November 15, 2024 – Konjit Sitotaw
በአዲስ አበባ በሚገኙ መድሃኒት ቤቶች የስኳር በሽታ መድሃኒት የሆነው ኢንሱሊን እጥረት መኖሩን የመድሃኒት ቤት ባለቤቶችና እና ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢንሱሊን ያሉ መሰረታዊ የስኳር መድሃኒቶች እጥረት መኖር እንደማይገባው በመግለጽ አሁን ላይ እጥረት ከሚስተዋልባቸው መድሃኒቶች አንዱ መሆኑን የከነማ መድሃኒት ቤት ቁጥር አስራ አራት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ታደሰ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡
በብዛት ከሚሸጡ የስኳር መድሃኒት አይነቶች ዋነኛው የሆነው ኢንሱሊን ከተፈላጊነቱ አንጻር ቶሎ እንደሚያልቅ እና መድሃኒት ቤቶች ምርቱን ሲጠይቁ በቶሎ እንደማይቀርብላቸው ይህ አይነቱ አሰራር ሊቀረፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በመርፌ የሚወሰዱት የበሽታው መድሃኒቶች ለውስን ሰአት በፍሪጅ የሚቀመጡ በመሆናቸው በተፈለገው ሰዓት ሁሉ በቂ አቅርቦት ሊኖርና በፍጥነትም አገልግሎት ላይ መዋል እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
አንዳንዴም ምርቱ እያለ እጥረት ያጋጥማል ይህም የግዢ ሰንሰለቱ ጤናማ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው አሁን ላይ ኢንሱሊንን ጨምሮ ሁሉም አይነት የስኳር መድሃኒት በበቂ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
መንግስት የስኳር መድሃኒትን በከነማ መድሃኒት ቤቶች በበቂ ሁኔታ አቅርቧል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የግል መድሃኒት አቅራቢዎችም ሆኑ መሸጫ መደብሮች በውድ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ሲባል እንደማይሰራጭላቸው አስታውቀዋል።
የግል መደብሮች የአገልግሎት አቅራቢውን አርማ በመጠቀም በውድ የሚያቀርቡ እንዳሉና ይህን ባደረጉት ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ዶ/ር አብዱልቃድር ገልጸዋል።
