https://www.bbc.com/ws/includes/include/vjafwest/1365-2024-us-presidential-election-banner/amharic/app

የትራምፕ ደጋፊዎች

ከ 5 ሰአት በፊት

የዶናልድ ትራምፕ ድል እውን መሆኑ መታወቅ ሲጀምር ጀምሮ የ47 ዓመቷ ኖራ ምሽቱን በጭንቀት አሳልፋለች። አሜሪካ ውስጥ ለ24 ዓመታት ኖራለች። ሁለት ሴት ልጆቿ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት አላቸው። አውዳሚ አውሎ ንፋስ ኒካራጓን ባጠቃበት ወቅት ነው ሰነድ አልባ ሆና አሜሪካ መኖር የጀመረችው።

“እንቅልፌን አጥቻለሁ። መተኛት አልቻልኩም። ፍርሃቱ እንደገና ተመልሷል” ስትል በስደተኝነቷ ምክንያት ስሟ እንዳይጠቀስ ጠይቃ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በመመለሳቸው በአሜሪካ ያለፈቃድ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለማስወጣት የገቡትን ቃል ሊፈጽሙ ይችላሉ ስትል ኖራ ፈርታለች።

ትራምፕ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “በአገራችን ታሪክ ትልቁ የተባለለትን የስደተኞች ማባረር እንፈጽማለን” ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ጄዲ ቫንስ በቅርቡ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተዋል። በዚህም “በአንድ ሚሊዮን እንጀምር … እና ከዚያ መቀጠል እንችላለን” ብለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ ስደተኞችን የማስወጣት ሥራ ከፍተኛ የሕግ እና የሎጂስቲክስ መሰናክሎች እንደሚገጥመው ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

የኖራ ሴት ልጆች

ስንት ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ ይኖራሉ?

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር እና የፒው የቅርብ ጊዜ ጥናት መረጃ እንደሚያሳየው እስከ 2022 ድረስ በአሜሪካ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ነበሩ። ይህም ከጠቅላላው ሕዝብ 3.3 በመቶ የሚሆነው ይይዛሉ።

ከ2005 ወዲህ ስተኞቹ ቁጥር በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሆኖ ቆይቷል። ከኩባ፣ ቬንዙዌላ፣ ሄይቲ እና ኒካራጓ ለመጡ 500 ሺህ ስደተኞች የተሰጡት እንደሰብአዊ ፈቃድ ያሉ ጉዳዮች ግምት ውስጥ አልገቡም ሲል ፒው ገልጿል።

አብዛኞቹ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች የረጅም ጊዜ ነዋሪ ናቸው። ወደ 80 በመቶ የሚጠጉት ስደተኞች በአገሪቱ ከአስር ዓመታት በላይ የቆዩ ናቸው። ግማሽ ያህሉ ከሜክሲኮ የመጡ ናቸው። ጓቲማላ፣ ኤል ሳልቫዶር እና ሆንዱራስ ተከታዮቹን ስፍራ ይዘዋል።

እነሱም በስድስት ግዛቶች ውስጥም በብዛት ይገኛሉ፡ ካሊፎርኒያ፣ ቴክሳስ፣ ፍሎሪዳ፣ ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ኢሊኖይ ናቸው።

የሕግ ተግዳሮቶች

ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ከመባረራቸው በፊት የፍርድ ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህ ሂደቶችን የማግኘት መብት አላቸው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ለማባረር መሞከር ደግሞ ቀድሞውንም የፍርድ ቤቶች በተከማቸው የስደተኞች ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራል።

አብዛኞቹ ስደተኞች እንዲባረሩ የሚደረጉት ከኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ አስከባሪ (አይሲኢ) ወኪሎች ሳይሆን በየግዛቶቹ በሚገኙ ሕግ አስከባሪዎች ነው። ብዙዎቹ ትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች እና አውራጃዎች የፖሊስ ኃይላቸው ከአይሲኢ ጋር ያለውን ትብብር የሚገድቡ ሕጎች አሏቸው።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻ ወቅት በእነዚህ “ከተሞች” ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብቷል። የአገሪቱ ውስብስብ የአካባቢ፣ የክልል እና የፌደራል ሕጎች ሁኔታውን ያወሳስቡታል።

የማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት (ኤምፒአይ) ባልደረባ የሆኑት ካትሊን ቡሽ-ጆሴፍ፣ በአይሲኢ እና በየአካባቢ ባለሥልጣናት መካከል የሚኖረው ትብብር ለማንኛውም የጅምላ ማባረር ዕቅድ “ወሳኝ” እንደሚሆን አፅንኦት ሰጥተዋል።

