
ከ 5 ሰአት በፊት
የቴአትር ባለሙያው ጋሽ ተስፋዬ ገሰሰ በ1989 “ዑመር ኻያም ልብወለዳዊ ታሪኩና ሩብያቶቹ” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሃፍ መታሰቢያ ያደረጉት ለተማሪ ቤት ወዳጆቻቸው ነው።
መጽሃፉ መታሰቢያ የተደረገላቸው የጋሽ ተስፋዬ ወዳጆች ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፣ ሰሎሞን ዴሬሳ እና ዓምደ ሚካኤል ኃብቴ ናቸው።
ስብሃት፣ ሰሎሞን እና ተስፋዬ የሚተዋወቁት አፍላ ወጣቶች ሳሉ ነው።በጊዜው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ይባል የነበረው ተማሪ ቤት ውስጥ።
ሶስቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የተወለዱ ዘመነኞች ነበሩ። ሰሎሞን ከወለጋ፣ ስብሃት ከአድዋ፣ ተስፋዬ ከሀረር መጥተው የተወዳጁት አዲስ አበባ ነው።
ሰሎሞን ዴሬሳ በአንድ ወቅት “ስብሃት፣ ተስፋዬ እና እኔ የጻፍነውን አንዱ ለሁለቱ ያነባል።ጓደኛሞች ነበርን በጣም” ብሎ ነበር።
“እነሱም ሌሎች ጓደኞች ነበሯቸው።እኔም ሌሎች ጓደኞች ነበሩኝ” የሚለው ሰሎሞን “በጽሁፍ የምንገናኘው ግን እኛ ነበርን፤ መጽሃፍ ደግሞ አብረን እናነብ ነበር” ሲል የአፍላነታቸውን ዘመን ያስታውሳል።
ጽሁፍ ያወዳጃቸው ሰለስቱ (ሶስቱ) ወጣቶች ኋላ ላይም በኢትዮጵያ ስነ ጥበብ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው። ጋሽ ሰለሞን ባሳተማቸው ሁለት የግጥም መድብሎች በኢትዮጵያ ስነ ግጥም ውስጥ ተደጋግሞ ስሙ ይነሳል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ ጽሁፍ ውስጥ የስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ረዥም እና አጫጭር ልብ ወለዶች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትርን ያለ ተስፋዬ ማሰብ የማይቻል ነው።
ጋሽ ተስፋዬ ገሰስ ይህን ወዳጅነት እና ጓደኝነት አስታውሰው ነው፤ “ላሳለፍነው የአ.አ.ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የትምህርት ዘመናችንና ጓደኝነታችን” ሲሉ መጽሃፋቸውን ለጉርምስና ዘመን ወዳጆቻቸው መታሰቢያ ያደረጉት።
መጽሃፍን እና ሌላ የስነ ጥበብ ስራን መታሰቢያ፣ ማስታወሻ ፣ መዘከሪያ ማድረግ እንዲሁም የከረመ ብሂል ነው።
ማርሊን ዋግማን ጌለር የተባለች ደራሲ “Once again to Zelda” በሚለው መጽሃፏ “ሥነ ጽሑፋዊ አበርክቶዎች መነሻቸው በ18ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን ታወሳለች።
“ማራኪ” ስትል ከጠራቻቸው ሥነ ጹሁፋዊ አበርክቶዎች ጀርባ ያለውን ታሪክ ባጠናችበት በዚህ መጽሃፏ ማርሊን ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ አበርክቶዎች በሐብታም ባለሟሎች ዘንድ ሞገስ ለማግኘት የሚደረጉ ሙከራዎች ነበሩ ትላለች።
