የጥራት ጉድለት ያለባቸው የሕክምና መሣሪያዎች በታካሚዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋቱ ነው የተገለጸው

ማኅበራዊ በሕክምና መሣሪያዎች ጥራት መጓደል የሚደርስ ጉዳት ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋቱ ተገለጸ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: November 20, 2024

በሕክምና መሣሪያዎች የጥራት መጓደል ምክንያት በዜጎች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋቱን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

‹‹ብሔራዊ የሕክምና መሣሪያ ቪጂላንስ ማዕከል›› ተብሎ የሚጠራው የሕክምና መሣሪያዎች አሉታዊ ክስተቶች ማለትም ሞት፣ አካላዊ ጉዳት፣ የጤና መታወክ፣ መሣሪያው የታለመለት ዓላማ አለማከናወን፣ የሕክምና መሣሪያ ያለውን ጉድለት (ሙሉ አለመሆን)፣ በተሳሳተ ምርመራ ውጤት ምክንያት ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት መተግበር መጀመሩን የባለሥልጣኑ የሕክመና መሣሪያ አምራቾች ኢንስፔክንሽንና ሕግ ማስፈጸሚያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሚኪያስ ጳውሎስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሥርዓቱ የተዘረጋው ከዚህ ቀደም  የሕክምና መሣሪያ በሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በባሙያዎችም ሆነ በተገልጋዮች ሪፖርት ስለማይደረግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሚኪያስ፣ በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ችግሮች በመስተዋላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ያስታወሱት አቶ ሚኪያስ፣ በሰመመን መስጫ መሣሪያ ምክንያት የሰው ሕይወት ማለፉና በመተንፈሻ መሣሪያ ችግር ሳቢያ በግለሰቦች ላይ የደረሰ ጉዳት መድረሱ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

ጥራት የጎደለው ኮንዶም ወደ አገር ውስጥ ስለመግባቱ በጥቆማ እንደተደረሰበት አስታውሰው፣ የእጅ ጓንትና ሲሪንጅ በተመሳሳይ መንገድ ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የመድኃኒት ‹‹ቪጂላንስ›› የሚል ጥቆማ የሚሰጥበት ሥርዓት እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን የሕክምና መሣሪያ ‹‹ቪጂላንስ›› ወይም ጥቆማ የሚሰጥበት ሥርዓት አልነበረም ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማት በሕክምና መሣሪያ ብልሽትና ጥራት ሳቢያ ሰው ላይ የሚደርስ ጉዳት ሪፖርት እንደማይደረግ፣ ባለሥልጣኑ ባደረገው ዳሰሳ ጥናት በመታወቁ ግን ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቀላል መመርመሪያዎች በምሳሌ ሲያስረዱ ሲያነሱት ያልፀነሰች እንስትን እንደፀነሰች የሚያሳይ የመመርመሪያ መሣሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን በዳሰሳ ጥናት እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡

የሕክምና መሣሪያዎች በጥራት፣ በደኅንነትና በብቃት ማነስ ምክንያት በዜጎች ላይ የተለያዩ ችግሮች ሊያስከትሉ እንደሚችሉና ችግሩ ሲከሰት ደግሞ ሪፖርት የሚደረግበት አግባብ ከፍ እንዲል ለማድረግ በዘርፉ ብዙ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሚኪያስ ገለጻ፣ የሕክምና መሣሪያ ጥራትና መሰል ችግሮች ከሁለት ወራት በፊት ከ200 በሚበልጡ የጤና ተቋማት በተደረገው የደሳሳ ጥናት የተለያዩ እክሎች ተገኝተዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት ጄኔራል ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች የሚያገኙበትና በዚህም የሕክምና መሣሪያዎች ብቃት ማነስ፣ የጥራትና የደኅንነት ችግሮች መስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀላል መመርመሪዎች፣ ሲሪንጅ፣ ጓንትና የመሳሰሉ አላቂ የሕክምና መሣሪያዎች ጀምሮ እስከ ትልልቅ መሣሪያዎች ችግሮች እንዳሉባቸውና መሣሪያዎቹን የሚጠቀሙ ባለሙያዎችም ክፍተቶች እንዳሉባቸው ነው የገለጹት፡፡

በአብዛኛው በዕርዳታ የሚገቡ የሕክምና መሣሪያዎች አገልግሎት በትክክል እንዳልሰጡ በዳሰሳ ጥናት መታወቁን የገለጹት አቶ ሚኪያስ፣ በርከት ያሉ የሕክምና መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ ሳይውሉ በክምችት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

የባለሥልጣኑ የሕክምና መሣሪያዎችና ምዝገባና ፈቃድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ታከለ እንዳሉት የሰዎችን በሽታ ለማከም ምርመራ ለማድረግ የደም ሥርን፣ አጥንትንና የልብ ምትን ተክተው የሚሠሩ የሕክምና መሣሪያዎች ችግር ቢኖርባቸው ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት ነው የተዘረጋው፡፡.