ከ 8 ሰአት በፊት
ሳብሪና ካርፔንተር የተባለች አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ተገላልጣ የሙዚቃ ቪድዮ እንድትቀረፅ የፈቀዱት የኒው ዮርክ ቄስ ሹመታቸው ተገፎ ከሥራቸው ተባረሩ።
ሞንሲኞር ጄሚ ጂጋንቲየሎ ከሥራቸው መታገዳቸውን ያስታወቀው የብሩክሊን ከተማ የሮማን ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ነው።
የዘፋኟ ቪድዮ የተቀረፀው አወር ሌዲ ኦፍ ማውንት ካርሜል ቸርች ውስጥ ሲሆን ይህን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ነው ቤተ-ክርስትያኗ ምርመራ የጀመረችው።
ቄሱ ሞንሲኞር ጄሚ ቤተ-ክርስትያኗን መምራት ተስኗቸዋል አሊያም ሥልጣናቸውን በዝብዘዋል ተብለው ከመከሰሳቸውም ባለፈ ያልተፈቀደ የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።
በተባረሩት ቄስ ፈንታ አዲስ ሰው እንደተሾሙ የጠቀሰው የቤተ-ክርስትያኗ መግለጫ ሥልጣናቸውን በዝብዘዋል የተባሉት ቄስ ካለፈው ዓመት ኅዳር ጀምሮ ታግደው እንደቆዩ ጠቅሷል።
ቄሱ ቤተ-ክርስትያኗን ወክለው ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት እንዳይፈፅሙ እንዲሁም የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ እንዳይገኙም ተደርገዋል።
- መንገደኞችን በማጓጓዝ ቀዳሚዎቹ ግዙፍ አውሮፕላኖች የትኞቹ ናቸው?20 ህዳር 2024
- ትራምፕ የነፃ ትግል ውድድር መሥራቿ የትምህርት ሚኒስትር እንዲሆኑ አጩከ 9 ሰአት በፊት
- በሶማሊላንድ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ አሸነፉ19 ህዳር 2024
ፊዘር በተባለው የሙዚቃ ቪድዮ ላይ ዘፋኟ አጭር ጉርዳ አድርጋ ቤተ-ክርስትያኗ ውስጥ ስትደንስ እና ሌሎች ከቤተ-ክርስትያኗ ሥርዓት ውጭ ናቸው የተባሉ ድርጊቶች ስትፈፅም ትታያለች።
የብሩክሊን የሮማን ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ይህ ድርጊት እንደተፈፀመ ባወቀች ወቅት እጅግ “ደንግጣ” እንደነበር አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ሞንሲኞር ጄሚ ጂጋንቲየሎ ዘፋኟ ቤተ-እምነት ውስጥ የሙዚቃ ቪድዮ እንድትቀርፅ መፍቀዳቸው “የማመዛዘን አቅመ ደካማ” መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረው ነበር። ነገር ግን ከሥራቸው ስለመባረራቸው እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ሞንሲኞር ጄሚ ከሥራ ከመባረራቸው በተጨማሪ የቤተ-ክርስትያኗን ንብረት ያለአግባብ ተጠቅመዋል፤ የቤተ-ክርስትያኗን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ጠኑክ ወቀሳ የቀረበባቸው ሲሆን ምርመራ ተከፍቷል።
ቄሱ ከአውሮፓውያኑ 2019 እስከ 2021 ባለው ጊዜ 2 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ከቤተ-ክርስትያኗ ሒሳብ ከቀድሞው የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ጋር ግንኙነት ወዳላቸው ሒሳቦች አዘዋውረዋል ተብለው ተከሰዋል።
ኤሪክ አዳምስ ባለፈው መስከረም ሙስናን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች ፈፅመዋል ተብለው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባላቸው ይታወሳል።
የቀድሞው የኒው ዮርክ ከንቲባ እና ከሳቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በከተማዋ ፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።