ባለፉት መቶ ዓመታት ግን ይህ ተቀይሯል። አበርክቶዎች ይበልጥ ግላዊ እየሆኑ መጥተዋል። ተደራሲው በአበርክቶዎች አጮልቆ ደራሲው/ዋ ግድ የሚሏቸውን ነገሮች ይገነዘባል።
ለማርሊን የአብርክቶዎች የጋራ መለያ አንባቢዎችን ወደ ደራሲው/ዋ የግል ህይወት መጋበዛቸው ነው። አበርክቶዎች ለደራሲው/ዋ ዋጋ ያላቸውን ሰዎች፣ ነገሮች ያሳያሉ።
በአማርኛ ስነ ጽሁፍ ውስጥ “መታሰቢያ”፣ “ማስታወሻ”፣ “አበርክቶ”፣ “መዘክር” በሚሉ ቃላት ይገለጻል። ኢትዮጵያውን ጸሃፍት እነዚህን አገላለጾች እያፈራረቁ ይጠቀሟቸዋል። በእንግሊዝኛ በሚጻፉ መጻህፍት ግን “Dedication” ተብሎ ይቀመጣል።
አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ገለጻዎች ሳይኖሩም መጻህፍት “ለእገሌ፣ ለእገሊት፥ ለእነ እገሌ….” ተብለው ይበረከታሉ።
ሁለት የግጥም መድብሎች እና አንድ ረዥም ልብወለድ የጻፈው ደሱ ፍቅርኤል “መታሰቢያ”፣ “ማስታወሻ”፣ “አበርክቶ” የሚሉት አገላለጾች ለእሱ የተለያዩ ናቸው መሆናቸው ይገልጻል።
ለደሱ አበርክቶ በዋናነት በህይወት ላሉ ሰዎች የሚበረከት ገጸ በረከት ነው። መታሰቢያ ደግሞ በህይወት ለሌሉ ሰዎች ለስማቸው መጠሪያ ለስራቸው ማስታወሻ የሚቀመጥ ነው። ሐውልት እንደማቆም አይነት።
የፎክሎር ባለሙያ እና ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በየትኛውም ገላጭ ቢቀመጥ “ብዙ ጊዜ በህይወት ለሌለ ሰው እንዲነሳ እንዲታወስ እንዲዘከር ያለህን ፍቅር ያለህን ክብር የምትገልጽበት አንዱ መንገድ ነው” ይላል።
በኢትዮጵያ ሥነ ጽሁፍ መጻህፍትን ለቤተሰብ አባላት፣ ለትዳር አጋር፣ለጓደኛ እና ወዳጅ ማበርከት ይዘወተራል።
ደራሲዎች በዚህ ገጽ መጽሃፉ ከተበረከተላቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን ዝምድና ይገልጻሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ስሙ ሌጣውን ይቀመጣል።
ስም ብቻውን ሲቀመጥ በተደራሲ ዘንድ “እገሌ አባባሉ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ያጭራል።
ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት የአበርክቶ ገጹን አልፎ ትንሽ መራመድ ደራሲውን/ዋን አሊያም የቅርብ ወዳጆቻቸው መጠየቅ ያሻል።
- “የመሻገር ሲቃ ከጻፍኳቸው መጻሕፍት ሁሉ በጣም የተሻለ እና እኔንም የሰራኝ መጽሐፍ ነው” ደራሲ እና ሃያሲ ያዕቆብ31 ታህሳስ 2023
- በዋጋ መናር ምክንያት የኢትዮጵያ ፀሐፊያን ሥራዎች የሕትመት ብርሃንን ላያዩ ይሆን?2 ሀምሌ 2023
- ‘የጠፉ መጽሐፍት አዳኙ’ ኤልያስ ሜክሲኮን እስከ ወዲያኛው ይሰናበታት ይሆን?10 ታህሳስ 2023