“የየግዛቶቹ ሕግ አስከባሪ አካላት ከተባበሩ አይሲኢ ስደተኞችን ከመፈለግ ይልቅ ከየእስር ቤት ለመውሰድ ይቀላቸዋል” ብለዋል።

እንደቡሽ-ጆሴፍ ግን ብዙዎች ከትራምፕ የጅምላ ማባረር ዕቅድ ጋር አይተባበሩም። የፍሎሪዳ ብሮዋርድ እና የፓልም ቢች አውራጃዎች የፖሊስ ጽህፈት ቤቶች ያወጡትን መግለጫ በመጥቀስም ኃላፊዎቹ አንስማማም ማለታቸውን አንስተዋል።

ማንኛውም የጅምላ ማባረር ዕቅድ ከኢሚግሬሽን እና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሕግ ጥያቄዎች ጋር ሊገጥሙት ይችላሉ።

የ2022 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ግን ፍርድ ቤቶች የሕግ ጉዳዮቹን እየገመገሙ ቢሆንም ስደተኞችን ማባረር እንዲቀጥል ፈቅዷል።

የሎጂስቲክስ ፈተናዎች

የሜክሲኮ አሜሪካ ድንበር

ምንም እንኳን የአሜሪካ መንግሥት እንደዚህ ባሉ ዕቅዶች ዙሪያ በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ቢችልም፣ ባለሥልጣናት ግን ትልቅ የሎጂስቲክስ ፈተናዎችን ማለፍ ይኖርባቸዋል።

በባይደን አስተዳደር ወቅት ማባረሩ ያተኮረው በቅርቡ በድንበር ላይ በተያዙት ስደተኞች ላይ ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት ከአሜሪካ በየዓመቱ የሚባረሩ ስደተኞች ቁጥር ከ100 ሺህ በታች ሆኖ ቆይቷል። በኦባማ አስተዳደር መጀመሪያ ወቅት ይህ ቁጥር ከ230 ሺህ በላይ ደርሶ ነበር።

“በአንድ ዓመት ይህንን ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ለማድረስ ብዙ ሀብቶችን ማፍሰስ ይጠይቃል” ሲሉ በአሜሪካ ኢሚግሬሽን ካውንስል የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት አሮን ራይችሊን-ሜልኒክ ተናግረዋል።

የአይሲኢ አሁን ያሉት ሠራተኞች ቁጥር 20 ሺህ ወኪሎች መሆኑን እና ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ከገቡት ቃል አንጻር ጥቂቱን እንኳን መፈጸም ስለመቻላቸው ባለሙያዎች ይጠራጠራሉ።

ራይችሊን-ሜልኒክ አክለውም የማባረሩ ሂደት ረጅም እና የተወሳሰበ መሆኑን ተናግረዋል። ማባረሩ የሚጀምረው ሕጋዊ ሰነድ የሌለውን ስደተኛ በመለየት እና በማሰር ብቻ ነው ብለዋል።

ከዚያ በኋላ እስረኞች ወደ ኢሚግሬሽን ዳኛ ከመቅረባቸው በፊት በመኖሪያ ቤት ወይም “በማቆያ ስፍራ” መቀመጥ አለባቸው። ይህ ደግሞ በተከማቸው የስደተኞች የፍርድ ሂደት ላይ የሚጨመር ነው።

ከዚያ በኋላ ብቻ ነው ስደተኞች ከአሜሪካ የሚወጡት። ይህ ሂደት ደግሞ ከተቀባይ አገር የሚሰጥ ዲፕሎማሲያዊ ትብብርንም የሚጠይቅ ነው።

“በእያንዳንዱ አካባቢም አይሲኢ በቀላሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በተመሳሳይ ሂደት የማሳለፍ አቅም የለውም” ብለዋል ሬይችሊን-ሜልኒክ።

ትራምፕ የብሔራዊ ዘብን ወይም ሌሎች ወታደራዊ ኃይሎችን በስደተኞች ማባረር ላይ እንዲሳተፉ ሃሳብ አቅርበዋል።

የአሜሪካ ጦር በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚጫወተው ሚና በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ድጋፍ በማድረግ ብቻ የተገደበ ነው። ይህ ዕቅድ እንዴት ይፈጸማል በሚለው ዙሪያ ትራምፕ ጥቂት ዝርዝሮችን ብቻ አቅርበዋል ።

