ከ 7 ሰአት በፊት
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል በተባለበት በዚህ ወቅት የሩሲያ ጦር ዩክሬን ውስጥ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል።
ዩክሬን ከአሜሪካ የተሰጣትን ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳዔል ወደ ሩሲያ ግዛት መተኮሷን ሞስኮ አስታውቃለች። የአሜሪካን ረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን ዩክሬን እንድትጠቀም የፈቀዱት ፕሬዝደንት ባይደን ናቸው።
ባይደን ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ለዩክሬን መሬት ውስጥ የሚቀበሩ ፀረ ሰው ቦምቦችን እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል። ባይደን ይህን ያደረጉት እየገሰገሱ ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን ለመግታት ነው።
የኢንስቲትዩት ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ዋር (አይኤስደብሊው) መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ሩሲያ እአአ በ2023 ካገኘችው በስድስት እጥፍ የሚጠጋ ግዛት በ2024 ከመቆጣጠሯም በላይ በምሥራቃዊ ዶንባስ ክልል ወደሚገኙ ቁልፍ የዩክሬን የወታደራዊ አቅርቦት ማዕከላት እየገሰገሰች ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ያደረገችው ያልተጠበቀ ወረራ እየከሰመ ነው። የሩሲያ ጦር የኪዬቭን ጥቃት ወደ ኋላ ገፍቶታል። ዩክሬን ያጋጠማትን የሰው ኃይል እጥረት ከግምት በማስገባት የጥቃቱን ስኬታማነት ባለሙያዎች ጥያቄ ያነሱበት ሲሆን፣ አንድ ባለሙያ ደግሞ “ስትራቴጂካዊ ሞት” ሲሉ ገልጸውታል።
እነዚህ ለውጦች የመጡት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሥልጣን ሲረከብ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውን እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ወቅት ነው።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በጥር ወር ሥልጣናቸውን ሲረከቡ ጦርነቱን ለማቆም ቃል ገብተዋል። አንዳንዶችም ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ ሊያቋርጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
በምሥራቃዊ ዩክሬን እየገሰገሰች ያለችው ሩሲያ
በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት የሩሲያ ጦር በዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ከመግፋቱ በፊት በፍጥነት ግዛቶችን እየተቆጣጠረ ነበር። እአአ በ2023 ግን ሁለቱም ወገኖች ይህ ነው የሚባል ድል አላስመዘገቡም ነበር። ግጭቱም በአብዛኛው ባለህበት እርገጥ መስሎ ቆይቷል።
የአይኤስደብሊው አሃዞች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን 2024 ለሩሲያ የበለጠ የድል ዓመት ሆኗል። ተቋሙ ትንታኔውን የሚሰጠው ከተረጋገጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ምሥሎች እና ቪዲዮዎች እንዲሁም በወታደራዊ እንቅስቃሴ ሪፖርቶች ላይ በመመሥረት ነው።
የአይኤስደብሊው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የሞስኮ ኃይሎች በዚህ ዓመት 2700 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዩክሬን ግዛት ይዘዋል። በ2023 የያዙት ግን 465 ካሬ ኪሜ ብቻ በመሆኑ የዘንድሮው በስድስት እጥፍ ከፍ ያለነው።
በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ የመከላከያ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማሪና ሚሮን ለቢቢሲ እንደገለጹት ከሆነ ሩሲያ በአሁኑ በፍጥነት ግስጋሴዋን ከቀጠለች የዩክሬን ምሥራቃዊ ግንባር በሞስኮ እጅ “ሊወድቅ ይችላል።”
ከመስከረም 1 እስከ ኅዳር 3 ባለው ጊዜ ከአንድ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ግዛት በሩሲያ ቁጥጥር ስር ወድቋል። ይህም በቅርብ ወራት ውስጥ የአገሪቱ በላይነት መጨመሩን ይጠቁማል።
