

በሶማሊያ ተሰማርቶ የቆየው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል
November 17, 2024
ታኅሳስ መገባደጃ 1999 ዓ.ም. የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለኢፌዴሪ ፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱን ያረጋገጠ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ሪፖርት በተሰማ ዕለት ደግሞ በፓርላማው የጦፈ ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ ቡልቻ ደመቅሳ፣ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ወዘተ የመሳሰሉ ጉምቱ ፖለቲከኞች የነበሩበት የዚያን ጊዜ ፓርላማ የኢትዮጵያን ጦር በሶማሊያ መሰማራት በሁለት መንገዶች ነበር የተቀበለው፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች በወራሪነት ስሟ ተጠርቶ የማያውቀው ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሌላ አገር መላኳ ይህን የቆየ ነባር መልካም ገጽታዋን የማያጠለሽ ነው በሚል ተቃወሙት፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላም መጠበቅ በሚል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በደገፈው የኮሪያ፣ የኮንጎና የላይቤሪያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ካልሆነ በስተቀር በተናጠል በሌላ አገር ጦር ያዘመተችበት አጋጣሚ አለመኖሩን በማጣቀስ፣ ጦሯን ወደ ሶማሊያ መላኳ ዓለም አቀፍ ውግዘትና የግንኙነት መሻከር ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ሞግተው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በጊዜው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ተወካይ የነበሩት እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉ ፖለቲከኞች ግን ጉዳዩን ደግፈውት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ አደጋ የደቀነ የሃይማኖት አክራሪነት በሶማሊያ እየበቀለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን የሽብር አደጋ ሰለባ እንድትሆን የሚያደርግ መሆኑን በመጠቆም ነበር ኢትዮጵያ ራሷን ቀድማ ለመከላከል ስትል ጦሯን ማስገባቷን እንደሚደግፉት የተናገሩት፡፡
በጊዜው በኢትዮጵያ ላይ ጂሀድ እስከ ማወጅ የደረሰ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የተባለ ቡድን በሞቃዲሾ እየተጠናከረ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ተጨባጭ አደጋ (Clear and Present Danger) የደቀነ መሆኑን፣ እንዲህ ባለው ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ሥጋቱን አስቀድሞ የሚቀልብስ ዕርምጃ ለመውሰድ ዓለም አቀፉ ሕግም ሆነ አሠራር እንደማይከለክላት በማስታወስ ነበር አቶ መለስ የዘመቻውን ተገቢነት የሞገቱት፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ያደረገው ዘመቻም ግፋ ቢል ከሦስት ሳምንት አለፍ ካለም በአንደ ወር የሚጠናቀቅና የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን አከርካሪ የመስበር ዓላማ ብቻ እንዳለው በመግለጽ፣ ፓርላማው የመንግሥታቸውን ውሳኔ እንዲደግፍ ለማሳመን አቶ መለስ ከፍተኛ አድርገው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የገባው ሕግን ተከትሎና የሶማሊያ መንግሥትን ግብዣ አግኝቶ ነው የሚለው ጉዳይም ሌላው ማሳመኛ ሆኖ ነበር፡፡
በቀጣይ ቀናት ስለዚሁ ጉዳይ ለአልጄዚራው መሐመድ አዶ ማብሪሪያ የሰጡት አቶ መለስ፣ ተልዕኮው ግፋ ቢል በጥቂት ሳምንታትና ወራት እንደሚጠናቀቅና ኢትዮጵያም የጂሃድ ጦርነት የከፈተውን ኃይል ከመደምሰስ ውጪ በሶማሊያ የመቆየት አንዳችም ፍላጎት እንደሌላት ተከራክረው ነበር፡፡ አቶ መለስ ይህን በሚሉበት ወቅት ግን የወቅቱ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ መሐመድ ጌዲ ግን የኢትዮጵያን ጦር ለወራት እንደሚቆይ፣ አስተማማኝ የፀጥታ ኃይል ለሌለው የሶማሊያ መንግሥትም ጥበቃ እንደሚያደርግ ሲገልጹ ተደምጠው ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ መለስ ዜናዊ ከአልጄዚራው መሐመድ አዶ ጋር በድጋሚ ለቃለ መጠይቅ ተገናኙ፡፡ ‹‹ክቡርነትዎ ያኔ የአገርዎን ጦር ወደ ሶማሊያ ሲያስገቡ በጥቂት ሳምንታት ግፋ ቢልም በወር ተልዕኮውን አጠናቆ ይወጣል ብለው ገልጸውልን ነበር፡፡ ያሉትን ሲፈጽሙ ግን አላየንም፡፡ አሁንስ መቼ ነው እንወጣለን የምትሉት?