤተሰብ ሲመጣ” በመንግሥት በተመሳሳይ ሁኔታ መገደሉንም ተናግረዋል።
“የባጃጅ ሠራተኛ [ሹፌር] የነበረ፣ አንደኛው አረቂ የሚሸጥ፣ ተማሪ፣ አንዱ ሱቅ የከፈተ ነጋዴ” ከተገደሉት ውስጥ እንደሚገኙበት አንድ ነዋሪ አመልክተዋል።
“አብዛኞቹ [ሟቾች] ምንም የማያውቁ፣ የፖለቲካ ግንዛቤ የሌላቸው፣ ለፍተው የሚድሩ፣ የቀን ሥራ የሚሠሩ ናቸው” ያሉ ሌላ ነዋሪ ደግሞ ግድያውን “የሚያሳዝን” ብለውታል።
“ልጅ ያለው ነው ይሄን ሊረዳው የሚችለው። አልፎም ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ። ሳይታሰብ፤ ሳይታለም. . .” በማለት ስለተጠማቸው ሐዘን የቤተሰብ አባላቸው የተገደለባቸው ነዋሪ ለቢቢሲ እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።
“. . . ህጻናት እና ወጣቶች ናቸው” ሲሉ የሰለባዎቹን የዕድሜ ክልል የገለጹ ነዋሪው፤ አንድ የ11 ዓመት ታዳጊ ልጅ ከሟቾች ውስጥ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
ሁለት ነዋሪዎች በጥቃቱ 23 ሰዎች መገደላቸውን ሲናገሩ፤ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ 18 ሰዎች መገደላቸውን እንደሰሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ይህን ያህል ነው ብለው መናገር እንደሚከብዳቸው ጠቁመው፤ “እኔ የማውቃቸው 10 ሰዎች ሞተዋል” ብለዋል።
“ማየት ይዘገንናል። . . . ከባድ ነው፤ ያሳዝናል” ሲሉ ጥቃቱን የገለጹ እና የአራት ሰዎችን አስከሬን ማየታቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ጥቃቱ “በአጋጣሚ የተገኙት ላይ ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ ታልሞ የተፈጸመ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
“[የመንግሥት ኃይሎች] ተመተው ይሁን ምን ይሁን አናውቅም። የበቀል እርምጃ ሕዝቡ ላይ እንደወሰዱ ነው እኛ ያረጋገጥነው” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ስለ ጥቃቱ ተናግረዋል።
መንገድ ላይ የተገደሉ ሰዎች አስከሬን “ተኩሱ ሲቆም” በሕዝቡ እንደተነሳ አንድ ነዋሪ የተናገሩ ሲሆን፤ ቀብራቸውም በተለያዩ ቀናት በአዲስ ቅዳም እና በዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች ውስጥ መፈጸሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳደር ግን በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ግጭቱ እንደነበር አረጋግጦ፤ ንጹሃን ሰዎች አልተገደሉም ሲል አስተባብሏል።
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢሻው “ሰላማዊ ሰው አልተገደለም” በማለት የመንግሥት ኃይል ያልታጠቀ ሰው ላይ “ጥይትም አይተኩስም” ብለዋል።
“የጠላት ፕሮፓጋንዳ” ሲሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ ያጣጣሉት ኃላፊው፤ “የአገር መከላከያ ሰላማዊ ሰዎችን ይዞ እርምጃ የሚወስድበት አንዳችም ምክንያት የለም” ሲሉ ጥቃቱን ከእውነት የራቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኃላፊው በነበረው ግጭት ከፋኖ ኃይሎች ሦስት የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉ እና መሳሪያም እንደማረኩም አክለው ተናግረዋል።
በአዲስ ቅዳም ከተማ የመንግሥት ኃይሎች እንደዚህ ዓይነት ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ባለፈው ዓመት በፋሲካ በዓል ማግስት ከ11 እስከ 15 የተገመቱ ሰዎች “በዓል እያከበሩ እያለ” ተገድለዋል ብለዋል።
“ከፋኖ ኃይል ጋር ተኩስ ሲለዋወጡ፤ ሕዝቡን መጥተው ይመታሉ። ለእኛ ሊገባን ያልቻለው ይሄ ነው። ሕዝቡ የራሱን ኑሮ ነው የሚኖረው። የገጠማቸው ኃይል አለ፤ ለእርሱ ማወራረጃ የሚያደርጉት ሕዝቡን ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ በምሬት ተናግረዋል።
በአካባቢው በአሁኑ ወቅት ያለው “ድባብ ከባድ ነው” የሚሉት ነዋሪ የተኩስ ልውውጦች ከጥቃቱ በኋላም እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
“የሐዘን ቆፈኑ ማኅበረሰቡን አልለቀቀውም። ተስፋ ቆርጧል። ምንም ዋስትና የለውም። አሁንም ማንገራገር አለ፤ አፈና አለ። ማኅበረሰቡ ቀን እስኪወጣ እየጠበቀ ነው” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው በአማራ ክልል በመካለከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በክልሉ ውስጥ ከባድ ችግር ማስከተሉን ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት እየተናገሩ ነው።
በሁለቱም ኃይሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ጥቂት የማይባሉ ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የመብት ተሟጋቾች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።
*ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ በአዲስ ቅዳም የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ አራት ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ ለደኅንነታቸው ባላቸው ስጋት ምክንያት ስማቸው እና የሚኖሩበት አካባቢ እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።