በዶኔትስክ ክልል የሚገኘውን የፖክሮቭስክ ቁልፍ የሎጂስቲክስ ማዕከልን የሚያገናኙት የካርኪቭ ክልሉ ኩፒያንስክ እና ኩራኮቭ ተመሳሳይ ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል።
- “ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር” – የፀጋ በላቸው ዘጠኝ የጠለፋ ቀናት18 ህዳር 2024
- የንጽህና አጠባበቅን የቀየሩ አምስት አፍሪካዊ ፈጠራዎች20 ህዳር 2024
- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል “ሥራውን ለመሥራት” የተወካዮች ምክር ቤትን እገዛ ጠየቀ19 ህዳር 2024
ኩፒያንስክ እና ከኦስኪል ወንዝ በስተምሥራቅ የሚገኙ አካባቢዎች በ2022 በካርኪቭ ጥቃት ነፃ ቢወጡም ሩሲያ ከወንዙ በስተምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ ቦታዎችን ቀስ በቀስ ተቆጣጥራለች። በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር በወጣው የስለላ መረጃ መሠረት የሩሲያ ወታደሮች የከተማዋን ሰሜናዊ ምሥራቅ ዳርቻ ለመስበር እየሞከሩ ነው።
በኅዳር 13 የተለጠፈ እና ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮም ከዚህ ትንታኔ ጋር የሚስማማ ነው። በቪዲዮው ላይ የሩሲያ የጦር መኪና ወደ አካባቢው ከሚያስገባው ቁልፍ ድልድይ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተቃውሞ ሲገጥመው ያሳያል።
እነዚህ ሪፖርቶች አካባቢዎቹን በቁጥጥር ስር መዋል ባያሳዩም፤ የዩክሬን ጦር ምን ያህል እንደሳሳ አመላካች ነው።
በተራራማ አካባቢ በሚገኘው እና ለቁልፍ አቅርቦቶች ወሳኝ በመሆኑ ሞስኮ ለሁለት ዓመታት የተዋጋችበትን የቩህሌዳር ከተማን በጥቅምት ወር በድጋሚ ተቆጣጥራ ሃብቷን ወደ ኩራኮቭ አዙራለች።
ከተማዋን የሚከላከለው የዩክሬን ጦር በደቡብ እና በምሥራቅ የሚደረጉ ጥቃቶችን ተቋቁሟል። መስመሩ ይበልጥ እየተጋለጠ ሲሆን፣ ሩሲያም ከሰሜን እና ከምዕራብ አቅጣጫ እንደምተከበው አስጠንቅቃለች።
የዩክሬን ጦር የስትራቴጂካዊ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ዬቭጄኒ ሳሲኮ እንደተናገሩት ከሆነ ሩሲያ “ጠንካራ ጥርሷን” በከተማዋ ዙሪያ በማስፈር ጦሩ እስኪፈርስ ድረስ ቀስ በቀስ “ይበላዋል።”
በቢቢሲ የተረጋገጠው እና ከከተማዋ የወጡ ምሥሎች እንደሚያሳዩት የመኖሪያ ሕንፃዎች ጨምሮ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰ ያሳያሉ።
ሞስኮ ዩክሬን ውስጥ 110 ሺህ 649 ካሬ ኪሜ ቦታ መያዟን አይኤስደብሊው አስታውቋል። ለማነጻጸር ያህል የዩክሬን ጦር ኩርስክን በወረረበት በመጀመሪያው ወር ከአንድ ሺህ 171 ካሬ ኪሜ ገደማ ተቆጣጠሮ ነበር። የሩሲያ ኃይሎች የዚህን ግማሽ ያህሉን መልሰው ተቆጣጥረዋል
ሩሲያ በርካታ አካባቢዎችን ብትቆጣጠርም ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች።
እአአ በየካቲት 2022 ሩሲያ ወረራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 78 ሺህ 329 ወታደሮች መገደላቸውን ቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገለግሎት ያደረገው ትንታኔ አረጋግጧል።
በዚህ ዓመት ከመስከረም እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ሞስኮ ያጣችው የጦር ቁጥር በ2023 ተመሳሳይ ወቅት ካጣችው ከአንድ ተኩል ጊዜ በላይ ብልጫ እንዳለው አረጋግጧል።
ጉዳቱ የተባባሰው በሩሲያ አዛዦች እንደሚወደድ በሚነገረለት “ሥጋ መፍጫ” በሚባለው ስትራቴጂ ነው። በዚህ ስትራቴጂ መሠረት የጠላት ወታደሮችን ለማዳከም ወደ ዩክሬን በገፍ ምልምል ወታደሮች እንዲገቡ ይደረጋል።
ሩሲያ በርካታ ቦታዎችን ብትቆጣጠርም አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ፍጥነቱ አሁንም ቀርፋፋ መሆኑን ገልጸዋል። በምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች የሰው ኃይልን እና ሃብቶችን ለመጠበቅ ቀስ በቀስ እየለቀቁ መሆኑን የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ ዴቪድ ሃንዴልማን ጠቁመዋል።
የኩርስክ ቁማር
ዩክሬን በነሐሴ ወር ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት አስደንጋጭ ወረራ ጀመረች። የኪዬቭ ወታደሮች በበርካታ የድንበር አካባቢዎችን በፍጥነት ሲቆጣጠሩ ሩሲያ ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት ለምን ጊዜ እንደወሰደባት ግልጽ አይደለም።
