በሀዲያ ዞን በደረሰ ከባድ ዝናብ ከ15 ሺ በላይ አርሶአደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ሸሾጎ ወረዳ ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ ከዘጠኝ መቶ 87 በላይ ሄክታር ማሳ መሬት ላይ የደረሱ ሰብሎችን ከጥቅም ውጪ ማድረጉ ተገለጸ።
በሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ጎርፉ ያደረሰው ጉዳት በወረዳው በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ላይ ሲሆን በደረሰው አደጋ 15 ሺ 850 አርሶ አደሮች ተጎጂ ሆነዋል ብሏል፡፡
በመሆኑም ተዘርቶ ለመሰብሰብ የደረሰ የጤፍ፣ የስንዴ የበቆሎ፣ የማሽላና ሌሎችም ሰብሎች ከጥቅም ውጭ ማድረጉን እና 9 መቶ 87 ሄክታር ማሳ በላይ በጎርፍ መጥለቅለቁ ተጠቁሟል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በነበረው ዝናብ እና ከተራራማ አካባቢ የሚወርደው ጎርፍ ጉደር፣ መቴቾሴ እና ወራ ወንዞች ሞልተው በመፍሰሳቸው የጎርፍ አደጋው መከሰቱ ተገልጻል፡፡
በወረዳው የተከሰተው አደጋ ጉዳት ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የክልሉ እና የፌዴራል ተቋማት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡም ጥያቄ መቅረቡ ተመላክቷል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ የሚገኘው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለያዩ ክልሎች በደረሱ እና እየደረሱ በሚገኙ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