
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ መንግሥት ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ኢራን ለመግደል አሲራለች ካለው ጋር በተያያዘ ተሳታፊ ተብሎ የተጠረጠረ አፍጋኒስታናዊ ላይ ክስ መስረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር አርብ ዕለት ትራምፕን ለመግደል “እቅድ የማቅረብ” ኃላፊነት ተሰጥቶት ተሳትፏል ሲል በወነጀለው የ51 ዓመቱ ፋርሃድ ሻኬሪ ላይ የመሰረተውን ክስ ይፋ አድርጓል።
የአሜሪካ መንግሥት ሻኬሪ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ገልጾ፣ ኢራን ውስጥ ይኖራል ተብሎ እንደሚታመን ገልጿል።
በማንሃተን ፍርድ ቤት በቀረበው በዚህ የወንጀል ክስ፣ አቃቤ ሕግ በኢራን የአብዮታዊ ጥበቃ ባለስልጣን የሆነ ግለሰብ ሻኬሪ ትራምፕን እንዲሰልል እና የግድያ ዕቅድ እንዲያቀርብ በመስከረም ወር ላይ መመሪያ መስጠቱ ተብራርቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሆኑት ሜሪክ ጋርላንድ በሰጡት መግለጫ “የፍትህ መሥርያ ቤቱ የኢራንን መንግሥት አካል ላይ ክስ የመሰረተው፣ አስተዳደሩ የወንጀል ተባባሪዎችን የኢራንን የግድያ ሴራ በዒላማዎቹ ላይ፣ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ እንዲፈጽሙ በመታዘዛቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የፍትህ መሥርያ ቤቱ ኢራንን በመተቸት የሚታወቅ አሜሪካዊ ጋዜጠኛን ለመግደል ተመልምለዋል ያላቸውን ሁለት ሌሎች ግለሰቦችም ላይ ክስ መስርቷል።
በፍትህ መሥርያ ቤቱ ክስ የተመሰረተባቸው ሌሎቹ ግለሰቦች ካርሊስሌ ሪቬራ በመባል የሚታወቀው የ49 ዓመት ጎልማሳ ከብሩክሊን እና የ36 ዓመቱ ጆናቶን ሎድሆልት ከስታተን አይላንድ እንደሆኑ አብራርቷል።
ሁለቱ ሐሙስ ዕለት በኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ትራምፕ በዚህ ዓመት ሁለት የተለያዩ የግድያ ሙከራዎች አጋጥሟቸዋል።
በሐምሌ ወር ላይ አንድ ታጣቂ የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ በፔንስልቬንያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ተኩሶባቸው ጆሯቸውን ጨርፏቸዋል።
በመስከረም ወር እንዲሁ ሌላ ግለሰብ ትራምፕ በዌስት ፓልም ቢች በሚገኝ መኖርያ ቤታቸው ጎልፍ ሲጫወቱ ጦር መሳርያ በማነጠጠሩ በቁጥጥር ስር ውሏል።
- አዲሷ የትራምፕ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ማን ናቸው?8 ህዳር 2024
- በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ8 ህዳር 2024
- በእገታ እና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 121 ሰዎችን መያዙን የባሕር ዳር ፖሊስ አስታወቀ8 ህዳር 2024
አፍጋኒስታናዊው ሻኬሪ ትራምፕን በሰባት ቀናት ውስጥ የመግደል እቅድ እንዲያወጣ ተጠይቆ ነበር ሲል ያትታል በአሜሪካ አቃቤ ሕግ የቀረበው ክስ።
እንደ አቃቤ ሕግ ገለጻ፣ ሻኬሪ ትራምፕን ለመግደል በሰባት ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀሳብ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ባለስልጣናት እቅዱን ለጊዜው ገትተውታል።
አቃቤ ሕግ ሻኬሪን ጠቅሶ እንዳለው የኢራን መንግሥት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ይሸነፋሉ ብሎ በማመኑ ከምርጫው በኋላ ለመግደል መሞከር ቀላል እንደሚሆን መወሰናቸውን ገልጿል።
አቃቤ ሕግ ሻኬሪን በልጅነቱ ወደ አሜሪካ የመጣ አፍጋኒስታናዊ ዜግነት ያለው ሲል ገልጾታል። በአውሮፓውያኖቹ 2008 ለ14 ዓመታት ከስርቆት ወንጀል ጋር በተያያዘ በእስር ካሳለፈ በኋላ ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደርጓል።
አቃብያነ ሕጎች እንዳሉት የ51 ዓመቱ ጎልማሳ፣ የኢራን መንግሥት ዒላማ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ክትትል ለማድረግ በእስር ቤት የሚገኙ “የወንጀል ተባባሪዎች መረብ”ን ሪቬራ እና ሎድሆልትን የሚባሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ተጠቅሟል።
ሻኬሪ ለሪቬራ እና ሎድሆልት የኢራንን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ሙስና የዘገበውን አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ለመግደል 100 ሺህ ዶላር ቃል ለመክፈል ቃል ገብቷል ሲል አቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አመልክቷል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ጋዜጠኛ ከዚህ ቀደምም ዒላማ ተደርጎ ነበር ሲል አቃቤ ሕግ ተናግሯል።
አርብ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መቀመጫዋን ብሩክሊን ያደረገች ማሲህ አሊነጃድ የተባለች ጋዜጠኛ ኤፍቢአይ እርሷን ለመግደል ያሴሩ ሁለት ሰዎችን ማሰሩን ጽፋለች።
ገዳዮቹ ብሩክሊን በሚገኘው ቤቷ ፊት ለፊት እንደመጡ ተናግራለች።
አሊነጃድ “ወደ አሜሪካ የመጣሁት በሕግ ላይ በግልጽ የተቀመጠውን የመናገር ነፃነቴን ለመጠቀም ነው፤ መሞት አልፈልግም” ስትል ጽፋለች።
አክላም “አምባገነንነትን መዋጋት እፈልጋለሁ፤ እናም ደህንነቴ ሊጠበቅ ይገባል” ብላለች።
ከአሜሪካዊው ጋዜጠኛ እና ትራምፕ በተጨማሪ የኢራን መንግሥት በማህበራዊ ሚድያ ላይ እስራኤልን የሚደግፉ እና ኑሯቸውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረጉ ሁለት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን ነጋዴዎችን ለመግደል ማቀዱን ክሱ ያስረዳል።
ሻኬሪ ለአቃቤ ሕግ ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ በጥቅምት 2024 በስሪላንካ የእስራኤል ቱሪስቶች ላይ በጅምላ ጥቃት ለማድረስ እንዲያቅድ የኢራን አካላት እንደጠየቁት ተናግሯል።
ሻኬሪ፣ ሪቬራ እና ሎድሆልት ሁሉም የተከሰሱት ግድያ ለመፈጸም በመመልመላቸው ሲሆን ይህም የ10 ዓመት እስራት ያስቀጣቸዋል።
በተጨማሪም እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ በሚችለው ገንዘብ ለመሰወር በማሴር እንዲሁም ለግድያ ተግባር በሦስተኛ ወገን ተመልምለው በማሴር ወንጀሎችም ይቀጣሉ።