ወረራው እስከቀጠለ ድረስ ክሬምሊን በአገር ውስጥ ፖለቲካ ኪሳራ እንደሚደርስበት ዶ/ር ሚሮን ጠቁመዋል። በሌሎች በግንባሮች ላይ ድል እየተመዘገበ መምጣቱ እስከቀጠለ ድረስ የዩክሬን ጦር በኩርስክ እንዲቆይ ለማድረግ የሩሲያ ጦር ፍላጎት ነበረው።
አሁን ግን ሞስኮ የተወሰደባትን ግዛቷን ለማስመለስ በግልጽ ፍላጎት አሳይታለች። ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ወደ ክልሉ ተሰማርተዋል።
የተረጋገጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በኩርስክ ግዛት ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ነው። ሩሲያ በሰው ኃይል እና በመሳሪያ ረገድ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባት ነው። መረጃው በገልጽ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን የዩክሬን ጦር በክልሉ ያለው ቁጥጥር እየቀነሰ መሆኑን ነው።
ከጥቅምት ወር ወዲህ የሩሲያ ጦር በወሰደው የመልሶ ማጥቃት 593 ካሬ ኪሜ መጠን ያለው የድንበር ግዛት አስመልሷል ሲል የአይኤስደብሊው መረጃ ያሳያል።
ተደጋጋሚ ውድቀት ያጋጠማት ዩክሬን በኩርስ ያደረገችው ወረራ ከሞራል አንጻር መጀመሪያ ላይ ትልቅ ጥቅም ነበረው። ድፍረት የተሞላበት ዘመቻው ጠላትን ለማስደንገጥ እና ለመጉዳት ያለውን ችሎታ የሚያሳይ ነበር።
የኩርስክ ወረራ “የታክቲክ ብልህነት” ቢሆንም ለዩክሬን “ስልታዊ ሞት” ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ሚሮን።
“ሃሳቡ ምናልባትም ድርድር ላይ የተወሰነ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ነበር። ወታደራዊ ግብ አንጻር ኩርስክን ነፃ ለማውጣት የሩሲያን ኃይሎች ከዶንባስ አቅጣጫ ፊታቸውን እንዲያነሱ ለማራቅ ነበር። እያየነው ያለነው ግን የዩክሬን ጦር እዚያ ላይ ታስረው መቀመጣቸውን ነው።”
አንዳንድ የኪዬቭ ልምድ ያላቸው እና ውጤታማ የጦር ክፍሎች ኩርስክ ውስጥ እየተዋጉ መሆናቸው ይታወቃል። የምዕራቡ ዓለም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቁ ሜካናይዝድ ክፍሎችም ይገኛሉ።
እንደዩክሬን መሪዎች ከሆነ ሞስኮ የተወሰነ ኃይሏን ከምሥራቃዊ ዩክሬን ለማዘዋወር እንደሚያስገድዳት እና ይህም የሩሲያ ግስጋሴን ይቀንሳል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ወደ አካባቢው ያቀኑት ሩሲያ የጦር አባላት የተመለመሉት ያን ያህል ጠንካራ ጦርንት ከሌለባቸው የዩክሬን አካባቢዎች የተወጣጡ ናቸው ብለዋል ባለሙያዎች።
“የዩክሬን ወታደሮች እንደሚሉት ኩርስክን የሚያጠናክሩት የሩሲያ ወታደሮች በዋናነት ከኼርሶን እና ዛፖሪዝሂያ የተውጣጡ ናቸው” ሲል የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዩሪ ክላቪየር ለቢቢሲ ተናግሯል።
“እዚያ ያለው ጦርነት እንደ ምሥራቁ ጠንከር ያለ አይደለም። ዩክሬን በኻርኪቭ ያለውን ጥቃት ለመከላከል በመቻሏ ምክንያት በአካባቢው የተሠማሩ አንዳንድ የሩሲያ ክፍሎች ወደ ኩርስክ እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል።”
ሁለቱም ወገኖች በማናቸውም ሁኔታ ወደ ድርድር ካቀኑ የግዛቱ አስፈላጊነት ትልቅ ይሆናል። ምንም እንኳን ስለሰላም ድርድር ባይወራም ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን እንዴት እንደሚያስቆሙ ሳይገልጹ በ24 ሰዓት ውስጥ ማስቆም እንደሚችሉ ግን ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት ዩክሬን አሜሪካ ያቀረበችላትን የረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩሲያ ተኩሳለች። ይህ የሆነው ዋሽንግተን ለጥቃቱ ፍቃድ ከሰጠች ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ይህ ውሳኔ የተላለፈው ዩክሬን ኩርስክን ይዛ በመቆየት ወደፊት ለሚደረግ ድርድር እንደ መደራደሪያ ለመጠቀም ነው።
ዶ/ር ሚሮን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ግን አዲሱ ትራምፕ አስተዳደር ሥልጣኑን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በርካታ የዩክሬን ስፍራዎችን መቆጣጠር የበለጠ የመደራደር ዕድል ይሰጣታል።
“አሁን እየተቆጣጠሩት ያለው ነገር የተወሰነ ጥቅም ይሰጣቸዋል” ብለዋል።
“ከሩሲያ አንጻር ካየነው ከዩክሬናውያን በጣም የተሻሉ መደራደሪያዎች አሏቸው።”