- የዶናልድ ትራምፕ ሕይወት በምሥሎች
- ከ 3 ሰአት በፊት
የዶናልድ ትራምፕ ሕይወት በምሥሎች

የዶናልድ ትራምፕ ሕይወት በምሥሎች

ከ 3 ሰአት በፊት
ዶናልድ ጆን ትራምፕ ኒው ዮርክ ውስጥ በምትገኘው ኩዊንስ በምትባል አካባቢ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 14/1946 ነበር የተወለዱት።
ወላጆቻቸው ካሏቸው ሦስት ወንዶች እና ሁለት ሴት ልጆች መካከል አራተኛው ናቸው። ወንድሞቻቸው ፍሬድ ጁኒየር እና ሮበርት እንዲሁም እህቶቻቸው ማሪያን እና ኤልዛቤት የሚባሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉት እህታቸው ኤልዛቤት ብቻ ናቸው።
አባታቸው ፍሬድ እዚያው ኒው ዮርክ ውስጥ ስኬታማ የግንባታ ተቋም ባለቤት ነበሩ። ትራምፕ በ1968 ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራውን ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆዩ በመሃል ማንሃተን ውስጥ ራሳቸውን ችለው መሥራት ጀመሩ።



ትራምፕ የካዚኖ ማጨወቻዎች፣ ኮንዶሚኒየሞች፣ የጎልፍ መስኮች እና ሆቴሎችን በባለቤትነት በመያዝ ሀብታቸው በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ከመስፋፋቱ በተጨማሪ ሥራውን ወደ ሕንድ፣ቱርክ እና ፊሊፒንስ አስፋፍተዋል።
ባላቸው ዘናጭ እና ትኩረት የሚስብ የሕይወት ዘይቤ ምክንያት ትራምፕ በኒውዮርክ የንግዱ ዘርፍ ጎልተው እንዲታዩ ከማድረጉ በተጨማሪ በመዝናኛው ዓለም ‘ዘ አፕሬንቲስ’ የተባለ የቴሌቪዥን ትርዒት በማቅረብ ዝነኛ ሆኑ።



ሦስት ጊዜ ጋብቻ የመሠረቱት ትራምፕ አምስት ልጆች አባት ናቸው። የመጀመሪያ የጋብቻ ቀለበታቸውን ያሰሩት ከኢቫና ዜሌኒኮቫ ጋር በአውሮፓውያኑ 1977 ነው።


ትራምፕ ሦስተኛ ሚስታቸው የሆነችውን ሜላኒያ ናውስን የተዋወቁት ከ20 ዓመት በፊት ሲሆን፣ ከመጋባታቸው ሰባት ዓመት በፊት ሲገናኙ ትራምፕ 52 ሜላኒያ ደግሞ 28 ዓመታቸው ነበር።
የትራምፕ የፖለቲካ ሕይወት የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2015 በቤተሰቦቻቸው ተከበው ትራምፕ ታወር በተባለው ሕንጻ ውስጥ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ሲያሳውቁ ነበረ።
ትራምፕ የምርጫ መቀስቀሻ መፈክራቸው “አሜሪካንን እንደገና ታላቅ ማድረግ” (Make America great again) የሚል ነው።



ከስምንት ዓመታት በፊት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት ትረምፕ እና ሂላሪ ክሊንተን ዕጩዎች ነበሩ። ሁለቱ ዕጩዎች ለመመረጥ ከፍተኛ ፉክክር ከማድረጋቸው በተጨማሪ ውዝግብም ነበረው።
በመጨረሻም ትራምፕ ሂላሪን በመርታት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን በአውሮፓውያኑ 2017 ቃለ መሐላ ፈጸሙ።


ከውጭ አገራት መሪዎች ጋር በይፋ በተደጋጋሚ ሲወዛገቡ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸው ለአሜሪካ ወዳጆች የተረጋጋ ወቅት አልነበረም።
ትራምፕ ዋነኛ ከሚባለው የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አገራቸውን በማስወጣት ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበረ።


ትራምፕ የሥልጣን ዘመናቸው የመጨረሻው ዓመት በኮቪድ ወረርሽኝ አያያዛቸው ምክንያት ከፍተኛ ትችት ውስጥ የቆዩበት ነበረ።
በሽታውን ተከትሎ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት ትራምፕ የኮሮና ቫይረስ ተግኝቶባቸው ከምርጫ ቅስቀሳው እረፍት እንዲወስዱ ተገደው ነበር።

በ2020 በተካሄደው ፕሬዝዳንታው ምርጫ ትራምፕ በጆ ባይደን ቢሸነፉም ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ምክንያት ውጤቱን አልቀበልም ብለው ነበር።
ደጋፊዎቻቸውም ዋሽንግተን ውስጥ የሚገኘውን የአገሪቱን ምክር ቤት እንዲወሩ ጥሪ አድርገው ከባድ ቀውስ ተከስቶ ነበር።
ተቃውሞው ተባብሶ ወደ ረብሻ ተቀይሮ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ትራምፕ በዕለቱ የፈጸሙት ተግባር ሁለት የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው አድጓል።


በተለያዩ ምክንያቶች በቀረቡባቸው በርካታ ክሶች ምክንያት የትራምፕ ፖለቲካዊ ሕይወት ያበቃለት መስሎ የነበረ ቢሆንም፣ ለሁለተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ አሳውቀው ወዲያው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው በአሁኑ ምርጫ ቀረቡ።
ትራምፕ የአሁኑን የምርጫ ዘመቻቸውን የጀመሩት 91 ክሶች ቀርበውባቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ባለበት ጊዜ ነው።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ትራምፕ የማጭበርበር እና ምሥጢር እንዳታወጣ ለአንዲት የፊልም ተዋናይት በከፈሉት ገንዘብ ምክንያት ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በ34ቱ ጥፋተኛ ተባሉ።
የቀረቡባቸው ክሶች ያላገዷቸው ትራምፕ ዳግም በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ ቅስቀሳ እያካሄዱ ባለበት ወቅት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ፔንሲልቬኒያ ግዛት በትለር ከተማ ውስጥ በአንድ የ20 ዓመት ጎረምሳ ከተተኮሰባቸው ጥይት ለጥቂት ነበር የተረፉት።


ትራምፕ በጥይት ከተመቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ በተካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ተገኝተው የፓርቲው ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰየሙ።
ትራምፕ ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን በዕጩነት የቀረቡበትን የአሁኑን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ በታሪክ በዕድሜ የገፉ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
የሥልጣን ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ ዕድሜያቸው 82 ዓመት ይሆናል።