ከደሱ ፍቅርኤል መጽሃፍት አንዱን እንምዘዝ። እጁን ያፍታታው በ2010 ዓ.ም ባሳተማት በግጥም መድብል ነው።
ደሱ መታሰቢያ ገጹ ላይ ስለሚያሰፍረው ነገር “በደንብ አስባለሁ” ይላል። “ሀገሬን ሰቀሏት” የሚል ርዕስ የሰጣትን መድበል መታሰቢያ ያደረገው ለቢትወደድ ሐብቱ ላቀው ነው።
ቢትወደድ ሐብቱ የደሱ አጎት ነበሩ። “አጎቴ ለእኔ ህይወት መሰረት ነው” የሚለው ደሱ፤ “ብዙ ነገር ያስተማረኝ እሱ ነው” ሲል ቢትወደድ ሐብቱ በእሱ ህይወት ያላቸውን ሚና ይገልጻል።
ደሱ ያደገው እሳቸው ጋር ነው። ቢትወደድ ሐብቱ ህይወታቸው ሲያልፍ ደሱ የ15 ዓመት ልጅ ነበር። የእሳቸው ማለፍ ደሱን ወደ ሥነ ጽሁፍ ገፋው። “የእሱ ሞት በፈጠረብኝ የልብ ክፍተት ምክንያት ነው ወደ ድርሰትም ሥነ ጽሁፍም በደንብ የገባሁት” ይላል።
ለዚህም የመጀመሪያ ሥራውን ለእሳቸው ሥም መጠሪያ እንዲሆን አብርክቶታል። አለት ጠርቦ ሳይሆን ቃላት ሰካክቶ መታሰቢያ ሐውልት አቆመላቸው።
መታሰቢያ/አበርክቶ ግን ለቤተሰብ ብቻ አይደለም የሚሰጠው።
ደራሲዎች በአካል ለማያውቋቸው፣ በዐይነ ስጋ አይተዋቸው፤ ድምጻቸውን ሰምተዋቸው ለማያውቁ ሰዎች ስራዎቻቸውን ያበረክታሉ።
ዶ/ር እንዳለጌታ ለመጀመሪያ ጊዜ አንብቦ የጨረሰው ልብ ወለድ የብርሃኑ ዘርይሁንን “የእንባ ደብዳቤዎች” ነው። የእንባ ደብዳቤዎች ብርሃኑ ዘርይሁን “ከውጨኛው ዓለም ኑሮ ጋር በሚገባ ሳይተዋወቅ የአጻጻፍ ልምምድ ሳይኖረው ከትምህርት ቤት በወጣ ማግስት” የጻፈው የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው።
እንዳለጌታ “[ብርሃኑ] በበቂ ሁኔታ ስራዎቹ አልተጠኑም አልተመረመሩም ብዬ ስለማስብ እኔ ውስጥም የፈጠረብኝ ትጋት እና ንቃት ከፍተኛ ስለሆነ መጽሃፌን ማስታወሻነቱን ለምን ለእሱ አላደርገውም አልኩኝ” ይላል።
ብርሃኑ እና እንዳጌታ የተለያየ ዘመን ሰዎች ናቸው። እንዳለም“እኔ ብርሃኑ ዘርይሁንን አላውቀውም በአካል አልደረስኩበትም ግን ስራዎቹን አንብቤያለሁ” ሲል ያክላል።
ሌሎች ደራሲዎችም መጽሃፋቸውን በአካል ለማያውቋቸው ነገር ግን ሥራዎቻቸው ተጽዕኖ ላሳደሩባቸው አሊያም በጥሩ ሁኔታ ለሞረዷቸው ሌሎች ጸሐፍት መታሰቢያ ያደርጋሉ።
ሀብታሙ አለባቸው የኢትዮጵያን አገር መንግስት ግንባታ የፈተሸበትን “ታላቁ ተቃርኖ” የሚለውን መጽሃፉን ያበረከተው ለገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ነው።
ገብረ ሕይወት እና ሀብታሙ የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው። ገብረ ሕይወት “መንግስት እና የሕዝብ አስተዳደር”ን ሲጽፉ ኢትዮጵያን የሚመሩት ፊውዳሎች ነበሩ።ሀብታሙ መጽሃፉን ሲያሳትም አብዮታዊ ዲሞክራቶቹ ኢህአዴጎች ኢትዮጵያን ይመሩ ነበር።

ደሱ ፍቅርኤል በቅርቡ ያሳተመውን ልብ ወለድ መታሰቢያነት ያደረገው በአካል ለማያውቃቸው ሰዎች ነው።
