Monday, 18 November 2024 07:06

Written by  Administrator

በካፒታል ገበያ ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የሚነገርላቸው የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አይደለም ተባለ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ካፒታል ገበያ መምጣቱ ሌሎች ድርጅቶችንም ሊያነቃቃ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2024 ካፒታል ገበያ ጉባኤ፣ ከባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አንስቶ መካሄድ ጀምሯል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤው፤ “ዘላቂነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ ከአፍሪካና ከዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተህክሉ፣ ጉባኤው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሲያከናውናቸው የቆዩ ስራዎችን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጪዎች ለካፒታል ገበያው በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡
“በሰዎች የተሳትፎ መጠን ጉባኤው የተሳካ ነበር” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ “ይህም ጠንክረን እንድንሰራና ተወዳዳሪ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር የሚያነሳሳን ነው” ብለዋል፡፡ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት መሆኑን በማውሳትም፣ በካፒታል ገበያ አገልግሎት ለሚሰጡ ሁለት ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ሁለቱም የኢንቨስትመንት ማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሲሆኑ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ሰነደ መዋዕለ ንዋዩን ይፋ ሲያደርግ ድጋፍ የሰጠው “deloitte” የተሰኘው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች ተቋማትም ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ሃና ተህክሉ፤ “በቅርብ ቀናት ውስጥ ፍትሕ ሚኒስቴር ይመዘግበዋል ብለን የምንጠብቀው ሰነደ መዋዕለ ንዋይን ለሕዝብ የማቅረብ መመሪያ ሲወጣ፣ ካፒታል ገበያን ወደ ስራ የሚያስገቡ የሕግ ማዕቀፎች ተሟልተዋል ተብሎ ይታሰባል” ብለዋል። ከ100 በላይ ገጾችን ይዟል የተባለው ይህ መመሪያ፣ ባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር እንደጸደቀ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ “ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ቁጥጥር መመሪያ” የጸደቀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ካልተመዘገቡ ወይም በዓዋጁና በመመሪያው ከዚህ ምዝገባ ነጻ ካልተደረጉ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ለሽያጭ መቅረብ አይችሉም ተብሏል።
ከዚህ ባሻገር፣ ማንኛውም ሰነደ መዋዕለ ነዋዮችን ለሕዝብ ማቅረብ የሚፈልግ ኩባንያ ሰነዶችን ለህዝብ ከማቅረቡ በፊት ዝርዝር መረጃዎችን ያካተተ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ለባለሥልጣኑ ማቅረብና ማጸደቅ እንደሚጠበቅበት ተብራርቷል። ይህንን ከማድረጉ በፊት ማስታወቂያ ማሰራትም ሆነ ከኢንቨስተሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም፣ በመመሪያው መሰረት።
በቀጣይ ጊዜያት በአነስተኛ የገንዘብ መጠን በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበትና ለአነስተኛ ድርጅቶች አመቺ ሁኔታ በሚፈጥረው ዓዋጅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ፣ ቡድን ተዋቅሮ እንደሚሰራበትም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሚካኤል ሃብቴ በበኩላቸው፣ የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አለመሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮም ወደ ገበያው መምጣት ሌሎችን ሊያነቃቃ እንደሚችል አመልክተዋል።
“ያለ አገናኞች የካፒታል ገበያው ሊሰራ አይችልም”ያሉት አቶ ሚካኤል፤ አገናኞቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር የካፒታል ገበያው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲፈጠር የሚያስችል ስራ ወደፊት እንደሚሰሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።