የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ማኅበራዊ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሁሉም ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ መስፋፋቱ ተገለጸ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: November 10, 2024

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሁሉም ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። 

በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ ያደረገው ቋሚ ኮሚቴው፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ በክልሉ በሚገኙ 67 ወረዳዎች ወረርሽኙ መከሰቱን አረጋግጧል። በ34 ወረዳዎች ሥርጭቱ የከፋ መሆኑም ታውቋል። 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር)፣ የወባ በሽታ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ የሚተላለፍበት ወቅትን አስቀድሞ ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፣ ይህ  ባይሆን ኖሮ ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችል ነበር ብለዋል።

‹‹በተመረጡ ከፍተኛ የወባ በሽታ ጫና ያለባቸው 222 ወረዳዎች ባለፉት ወራት በሚገባ እየተሠራ ነው። የመቀነስ አዝማሚያ ያሳየባቸው አካባቢዎች አሉ። እነዚህ አካባቢዎች የበሽታው ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ በሚጨምርባቸው ወራት ታሳቢ ያደረጉ ዕቅዶች እስከ ቀበሌ ድረስ እየተሠራበት ነው ያለው፤›› ብለዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንዱ ወረዳ ከሌላው ወረዳ መጠኑ የተለያየ ቢሆንም፣ በሁሉም አካባቢዎች ሥርጭቱ ተስፋፍቷል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል ካለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድጋፎችን ለማዳረስ ከባድ እንደሆነና ባለፉት ወራት በተከታታይ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እነዚህን ሁኔታዎች እያስተናገደ ስላለበት ሁኔታ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ሁሉንም የፖለቲካ አመራር፣ የጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ባካተቱ የመከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች አገር አቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር የምላሽ ሥራውን ያስጀመርነው፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሚዛን አማን ከተማ ውስጥ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አፈጻጸሙ በየሳምንቱ እየተገመገመ በየወረዳው የምላሽ ሥራውን የሚያስተባብሩ ቡድኖች ተቋቁመው እየሠራን ነው፤›› ብለዋል። 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ፣ ‹‹የክልሉ ጤና ቢሮና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ ንቅናቄ ፈጥረው ጤና ጣቢያን ማዕከል ያደረጉ የምላሽ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ከሁሉም ወረዳወዎች መረጃ እያገኘን ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ነው እኛ ዘንድ ያለው መረጃ የሚያሳየው፤›› ሲሉም አስረድተዋል። 

የወባ በሽታን ሥርጭት ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል የሚያስችል በጀት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢንስቲትዩቱና ከአጋር አካላት በየደረጃው ላለው መዋቅር እየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ኢንስቲትዩቱ ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ባለሙያዎች አሰማርቶ ብሔራዊ ዕቅድ በማውጣት፣ የምላሽ መስጫ ሥርዓት ለመዘርጋት በየደረጃው እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።