“እስከ መቅደላ” የተሰኘው መጽሃፍ መታሰቢያነት ለእቴጌ ተዋበች አሊ፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋሪያት እና ለአቶ ገሪማ ታፈረ ነው።
እቴጌ ተዋበች የአጼ ቴዎድሮስ ሚስት ፤ ደጃዝማች ታከለ የታወቁ አርብኛ፤ አቶ ገሪማ ታፈረ ደግሞ የእውቁ የፊልም ባለሙያ ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ ወላጅ አባት እና የታሪክ ባለሙያ ናቸው።
ደሱ መጽሃፉን ለሶስቱ ሰዎች መታሰቢያ ያደረገው “የእነዚህ ሶስት ሰዎች መንፈስ መጽሀፉ ውስጥ አለ ብዬ ስለማምን ነው” ሲል ይገልጻል።
ዶ/ር እንዳለጌታ “መታሰቢያ የሚደረግላቸው ሰዎች አስተምህሯቸው መታሰቢያ ከተደረገላቸው መጽሃፍ ጋር ሊዛመድ ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፈጽሞ እሱን ላይመስል ይችላል” ይላል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መጻህፍት ለቡድኖች፣ ለትውልድ፣ ለባለሙያዎች ይበረከታሉ። በዚህን ጊዜ የመጽሃፉ ይዘት አሊያም ደራሲ ከተበረከታለቸው ሰዎች ጋር ይዛመዳል። ፖለቲከኞች የሚጽፏቸውን መጽሃፎቻቸው ለፖለቲካ ጓዶቻቸው፣ ለትግል አጋሮቻቸው እንደ መታሰቢያ ያበረክታሉ።
በ“ ያ ትውልድ” አሊያም ስለ “ያ ትውልድ” የተጻፉ መጽሃፎች ለዚህ ማሳያ ናቸው።
ታደለች ኃይለ ሚካኤል “ዳኛው ማነው?” የሚለው መጽሃፏና መታሰቢያነት ያደረገችው ለትዳር አጋሯ ብርሃነመስቀል ረዳ እና “በእምነት እና ቆራጥነት በኢህአፓ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈው ለተሰዉ” ነው።
የኢህአፓ መስራች አባሉ ብርሃነመስቀል ረዳ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበረው።
ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ “ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ” የተሰኘውን ግለ ታሪካቸውን ማስታወሻ እንዲሆን ያበረከቱት፤ “የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ብሎም ለማዳበር ለሚጥሩ. . . በማስተማር ላይ ለተሰማሩ” ነው።
የሥነ ሕይወት ሊቁ ፕሮፌሰር ሽብሩ ሙሉ ዘመናቸውን ያሳለፉት በማስተማር እና በምርምር ላይ ነው። ለዚህም ነው መጽሃፋቸውን እሳቸውን ለሚመስሉ መምህራን ማስታወሻ እንዲሆን ያበረከቱት።
15 መጽሃፍቶችን የደረሰው እንዳለጌታ ከበደ የመጽሃፍ አበርክቶ ሲያሰፍር እነዛን ሰዎች “እንዴት እንደምወዳቸው፣ እንደማከብራቸው እኔ ውስጥ የጫሩት እሳት እንዴት የመንፈስ ግለት እንደፈጠረብኝ ለማሳየትም ጭምር ነው” ይላል።
አበርክቶ፣ ማስታወሻ ወይም መታሰቢያ “እንዳንዴ ከዋናው ታሪክ ጋር ይገናኛል፤ አንዳንዴ ደግሞ ላይገናኝም ይችላል” የሚለው እንዳለጌታ፤ “ትልቁ ነገር ግን ከበሬታ ያልሰጠኸውን ሰው ማስታወሻ አታኖርለትም” ባይ ነው።