November 6, 2024 

“እስከ መቶ እጥፍ ደሞዝ ጨምረናል” የተባለው ውሸት ነው!
….
የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች መምህራን የደምወዝና የጥቅማጥቅም ማስተካከያ እንዲደረግ የዓብይ አህመድ አገዛዝ በመጣ ማግስት ጀምሮ እስከ ስራ ማቆም የደረሰ ጥያቄ፣ ቀጥሎም የስራ ማቆም አድማ ተደርጎ ነበር።

ዓብይ አህመድም የመምህራን ተወካዮችን አግኝተው የተለመደ ስድብና ለሌክቸረሩ ስለራሳቸው ኢጎ (Ego ) ሌክቸር ማድረጋቸው በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

ታዲያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት በሚዲያ እስከ መቶ እጥፍ ድረስ ደምወዝ ጨምረናል የተባለለት የደምወዝ ጭማሪ የመምህሩን ጥያቄ ወደጎን በመተው እንደአገር የተጨመረው ደምወዝ ጭማሬ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች መከፈል ጀምሯል። አንዳንዶች ስድብና ንቀት፣ ለትምህርት ዘርፉ የአብይ ምልከታ ከዚህ የተሻለ እንዳልሆነ፣ ትምህርት ጠል ስርዓት ፣ አፍቃሬ ጦርነት አገዛዝ በጎበዝ አለቃው አብይ አህመድ እየነገሰ ስለመምጣቱ ምልክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለአንድ ሌክቸረር ከ115.75 የአሜሪካ ዶላር በታች ደምወዝ ከፋይ አገር ሆናለች። አለም በትምህርት ያምናል። ለትምህርት ማህበረሰቡና ልሂቁ ከፍ ያለ ቦታ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጀምሮ ክብር ይሰጣል። በአገዛዙ በኩል ማሰር፣ ማሳደድና ማዋከብ ሲሆን የተጀመረው ይህ ትምህርት ጠልነትም የትምህርት ሚኒስተር ሲሰይሙ የጀመሩት መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።

የአዲስ አበባው የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (ምንም እንኳ እርሳቸውም የስርዓቱ አሽቃባጭ ቢሆኑም) አብይን ወፈር ባለ ትችት የነረቱት ከትምህርት ጋር በተያያዘ መሆኑ ይታወሳል። የፍልስፍና መምህሩ ” ጫካ ጠመንጃ ይዞ ሲዋጋ የነበረ ጦረኛ ወደአገር አስገብተው የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ስለመሾማቸው” በስላቅ ትችት ወርውረው ነበር።

የመምህራን ደምወዝ የእውነትም በአገር ግንባታና የትውልድ ግንባታ ተግባር ላይ ለተሰማሪ ያውም ለጀምሩ የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ ይህ መሆን አልነበረበትምተ የትምህርት ጥራት ጋር አብሮ የሚነሳው የመምህራን የኑሮ ሁኔታ፣ የስራና ክፍያ አለመመጣጠን አሁንም በትውልድ ንቅዘት ላይ አገዛዙ ይሁነኝ ብሎ እየሰራ ስለመሆኑ ልብ ይሏል።