
ከ 5 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ በስድስት ወር ውስጥ ብቻ በጋዛ ጦርነት ከተገደሉት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸው ማረጋገጡን ጠቅሶ አውግዟል።
ኤጀንሲው የሟቾች ቁጥሩ እንዲህ በከፍተኛ ሁሌታ ሊያሻቅብ የቻለው እስራኤል ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሰፊ ጉዳት የሚያደርስ የጦር መሳሪያ በመጠቀሟ እንዲሁም የተወሰኑ ሞቶች ደግሞ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች የሚያስወነጭፏቸው መሳርያዎች ላይ ባጋጠመ ችግር በደረሱ ፍንዳታዎች ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
ሪፖርቱ “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ” የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን እንዳስተዋለ ገልጾ፣ ይህም “የጦርነት እና ሌሎች የጭካኔ ወንጀሎች” ስጋት ፈጥሯል ብሏል።
እስራኤል ከዚህ ቀደም የሐማስ ታጣቂዎችን ዒላማ ማድረጓን እና ትክክለኛ ዒላማዎችን በመለየት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ገልጻ ነበር።
ቢቢሲ አርብ ዕለት በወጣው በዚህ ሪፖርት ላይ ምላሽ ለማግኘት የእስራኤል መከላከያ ሰራዊትን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሕዳር 2023 እስከ ሚያዝያ 2024 ድረስ በጋዛ 8,119 ሰዎች መገደላቸውን በመረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህ ጥናት መሞታቸው በማስረጃ ከተረጋገጠ ግለሰቦች መካከል 44% ያህሉ ሕጻናት እና 26%ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ከሟቾች መካከል እድሜያቸው ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት እድሜ ያላቸው በርካታ ሕጻናት ተገኝተዋል።
80 በመቶ ያህሉ ሟቾች የተገደሉት በመኖሪያ ሕንጻዎች ወይም መጠለያ ቤቶች ነው ሲል ኤጀንሲው አክሎ ገልጿል።
በሪፖርቱ የተሰበሰበው መረጃ “ለንጹኃን ዜጎች ሞት ቸልተኝነት፣ ጥቅም ላይ የዋሉ መሳርያዎች እና የውግያ ስልቶች” አስተዋጽኦ እንዳላቸው አሳይቷል።
- በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ8 ህዳር 2024
- አዲሷ የትራምፕ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ማን ናቸው?8 ህዳር 2024
- ቼልሲ ከአርሰናል – ማን ያሸንፋል? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ውጤት ግምት8 ህዳር 2024
የተባበሩት መንግሥታት አስተማማኝ መረጃ ነው ሲል የሚገልጸው በጋዛ የሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ባለፉት 13 ወራት ውስጥ ከ43,300 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያሳያል።
በጋዛ በርካታ አስከሬኖች በቦምብ በፈራረሱ ሕንፃዎች ሥር ተቀብረው እንደሚገኙ ይታመናል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለተገደሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ መረጃ ማግኘቱን ጠቅሶ፣ የሕጻናት ሟቾች ቁጥር ከሦስቱ ውስጥ አንዱን እንደሚይዙ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ በሰጡት መግለጫ “ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የሰላማዊ ዜጎች ግድያ እና ጉዳት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ መሰረታዊ መርሆችን ባለማክበር የመጣ ቀጥተኛ ውጤት ነው” ብለዋል።
ኃላፊው ዓለም አቀፍ ሕግን ጠቅሰው፣ ተፋላሚ ወገኖች ተዋጊዎችንና ሰላማዊ ዜጎችን እንዲለዩ፣ ተመጣጣኝነት፣ ወታደራዊ ጠቀሜታ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር ተለይቶ መመዘን እንዳለባቸው እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ዘርዝረዋል።
ቱርክ “በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ከባድ ጥሰት ተፈጽሟል የሚለውን ውንጀላ ተከትሎ ተገቢው ግምት” እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቀደም ሲል ለቀረበበት ክስ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ” ሁሌም እንደምናደርገው በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት እርምጃችን ይቀጥላል” ሲል ገልጾ ነበር።

ሪፖርቱ በተጨማሪም ተፋላሚ ወገኖች በጋዛ ያለውን ግጭት ያካሄዱበት መንገድ “አሰቃቂ የሰው ልጅ ስቃይን አስከትሏል” ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ሕዝብ ከሚበዛባቸው አካባቢዎች ጦርነት መክፈታቸውን፣ ያለምንም ልዩነት የሚወነጨፉ መሳርያዎች መጠቀማቸው ለሟቾች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ሰላማዊ ዜጎች የሚጠቀሙባቸውን መሠረተ ልማቶችን በማውደም “ብዙዎች በሕይወት ያሉ እና የቆሰሉ ዜጎችን እንዲፈናቀሉ ያለምንም በቂ ውሃ፣ ምግብ ወይም የጤና እንክብካቤ እንዲራቡ አድርጓል” ብሏል።
ይህ ሁኔታ በሰሜን ጋዛ እጅግ የከፋ ነው ያለው ሪፖርቱ የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚገልጹት አካባቢው እስራኤል በሐማስ ላይ አዲስ የምድር ጥቃት ከከፈተበት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በእስራኤል ከበባ ውስጥ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጥቅምት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ ወደ ሰሜን ጋዛ አለመግባቱን ማስታወቁን ተከትሎ አሜሪካ ለእስራኤል ማስጠንቀቅያ ሰጥታ ነበር።
በወቅቱ አሜሪካ እስራኤል እስከ ሕዳር 12 ድረስ ወደ ስፍራው የሚገባውን እርዳታ የማትጨምር ከሆነ የወታደራዊ ድጋፍ ልታጣ እንደምትችል ነበር ማስጠንቀቅያ የሰጠችው።
የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል የእርዳታ ድርጅት ኃላፊ ያን ኤጌላንድ አርብ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቅርብ ጊዜ በጋዛ ባደረጉት ጉብኝት ላይ “ሊያምኑት ከሚችሉት በላይ የሆነ ውድመት እና ተስፋ መቁረጥ” ማየታቸውን ገልጸዋል።
“ያልወደመ ሕንፃ ማግኘት አይታሰብም። ሰፊ ቦታ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የነበረውን ስታሊንግራድን ይመስላል። ይህ ያለገደብ የሚፈጸም የቦምብ ጥቃት በዚህ መላወሻ ባጣው ሕዝብ ላይ ምን ያህል ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ መገመት አይቻልም” ብለዋል።
“ለዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉት በመጀመሪያ ደረጃ ሕጻናትና ሴቶች መሆናቸው ግልፅ ነው” ሲሉም አክለዋል።
መስከረም 26፣ 2016 ዓ.ም. የሐማስ ጦር በእስራኤል 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ታጋቾችን ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።