›› የሚል ጥያቄ ጋዜጠኛው አነሳላቸው፡፡ መለስ ለዚህ መልስ ሲሰጡም፣ ‹‹ያኔ በጥቂት ጊዜ እንወጣለን ብዬ ግምት በመናገሬ ስህተት ሠርቼያለሁ፡፡ አሁንም በዚህ ጊዜ እንወጣለን ብዬ ድጋሚ ስህተት አልሠራም፡፡ ዋናው ተልዕኳችን በሶማሊያ ሰላም መፍጠርና የተረጋጋ መንግሥት እንዲመሠረት ማድረግ በመሆኑ እሱን እንዳሳካን ለቀን እንወጣለን፤›› በማለት ነበር በጊዜው የተናገሩት፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ 17 ዓመታት አለፉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት መካከል አቶ መለስ ዜናዊ በሞት ከመለየታቸው በስተቀር እንደተገመተው በሶማሊያ ሰላም አልሰፈነም፡፡ እንዲሁም የተረጋጋ ጠንካራ መንግሥታዊ ሥርዓት አልተፈጠረም፡፡ ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ካስገባች በኋላ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የተባለው ኃይል ተበታትኗል፡፡ ይሁን እንጂ በቦታው እንደ አልሸባብ ዓይነት የበለጠ ጦረኛ የሆነ፣ በሽብርና በደፈጣ ጥቃቶቹ ከሶማሊያ አልፎ ጎረቤት አገሮችን በእጅጉ ሥጋት ላይ የጣለ ኃይል ተተክቷል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን በመላኳ ምን አተረፈች ሲሉ አንዳንዶች ይጠይቃሉ፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የቀጣናው ሰላም እንደ አልሸባብ ያሉ ኃይሎች በመፈጠራቸው የተነሳ የሥጋት ደመናው አየለበት እንጂ ችግሩ አልተቀረፈም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው የቆሙ ወገኖች ኢትዮጵያ ላይ ተጨባጭ ሥጋት ደቅኖ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረቱ መደምሰሱን፣ በቦታው የተተካው አልሸባባም ቢሆን መጀመሪያ ጠንካራ የነበረ ቢሆንም በሒደት ግን መዳከሙን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ጦር ማሰማራት አስፈላጊ እንደነበር ይከራከራሉ፡፡
ይህ ሁሉ ቢጠየቅም ኢትዮጵያ በተናጠልም እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሥር ጦሯን በሶማሊያ አሰማርታ ነው የቆየችው፡፡ መጀመሪያ አሚሶም (AMISOM) ቀጥሎ አትሚስ (ATMIS) በሚባሉት የኅብረቱ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሥር ተሰማርቶ የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን ሲዋጋ ቆይቷል፡፡ ለረዥም ዓመታት አልሸባብን በመዋጋቱ ሒደት ከፍተኛ የቁስና የሰብዓዊ መስዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ መሰማራትም በአንፃራዊነት የተሻለ ሰላምና የተረጋጋ የመንግሥት ሥርዓት እንዲፈጠር ማድረጉም ይነገራል፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሁሉ ተረስቶ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ይውጣ የሚል ተቃውሞ በርትቶ ይሰማል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በራሷ በሶማሊያ መንግሥት ግብዣ መግባቱም ሆነ በተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሥር መሰማራቱ እየታወቀ፣ አሁን ግን በሶማሊያ መገኘቱ እንደ ጥፋት እየተቆጠረ ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ጦር ይውጣልን የሚለው ሙግት ደግሞ በተለይም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የአገርነት ዕውቅና በመስጠት በምትኩ የባህር በር ለማግኘት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ የበለጠ እየተጠናከረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟን እንደ ሉዓላዊነት ጥሰት የቆጠሩት የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እስከ ማቋረጥ የደረሱ ሲሆን የኢትዮጵያ ጦርም ከሶማሊያ ይውጣልን እያሉ ነው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በአትሚስ ሥር በሶማሊያ ተሰማርቶ የነበረውን ጦር ከ20 ሺሕ ወደ 13 ሺሕ ዝቅ እንዲል ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በቀጣዩ ወር መገባደጃ ይህ ጦር ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ የሚደረግ ሲሆን፣ በምትኩ ደግሞ አውሶም (AUSSOM) ተብሎ የሚጠራ 12ሺሕ ኃይል በቦታው ለመተካት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር ከባድ ውዝግብ ውስጥ የሚገኙት የሶማሊያ ባለሥልጣናት፣ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አውሶም ውስጥ እንዳይካተት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ይልቅ አሥር ሺሕ ጦር ለማሰማራት ቃል የገባችው ግብፅ በሶማሊያ አዲስ ሚና እንዲኖራት እንደሚፈልጉ በይፋ አሳውቀዋል፡፡ ግብፅ ከጦር መላክ በተጨማሪ ጦር መሣሪያና ወታደራዊ ሎጂስቲክስ ወደ ሶማሊያ እያጋዘች መሆኑ ደግሞ፣ በዚያ የኢትዮጵያን የቆየ የሰላም ማስከበር ሚና ልትተካ ጫፍ ደርሳለች የሚል ግምት እያሰጠ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊያ ባለሥልጣናት በደም ፍላትና በስሜታዊነት የኢትዮጵያን ጦር ውለታ ረስተው በግብፅ የመተካት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገቡ በተደጋጋሚ ስታሳስብ ቆይታለች፡፡ በጥቅምት ወር በሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጦር ካሰማሩ እንደ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲና ብሩንዲ ካሉ አገሮች የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር በአዲስ አበባ ስብሰባ ያደረጉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ መቆየቱ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቅርቡ ከሶማሊያ ለቆ የወጣ ከፊል ጦር ኃይልን በሶማሌ ክልል ተገኝተው ሲቀበሉም ግብፆች ከሩቅ መጥተው በሶማሊያ ጉዳይ ከእኛ በላይ ለአሳር ማለታቸውና ሰላም አስከባሪ ካልላክን ማለታቸው ጤናማ አካሄድ አለመሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በእነዚህ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ብዙ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አውሶም ውስጥ እንድትካተት ብዙ ውትወታ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ መቆየቷ ከሶማሊያ አልፎ ለቀጣናው ሰላምም ያለውን በጎ ሚና ለማስረዳት ሲጥሩ ታይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ጉዳዩን አልፈለጉትም፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ኖራ አልጠቀመችም፣ እንዲያውም አልሸባብ ለረዥም ጊዜ ሥጋት ሆኖ እንዲቀጥል ነው ያደረገችው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ መግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ መፈራረሟን ተከትሎ አልሸባብ እንዲጠናከር፣ አልሸባብን የሚቀላቀሉና የሚደግፉ ሰዎች እንዲበራከቱም ምክንያት ሆናለች በሚል እየከሰሷት ነው፡፡
ከሰሞኑ ስለአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ አውሶም ሥምሪትን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃዲር መሐመድ ኑር አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እርግጠኛ የሆነው ነገር ኢትዮጵያ በአዲሱ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደማትካተት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነታችንን የጣሰች አገር ነች፤›› ሲሉ ነበር ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን በአዲሱ ተልዕኮ አለመካተት የተናገሩት፡፡
በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ በዳይሬክተር ደረጃ ከዚህ ቀደም የሠሩት ሶንከር ጎይሬ (ፕሮፌሰር) ለቪኦኤ እንግሊዝኛ እንደተናገሩት፣ ሶማሊያ ማን በአገሯ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደሚሰማራ የመምረጥ መብት አላት፡፡ በዚህ የተነሳ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ወደ ድንበሬ ጦር አትላክብኝ ብላ መከልከል እንደምትችል ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ልፈራረም ማለቷም ሶማሊያን ዓይነት ዕርምጃ እንድትወስድ የሚጋብዝ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡
የሶማሊያ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ አውሶም ተልዕኮ ሥር መካተትን ጨርሶ የፈለጉት አይመስልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚወስነው የተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ ዓርብ ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ይተላለፋል ተብሎ ቢጠበቅም በስተመጨረሻ ግን ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ነው የተሰማው፡፡
ሐሙስ ዕለት መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበርና አሸባሪው አልሸባብ ቡድንን ለመዋጋት ያደረገችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናገረዋል፡፡ አምባሳደሩ ይህን ቢሉም ኢትዮጵያ በአዲሱ የአውሶም ተልዕኮ መሳተፍ አለባት ወይም የለባትም የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት ስለሚከተለው አቋም አላብራሩም፡፡
ሐሙስ ዕለት የተመድ ፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን አብዬ የተሰማራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲራዘም መወሰኑ ታውቋል፡፡ ወደ 4,200 ጦር በአብዬ ያሰማራችው ኢትዮጵያ በዚሁ የሰላም ማስከበር ሚናዋ ለመጪው አንድ ዓመት እንደምትቀጥል ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ሚናዋ ይቀጥላል ወይ የሚለው ግን የተመድን ውሳኔ ይጠብቃል፡፡
