

ጌታሁን ታረቀኝ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር ፕሬዚዳንት
ማኅበራዊ በኢትዮጵያ 1.9 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር ይኖራሉ ተባለ
ቀን: November 13, 2024
በኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝና 1.9 ሚሊዮን ሰዎች ከበሽታው ጋር የሚኖሩ መሆናቸው ተነገረ።
የጤና ሚኒስቴር ስለ ስኳር ሕመም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው የግንዛቤ መድረክ ላይ፣ ሕመሙ ወረርሽኝ በሚመስል ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ በመሠራጨት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ፣ የስኳርና የሆርሞኖች ክፍል ስፔሻሊስት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር ፕሬዚዳንት ጌታሁን ታረቀኝ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ 3.3 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር፣ 9.9 በመቶ ሰዎች ከቅድመ ስኳር ሕመም ጋር የሚኖሩ ናቸው።
የስኳር ሕመም የሚከሰተው በደም ውስጥ ያለው ስኳር/ግሉኮስ/ ሲጨምር መሆኑን በመድረኩ ላይ፣ ይህም ዓይነ ሥውርነትን፣ የኩላሊት ሥራ ማቆምን፣ የልብ ችግር፣ ስትሮክ፣ የእግር መቆረጥና የመገጣጠሚያ ችግሮችን እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡
በዓለም የስኳር ሕመም በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ በስኳር ሕመም ላይ የሚሠራው የኢንተርናሽናል ዳያቤትስ ፌዴሬሽን መረጃ ያሳያል፡፡ ፌዴሬሽኑ እ.ኤ.አ. በ2021 ባወጣው መረጃ መሠረት 537 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ 541 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ቅድመ ስኳር (ወደ ስኳር ሕመም የሚሄድ፣ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ከ100 – 125 ባለው መጠን የሚገኝበት) ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
እንደ ጌታሁን (ዶ/ር)፣ በስኳር ሕመም ከተጠቁ ከአራቱ ሰዎች ሦስቱ በማደግ ላይ ባሉና ባላደጉ አገሮች የሚገኙ ናቸው። በአፍሪካ አራት ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር ይኖራሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ እ.ኤ.አ. በ2045 ይህ አኃዝ ወደ 55 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።
በየዓመቱ 6.7 ሚሊዮን ሰዎች በስኳር ሕመም እንደሚሞቱ፣ 960 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሀብት ከስኳር ሕመም ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የሚወጣ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ በፋብሪካ የተዘጋጁና ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች አዘውትሮ መጠቀም፣ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት፣ አልኮል ማዘውተር፣ ሲጋራ ማጨስና የሰውነት ውፍረት መጨመር፣ ለስኳር ሕመም ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጌታሁን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የተለያዩ የስኳር ዓይነቶች አሉ። ‹‹ዓይነት አንድ›› የሚባለው የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በሕፃናት ላይ የሚከሰትና ቆሽት የተባለ አካል ኢንሱሊን ማምረት ሲያቆም ነው።
‹‹ዓይነት ሁለት›› የሚባለው ከ90 እስከ 95 በመቶ ያህሉ በመካከለኛ ዕድሜ ክልልና ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው። ይህም ቆሽት በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሳይችል ሲቀር የሚመጣ ነው።
‹‹ዓይነት ሦስት›› የሚባለው የስኳር በሽታ በነፍሰ ጡሮች ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
80 በመቶ የስኳር ሕመምን ቀድሞ በሚደረግ ምርመራ መከላከል ይቻላል የሚሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ውፍረት መቀነስ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል አለመጠጣትና ሌሎችም በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ኅዳር 5 ቀን የሚከበረው የዓለም የስኳር ቀን የዘንድሮ መሪ ቃል ‹‹መሠናክሎችን መቅረፍ ክፍተቶችን መሙላት›› (Breaking Barriers Bridging Gaps) ነው፡፡
በዚህም መሠረት በቀኑ የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስና እያንዳንዱ በስኳር በሽታ የተያዘ ማንኛውም ሰው ፍትሐዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ተመጣጣኝና ጥራት ያለው ሕክምናና ክብካቤ እንዲያገኝ ትኩረት ይደረግበታል፡፡
የዓለም የስኳር ቀን በኢንተርናሽናል ዳያቤትስ ፌዴሬሽንና የዓለም ጤና ድርጅት የተፈጠረው እ.ኤ.አ. በ1995 ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም አቀፍ ቀንነት ዕውቅና የሰጠው በ2006 ነበር፡፡ ኖቬምበር 14 (ኅዳር 5 በየአራት ዓመቱ ኅዳር 4) ቀን የተመረጠው ደግሞ ኢንሱሊን ያገኙት ሳይንቲስት ስር ፍሬድሪክ ባንቲንግ የተወለዱበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡
