November 20, 2024
ጥንታዊ መዲናና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ የሃይማኖት ማዕከል ብሎም ክርስቲያናዊ መንግሥት በዓለም ውስጥ የመሠረተች ናት፡፡ በውስጧም እጅግ በጣም የተቀደሰው ጽላትና የክርስትና ሃይማኖት የተለየው መገለጫ ይገኛል፡፡ በዓለም ይገኙ ከነበሩት አራቱ ኃያላን መንግሥታት ከሮም፣ ከፋርስና ከቻይና ጋር የምትጠቀስ ነበረች፡፡
ለኃያልነቷ ምስክር ግዙፍ ሐውልቶች፣ ግዙፍ የድንጋይ፣ ጠረጴዛ፣ ግዙፍ የዘውድ መሠረታዊ ድንጋይ የተሰባበሩ ትላልቅ ዓምዶች፣ የነገሥታት መቃብር ከተለያዩ የማይዳሰሱ አፈ ታሪኮችና ባህሎች ጋር ተገኝታለች፡፡ ዜና መዋዕሏን በድንጋይ ላይ በሦስት ቋንቋዎች (በግእዝ፣ ሳባና ግሪክ) በመጻፍ እስከ አሁን ዘመን በተላለፉት ብራናዎች ላይ ከትባ አቆይታለች፡፡ የዕውቀት መንገድ፣ ብልጫ ያላት የባህልና የንግድ ማዕከል ሆናም ታይታለች፡፡ ይህች የኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ሉል የሆነችው አክሱም የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ ማሳያ በመሆኗ ነው ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገባት። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተከስቶ በነበረው ጦርነት በሕዝቡ ላይ ከኅልፈተ ሕይወት እስከ ጉዳት ደርሷል፡፡ ምትክ የማይገኝላቸው ቅርሶችም ጠፍተዋል፣ ተጎድተዋል። ሆኖም የፕሪቶርያ ስምምነትን ተከትሎ ዛሬ ላይ አክሱም ሰላም ሰፍኖባታል፡፡ ውስን ቢሆኑም ቱሪስቶች እየጎበኟት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ከወዲሁ ጎብኚዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል፡፡ በተለይ ምዕመናንም ሆኑ ቱሪስቶች የሚገኙበትን የኅዳር ጽዮን በዓልን ለማክበር ዝግጅቶች ከተጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ‹‹ዳግማዊት ኢየሩሳሌም›› የምትባለው አክሱም ጽዮን የኅዳር 21 በዓሏን ለማክበር ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የሚመጡ እንግዶችን ቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነች የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹በሰላም ኑ›› ብለው ጥሪ አድርገዋል፡፡ እንግዶችን ከወዲሁ ለመቀበል ከተዘጋጁት መካከል የአክሱም ሆቴሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚገኙት በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሆቴሎች በማኅበራቸው አማካይነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ መሰንበቻውን አክሱም ጽዮን የተገኘው ሔኖክ ያሬድ የአክሱም ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአርማህ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት የሆኑትን አቶ ጎይትዖም ትዕዛዙን አግኝቶ ስለ አክሱም ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅድሚያ ስለድርጅትዎና ስለ አካባቢው የቱሪዝም ገጽታ ቢገልጹልን?
አቶ ጎይትዖም፡- አርማህ ኢንተርናሽናል ሆቴል በኢንቨስትመንት መስክ ተሰማርቶ ሥራ የጀመረው በኅዳር 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሁለት ዓመት ከሠራ በኋላ በዓለም በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ባልተጠበቀ ሁኔታ እንዲቀዛቀዝ ሆኖ ሠራተኞችን ቀጥረን ለማሠራት የተቸገርንበት ሁኔታ ነበር፡፡ እሱን እንደምንም ብለን ከተወጣነው በኋላ ደግሞ በክልላችን በተፈጠረው አስቸጋሪ ጦርነት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ምንም መሥራት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ ቱሪዝም እንደሚታወቀው ከሁሉም በላይ ሰላም አለመኖሩ በክልላችንና በከተማችን በአካባቢያችንም በተፈጠረው ጦርነት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በኢትዮጵያ ለነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም የቱሪዝም ፓኬጁ ወደ አንድ ቦታ ብቻ አይደለም እንግዳ የሚመጣው፡፡ ታሪካዊ ቅርስና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለባቸውን የሰሜን ኢትዮጵያ ለማየት ይመጣል፡፡ በፓኬጁ አክሱም ሲኖር ቱሪስቱ የበለጠ ይፈልገዋል፡፡ በትግራይ የነበረው ትልቁ ጦርነት በሰሜኑ ለነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጎድቶታል፡፡ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪው ለአገሪቱ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ነው፡፡ ቱሪዝም የሚንቀሳቀሰው ሆቴልን በምናስተዳድር ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከትናንሽ የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ ነው፡፡ ከጉሊት እስከ ሱፐር ማርኬት ተያይዞ ገበያው ይንቀሳቀሳል፡፡ ጦርነት በመነሳቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴያችንን በጣም ተጎድቶ ቢቆይም የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተደረገ በኋላ በአገራችን በተፈጠረው የሰላም ሁኔታ በትልቅ ሞራል ውስጥ ሆነን የቱሪዝም እንቅስቃሴያችን ወደነበረበት እንመልሰዋለን ብለን ተስፋ እያደረግን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ የአክሱም የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር አክሱምን በሚገባ ልክ አስተዋውቃችኋል፣ ገበያውንስ አምጥታችሁታል?
አቶ ጎይትዖም፡- አክሱምን ይበልጥ አስተዋውቀናል፣ ገበያውንም አምጥተነዋል ማለት አያስደፍርም፡፡ አክሱም እምቅ የቱሪዝም ሀብት ያለበት ከተማ ነው፡፡ ቅድስት ከተማ፣ የሃይማኖት መሠረት፣ የታሪክና የሥልጣኔ፣ የቅርስ መሠረት ነው፡፡ ይህ ትልቅ የቅርስ፣ የሥነ ጥበብ ሀብት ከሚገባው በላይ ለዓለም አስተዋውቀን መጠቀም ያለብንን ነገር ተጠቅመናል ብለን አናስብም፡፡ ብዙ ይቀረናል፡፡ ከሦስት ሺሕ፣ ከአራት ሺሕ ዓመት በፊት የነበሩት የሠሩትን ሥራ ለመሥራት ሳይሆን፣ የሠሩትን እንኳ ነግረን አስተዋውቀን ለመጠቀም አልቻልንም፡፡ የሃይማኖቱም የፍልስፍናውንም የቅርሱንም መሠረት፣ የት አገኛለሁ ካልህ መልሱ አክሱም ነው፡፡ በሥነ ቅርስም ሆነ፣ በታሪክ አሁን አሉ የሚባሉ የፊዚክስ ምሁራንን ቆሞ ያለውን 50 ቶን እና 70 ቶን የሚመዝን ትልቁን ሐውልት ጥንቶቹ በምን ፎርሙላ ነው እንዲቆም አደረጉት ብለን ስንጠይቅ የሚመልስልን ሰው የለም፡፡ በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት ሳይንቲስቶች ነበሩ ነው የምንለው፡፡ ከባድ ክብደት ያለውን ቅርስ ከመሬት በላይ ከመሬት በታች ክብደቱን አዋህደው በምን ሥሌት ነው የሠሩት ብለን ስናስብ ግራ ነው የሚገባን፡፡ እንዴት ሠሩት፣ እንዴት ቀረፁት፣ እንዴትስ አመጡት ማለት ካልሆነ ምላሹን የሚሰጠን አናገኝም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ዝማሬም ቢሆን ስለ ቅዱስ ያሬድ የሚነገረውና የሆነው ነገር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይህንን ራሱ በሥርዓቱ አስተዋውቀን አልተጠቀምንበትም፡፡ አገሪቱ ያለባትን ከቱሪዝም ሀብት ጥቅም ገና አላገኘችም፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ታሪክና ቅርስ እምብዛም ሳይኖራቸው የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ይዘው የሚያገኙት ዓመታዊ የኢኮኖሚ ገቢ ስናይ ከፍ ያለ ነው፡፡ እኛ ጋ ሁሉን አሟልተን የምናገኘው ገቢ ግን ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ እያዘንክ መቆየቱ ጥሩ አይደለም፡፡ ይህንን ችግር መስበር አለብን፡፡ እንዴት ነው የምንሰብረው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት፡፡ የውጭ ቱሪስት ብቻ አይደለም መጠበቅ ያለበት፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ አካባቢ አራትና አምስት የአፍሪካ አገሮችን የሚያክል ክልል ነው፡፡ በደንብ ካስተዋወቅህ ‹‹አክሱምን እንጎብኝ የሚል ፕሮግራም ከያዝህ ተጠቃሚ ትሆናለህ፡፡ ቱሪስት በየሳምንቱ ማምጣት ብንችል፣ ሰላም ነው አገራችሁን እዩት ብለን ካልን የአካባቢው እንቅስቃሴ ይቀየራል፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የላቀ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ወደ አማራም ሆነ ደቡብም ሄደን አክሱም ሰላም ነው፣ ይህን የሚመስል ቅርስ አለን፣ ለምን አንጎበኝም ብለን ብናስተዋውቅ ማግኘት ያለብንን ነገር እናገኛለን፡፡ እኛ በተለያዩ ምክንያቶች ማስተዋወቅ አልቻልንም፡፡ ሚዲያው አጋር ሆኖ ከሠራ ቀስ በቀስ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ይጨምራል፡፡ ማስተዋወቅ ያለብንን ነገርንም በቻልነው መጠን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ትንሽ ጀምረናል፡፡ አለን ብለን መቆየት ትርጉም የለውም፡፡ የተወሰነ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ መጣር ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን የሠሩትን ማስተዋወቅ ካልቻልን ደግሞ የድህነት አረንቋ የምንይዘው፡፡ ስለዚህ ትልቅ ኃላፊነት አለን ብለን እናስባለን፡፡ ከሁሉም ጋር ተባብረን ለማስተዋወቅ እንዘጋጃለን፡፡
ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ስም ‹‹አርማህ›› እንዴት ተመረጠ? ሕንፃው ከአክሱም ኪነ ሕንፃ የቀዳው አለ?
አቶ ጎይትዖም፡- አንዳንዴ ስሞች በስሜት ከተለያዩ ገጠመኞች በመነሳት ይመረጣሉ፡፡ እኛ አርማህ ያልነው በአክሱም በነገሠው ንጉሥ አርማህ ስም ነው፡፡ አርማህ የነበረበት ሰባተኛው መቶ ዘመን ሳንቲሞች ለመገበያያነት በብዛት ሥራ ላይ የዋሉበት እንደነበር ይነግሩናል፡፡ ሌላው የሃይማኖት መቻቻል የታየበት ጊዜ ነበረበት ብለው የጻፉም አሉ፡፡
‹‹አልነጃሺ›› ንጉሥ ብዙ ጊዜ እንላለን፡፡ በንጉሥ አርማህ የንግሥና ጊዜ ተሰደው የመጡ ሰዎችን በሰላም ነው የተቀበሉት፡፡ ስለዚህ በገንዘብ መገበያየት ትልቅ ደረጃ ደርሶበት የነበረው ወቅት መሆኑ፣ በሌላ በኩልም የሃይማኖት መቻቻልን ያሳዩ ንጉሥ ስለሆኑ፣ ለሁሉም መሠረት ይሆናሉ ብለን ነው የሰየምነው፡፡ ብዙ ጊዜ በአክሱም ሕንፃ ሲሠራ አርክቴክቶቹ በተወሰነ መልኩ ትውፊቱን ለመያዝ ይጥራሉ፡፡ ግን እንደሚገባው ተሠርቷል ማለት ያስቸግራል፡፡ በውጭ ሆነህ ስታየው የሐውልት ቅርፅ ያለው እንዲመስል አርክቴክቶቹ ይሞክራሉ፡፡ ግን ማድረግ የሚገባንን ያህል እያደረግን አይደለም፡፡ ወደፊት ንጉሥ አርማህን ሊገልጹ የሚችሉ ነገሮችን ለማሟላት እያሰብን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአክሱምን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ምን እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ጎይትዖም፡- እኛ ከጦርነት ገና ስለወጣን ብዙ እንቅስቃሴ አልጀመርንም፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴሎች ማኅበር እንዲያግዙን እየጠየቅን ነው፡፡ ዓምና የጋይድ፣ የቱር፣ የሆቴል ተቋማት ያካሄዱት ወርክሾፕ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የቱሪዝም እንቅስቃሴውም ወደነበረበት ለመመለስ፣ ሰላሙ ከሰፈነ በኋላ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ዳግም መከፈቱን የሚያመለክት ሥነ ሥርዓት ማካሄድ አለብን በማለት ተንቀሳቅሰናል፡፡ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች አክሱም በመጡ ጊዜ ሰላም አለመኖሩን የሚያሳየውን ቀይ ምልክት ካላነሳችሁልን፣ እንዴት ቱሪስት ይመጣልናል ብለን ጠይቀናቸዋል፡፡ እኛኮ የመጣነው ሰላም አለ ብለን ነው፡፡ ምስክሮች ነን ብለው አጭር መልስ ነው የሰጡን፡፡ የቀይ መስመር ተነስቶ ትግራይ ሰላም ነው፣ ቱሪስት ገብቶ መውጣት ይችላል የሚል እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥረት እናደርጋለን፡፡ እንደ ማኅበር የአክሱም ዮሐንስ አራተኛ ኤርፖርትን ለመክፈት ብዙ ጥረት ነበር ያደረግነው፡፡ ኤርፖርቱ ተከፈተ ብሎ ሪቫን ከመቁረጥ ይልቅ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ከቱሪዝም ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች እንዲመጡና የአክሱም ቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ለማብሰር ሞክረን ነበር እዚህ ላይ አክሱምን አየህ ማለት የሰሜኑን ሥልጣኔ መነሻን አገኘህ ማለት ነው፡፡ መነሻን ስታይ ተከታዩን ለማየት ትነሳለህ፡፡ የአክሱም ብቻ ሳይሆን ተያያዥ የሆኑት ላሊበላና ጎንደርም መታየት አለባቸው፡፡ በፓኬጅ የሚያያዙ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየከሰረም ቢሆን ካለማመደልን ቱሪስቶች ሊመጡልን ይችላሉ፡፡