ከ 9 ሰአት በፊት
የነፃ ትግል ውድድርን ከባላቸው ጋር የመሠረቱት ሊንዳ ማክማሆን የትምህርት ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ በዶናልድ ትራምፕ ታጩ።
ዎርልድ ሬስትሊንግ ኢንተርቴይንመንት (WWE) የተባለው ውድድር መሥራቿ የሥልጣን ሽግግሩን እየመሩ ካሉ ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው።
የዶናልድ ትራምፕ የረዥም ጊዜ ወዳጅ የሆኑት ሊንዳ በትራምፕ የመጀመሪያው ዘመነ ሥልጣን የአነስተኛ እና ጥቃቅን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው መግለጫ ያወጡት ትራምፕ ዕጩዋ ሚኒስትር “ለዓመታት ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም መጪውን ትውልድ ይቀርፃሉ፤ አሜሪካን በትምህርት ከዓለም አንደኛ ያደርጋሉ” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዶክተር ማሕሜት ኦዝ የተባሉት ታዋቂ የቴሌቪዥን የጤና ፕሮግራም አስተዋዋቂ ሜዲክኤይድ የተባለውን ግዙፍ የመንግሥት ድርጅት እንዲያስተዳድሩ በትራምፕ ተሹመዋል።
ትራምፕ ታማኝ ይሆኑልኛል ያሏቸውን ሹማምንት ለሥልጣን እያጩ ሲሆን የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ይህን ሹመት ማፅደቅ አለበት።
- መንገደኞችን በማጓጓዝ ቀዳሚዎቹ ግዙፍ አውሮፕላኖች የትኞቹ ናቸው?20 ህዳር 2024
- በሶማሊላንድ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ አሸነፉ19 ህዳር 2024
- የንጽህና አጠባበቅን የቀየሩ አምስት አፍሪካዊ ፈጠራዎች20 ህዳር 2024
የነፃ ትግል የሚወዱት ትራምፕ አንዳንዴ ውድድሩ ላይ ብቅ ብለው ደጋፊዎቻቸውን ያስፈነድቁ ነበር።
ሊንዳ በአውሮፓውያኑ 2009 ነው የነፃ ትግል ውድድርን ትተው ወደ ፖለቲካው የመጡት። አሜሪካ ፈርስት ፖሊሲ የተባለው የትራምፕ ተቋም የቦርድ አባል የሆኑት ሊንዳ ሥልጣናቸው በቀላሉ ይፀድቅላቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች መካከል ናቸው።
ትራምፕ የትምህርት ሚኒስቴርን እዘጋለሁ ሲሉ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ይሰማል።
ሌላኛው በትራምፕ ሥልጣን የተሰጣቸው ዶክተር ማሕሜት ኦዝ ሲሆኑ ግዙፉ የመንግሥት የጤና ተቋም የሆነውን መሥሪያ ቤት እንዲያስተዳድሩ ተሹመዋል።
የቀዶ ጥገና ዶክተር የሆኑት ኦዝ መጀመሪያ የኦፕራ ዊንፍሬይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በመቅረብ ነው ዕውቅና ያተረፉት።
ሰውዬው ለክብደት መቀነስ በሰጡት ምክር እና የወባ በሽታ መድኃኒት ኮቪድን ለመከላከል ይሆናል ብለው በሰጡት አስተያየት ከብዙዎች ዘንድ ነቀፌታ ገጥሟቸው ነበር።
የትራምፕ የሥልጣን ሽግግር ቡድን እንዳለው ዶክተር ኦዝ የጤና ሚኒስትር እንዲሆኑ ከተሾሙት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር ጋር በቅርበት ይሠራሉ።
ዶክተር ኦዝን ጨምሮ ሌሎች ተሿሚዎች በሚመጣው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ሹመታቸው ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።