https://www.bbc.com/ws/includes/include/vjafwest/1365-2024-us-presidential-election-banner/amharic/app

የኤፍቢአይ አርማ

ከ 4 ሰአት በፊት

በመላው አሜሪካ ለሚገኙ ጥቁሮች የተላኩ ዘረኛ የጽሑፍ መልዕክቶች ላይ ምርመራ መክፈቱን የአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ቢሮ አስታወቀ።

የተላኩት የጽሑፍ መልዕክቶች በባርነት ዘመን እንደነበረው “ወደ ማሳዎች ሄደው ጥጥ ለቅመው ለጌቶቻቸው ሪፖርት” እንዲያደርጉ የሚጠቅስ ነው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የዩኒቨርስቲ ጥቁር ተማሪዎችን ጨምሮ በአላባማ፣ ሰሜን ካሮላይና፣ ቨርጂኒያ፣ ኒውዮርክ እና ፔንስልቬንያ ግዛቶች ነዋሪ የሆኑ ጥቁሮች እነዚህ የጽሑፍ መልዕክቶች ደርሷቸዋል ተብሏል።

“ኤፍቢአይ ለነዋሪዎች የተላኩትን አጸያፊ እና ዘረኛ የጽሑፍ መልዕክቶችን ያውቃል እናም በጉዳዩ ላይ ከፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከሌሎች የፌደራል ባለስልጣናት ጋር እየመከረ ነው” ብሏል የፌደራል ምርመራ ቢሮው

የጽሑፍ መልዕክቶቹ መላክ የጀመሩት አሜሪካ ካደረገችው ብሄራዊ ምርጫ ማግስት እንደሆነ ይታመናል። አንዳንድ መልዕክቶች የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ቡድንን ቢጠቅስም ቡድኑ በበኩሉ ንክኪ የለኝም ሲል ውድቅ አድርጓል።

“የምርጫ ቅስቀሳ ቡድኑ ከእነዚህ የጽሑፍ መልዕክቶች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” ሲሉ የቅስቀሳ ዘመቻው ቃል አቀባይ ስቲቨን ቼንግ ተናግረዋል።

ላኪዎቹ ያልታወቁት መልዕክቶች ምንጭ እንዲሁም አጠቃላይ የተላኩት የጽሑፍ መልዕክቶች ቁጥር እስካሁን አልታወቀም።

በኢንዲያና ግዛት የምትኖር አንዲት እናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችውን ልጇ የደረሳትን የጽሑፍ መልዕክቶች ለቢቢሲ ልካለች።

ልጅቷ “በአቅራቢያዋ በሚገኝ እርሻ ላይ ባሪያ እንድትሆን እንደተመረጠች” እና በነጭ ሚኒባስ መኪና እንደምትወሰድ እና መዳረሻዋ ላይ በጥብቁ እንደምትፈተሽ ይገልጻል።

ለደህንነቷ ስትል ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው ይህችው እናት የጽሑፍ መልዕክቶቹን እጅግ በጣም አስደንጋጭ ያለችው ሲሆን “የተጋላጭነት ስሜት” እንደፈጠረባት ገልጻለች።

ሃይሌይ ዌልች የተባለች አንዲት ተማሪ በበኩሏ ለአላባማ ዩኒቨርስቲ ጋዜጣ እሷን ጨምሮ በርካታ ጥቁር ተማሪዎች የጽሑፍ መልዕክቶቹ እንደደረሳቸው ገልጻለች።

“መጀመሪያ ላይ ቀልድ መስሎኝ ነበር በኋላ ግን ሁሉም እነዚህ የጽሑፍ መልዕክቶች እየደረሳቸው እንደሆነ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያጋሩ ጀመር። በጣም ነው ያስጨነቀኝ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ስላልገባኝ አስፈራኝ” ስትል ክሪምሰን ዋይት ለተሰኘው ጋዜጣ ገልጻለች።

የጽሑፍ መልዕክቶቹ ላይ ያሉት ቃላቶች እና አገላለጾች ቢለያዩም በአጠቃላይ ግን ጥቁሮች ወደ ማሳዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ በመኪና ለመወሰድ እንዲጠብቁ እና የባሪያ ጉልበትን የሚጠቅሱ ናቸው።

የጽሑፍ መልዕክቶቹ የተላኩት ቢያንስ ከ25 የተለያዩ ግዛቶች እንደሆነ የአካባቢው መለያ ቁጥሮች ማሳያታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።