ትራምፕ ከታይም መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አዳዲስ የስደተኞች ማቆያ ስፍራዎችን ስለመገንባት እና ፖሊስ ያለመከሰስ መብት እንዲኖረው እንዲሁም ለተባባሪዎችን ማበረታቻዎችን እንደሚሰጥ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ጥብቅ የስደተኞች ቁጥጥር እንዲኖር የሚጠይቀው የነምበርስዩኤስኤ የጥናት ዳይሬክተር ኤሪክ ሩርክ በበኩላቸው ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር እንዲኖር አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ይህ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ በአገር ውስጥ ያሉት ላይ ማተኮር በጣም ትንሽ ለውጥ ብቻ ያመጣል” ብለዋል።

ሕጋዊ ያልሆኑ ሠራተኞችን በሚቀጥሩ ኩባንያዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።

“ለሥራ እየመጡ ነው። እነዚህን ሥራዎችም እያገኙ ነው። ምክንያቱም የሕግ አስከባሪ አካላቱ ፈርሰዋል” ብለዋል።

የገንዘብ እና የፖለቲካ ወጪዎች

ዶናልድ ትራምፕ

ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ከሆነ አንድ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ስደተኞችን ለማባረር የሚወጣው ወጪ አስር ወይም መቶ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ።

አይሲኢ እአአ በ2023 ለመጓጓዣ እና ለማባረር የተፈቀደለት በጀት 420 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በዚያ ዓመት ኤጀንሲው ከ140 ሺህ በላይ ሰዎችን ከአገር አባሯል።

የማቆያ ማዕከላትን መገንባት እና የማባረሪያ በረራዎችን ማስፋፋትም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልገዋል። በአስር ወይም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮች ያስፈልጋል ብለዋል ሬይችሊን-ሜልኒክ።

ትራምፕ ደቡባዊውን የድንበር አጥር ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ ከመጠየቁ አንጻር የሀብት ሽሚያ ይፈጠራል።

የላቲን አሜሪካ የዋሽንግተን ጽሕፈት ቤት የፍልሰት እና የድንበር ኤክስፐርት የሆኑት አዳም አይዛክሰን ደግሞ “የቅዠት ሃሳቦች” ያሉት የጅምላ ማባረር የትራምፕ አስተዳደርን ከሕዝብ ግንኙነት አንጻርም ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል ብለዋል።

“በአሜሪካ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚያውቋቸው እና የሚወዷቸው ሰዎች ሲባረሩ ያያሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “በቲቪ ላይም የሚያለቅሱ ልጆች እና ቤተሰቦች ሊያዩ ይችላሉች። ይህ ሁሉ መጥፎ ስም ይፈጥራል። ይህ የቤተሰብ መለያየት ነው” ብለዋል።

የጅምላ ማባረር ከዚህ በፊት ተከናውኖ ነበር?

በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተባረዋል። የባይደን አስተዳደር እነዚህ አሃዞች ላይ ለመድረስ እየተንደረደሩ ነው።

በኦባማ ሁለት የሥልጣን ዘመን ደግሞ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከአሜሪካ ተባርረዋል። ይህም ከአንዳንድ የኢሚግሬሽን ተሟጋቾች “ዋናው አባራሪ” የሚል ቅጽል ስም አስገኝቶላቸዋል።

ምናልባትም በቅርቡ የተደረገው የጅምላ ማባረር የተከናወነው እአአ በ1954 ሲሆን እስከ 1.3 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በዘመቻ ዌትባክ የተባበሩበት ነው።

ይህ ፕሮግራም ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። አንደኛው ምክንያት አንዳንድ የአሜሪካ ዜጎች አብረው በመባረራቸው ነው። ይህም በ1955 ተጠናቋል።

የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ዘመቻው ከሩቅ አገራት የመጡ ቤተሰቦችን ሳይሆን ያላገቡ የሜክሲኮን ወንዶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ከዘመናዊው የማባረር ጥረት ጋር በቀጥታ የሚወዳደር አይደለም።

ከባድ ውሳኔ

ኖራ ወደ ትውልድ አገሯ ኒካራጓ መመለሷ በጣም አስፈሪ ሆኖባታል።

“በእነዚህ በዩናይትድ ስቴትስ በቆየሁባቸው 24 ዓመታት ስሠራ እና ግብር ስከፍል ብቆይም የመኖሪያ ፈቃዴን የምቀይርበት ሌላ መንገድ አልነበረም” ስትል ኖራ ተናግራለች።

“ወደ ኒካራጓ ስለመመለስ ማሰብ ከባድ ነው” ስትል አክላለች።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እና በምርጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ የሰጡት ሴት ልጆቿ አስፈላጊ ከሆነ አብረዋት እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

“ለእናታችን የሚያስፈልገውን ሁሉ እናደርጋለን” ብላለች የኖራ ልጅ ሊያ።